በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀዳሚ ስም ያለውና በመንግሥት ባለቤትነት ሥር የሚተዳደረው ሂልተን አዲስ አበባ፣ በተጠናቀቀው የ2017 የሒሳብ ዓመት 308.6 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ።
ካፒታል ከኩባንያው ኦዲት ሪፖርት እንደተመለከተው ፣ ሂልተን በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ጠቅላላ ገቢ 506.4 ሚሊዮን ብር ደርሷል። ይህ አኃዝ በ2016 የበጀት ዓመት ከነበረው 256.5 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ97 በመቶ ገደማ ዕድገት አሳይቷል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) በበላይነት የሚመራው ይህ ኩባንያ ፤ ከታክስ በፊት ያለው ትርፍ ደግሞ 437 ሚሊዮን ብር ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ መንግሥት የሚፈልገውን የትርፍ ግብርና ሌሎች ተቀናሾች ከተደረጉ በኋላ ሆቴሉ ከ 308 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል። በ2016 የሒሳብ ዓመት የተጣራ ትርፉ 140.4 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደነበር ይታወሳል።
ኩባንያው ካስመዘገበው ከፍተኛ ትርፍ ውስጥ 317 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ድርሻ ለመንግሥት (ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ) በትርፍ ድርሻ ወይም በዲቪደንድ መልክ እንዲከፍል መወሰኑ ተገልጿል። በተጨማሪም የሆቴሉ አጠቃላይ የሀብት መጠን 1.98 ቢሊዮን ብር መድረሱ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የሆቴሉ ማኔጅመንት በሪፖርቱ ላይ እንደገለጸው፣ ይህ አስደናቂ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በዋናነት በአዲስ አበባ እየታየ ካለው የቱሪዝም ዘርፍ ማገገም፣ በከተማዋ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች መጨመር እና የሆቴሉን የአሠራር ቅልጥፍና ለማሻሻል ከተደረጉ ጥረቶች የመነጨ ነው።
የሂልተን አዲስ አበባ ሆቴል ባለቤት የሆነው የልማትና ሆቴሎች አክሲዮን ማኅበር ካገኘው ገቢ ውስጥ አብዛኛው ማለትም 484.4 ሚሊዮን ብር የሚሆነው የተገኘው ከሆቴሉ የትርፍ ክፍፍል መሆኑ ተገልጿል።
