ሃይንከን ኢትዮጵያ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ7 ሚልየን ብር ወጪ ያስገነባቸውን የወተት ላሞች እርባታ እና የዶሮ እርባታ ማዕከላት ለተመረጡ 22 የአካባቢው አባወራዎች ትናንት ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም አስረክቧል፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኀብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በማሰብ በበደሌ ከተማ አጠገብ የተገነባው ይህ ፕሮጀክት፤ በቂ ጥናት ተደርጎበት የተገነባ እና በትክክል ለሚያስፈልጋቸው ተረጅዎች የተሰጠ መሆኑን የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ የሆኑት እና የጅማ ዩንቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ምክትል ኃላፊ ፍቅረ-ማርያም ገዳ-አራለሜ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
እንዲህ አይነት ፕሮጀክቶችን እየገነቡ ለማህበረሰቡ ማስረከብ ከፋብሪካዎችና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠበቅ መሆኑን የሚገልጹት ዋና አስተባባሪው፤ “በዚህ መልኩ ማህበረሰባችንን ተጠቃሚ ማድረግ አገርን መጥቀም ስለሆነ ይህ ቀጣይነትም ይኖረዋል” ብለዋል።
አሁን ላይም ሃይኒከን ኢትዮጵያ 300 ዶሮዎችን እና 5 የፈረንጅ ላሞችን በመግዛት የማርቢያ ፕሮጀክቱን ገንብቶ ለተመረጡ 22 የአካባቢው አባዎራዎች ማስረከቡ ተናግረዋል።
የሃይንከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ባርት ዲ ክኒንክ በበኩላቸው፤ ኩባንያው ማኀበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እና በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን ለመደገፍ ሰፋፊ ሥራዎችን በመላ ሀገሪቱ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ሃይንከን ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ብቻ 14 ቢልየን ብር የግብር ግዴታውን በሀገር አቀፍ ደረጃ በመወጣት ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረጉን የገለጹ ሲሆን፤ ይህም ከግሉ ዘርፍ በግብር ከፋይነት አንደኛ እንዳደረገው ጠቅሰዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ፕሮጀክቱ ተገንብቶ የተሰጣቸው ቤተሰቦች በተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱም ተጠቃሚ ለመሆን በርትተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ይህ ሥራ እንዲሰራ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሀሳብ አመንጭነት ጀምሮ እቅዱ ተፈፃሚ እስከሚሆን ድረስ በዘርፉ ያለውን እውቀት እና የሰው ኃይል በማቀናጀት ላቅ ያለ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ስለመወጣቱ ተገልጿል።
ጅማ ዩንቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ባሻገር ከዩኒቨርሲቲው ወጣ ብሎ ሰፋፊ ማህበረሰብ ተኮር ሥራዎች ላይ በመሳተፍ አመርቂ ሥራዎችን እየሰራ ስለመሆኑ የገለጹት የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ፤ “የዩኒቨርሲቲው አንዱ አላማ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ስለሆነ ይህንንም በሚገባ እየተወጣ ነው” ብለዋል።
አክለውም “ዩንቨርሲቲው ማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት ፍልስፍና ስለሚከተል እንደዚህ አይነት ሥራዎችን ከአጋዥ አካላትና ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር እየሠራን እንገኛለን” በማለት ገልጸው፤ “በዕለቱ በበደሌ ከተማ ተመርቆ ለአባዎራዎች የተሠጠውም ይሔው ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም ሃይኒከን ኢትዮጵያ በደራሽ የጋራ መኖርያ ቤት ፕሮጀክት አማካይነት በ32 ሚልየን ብር ወጪ 30 ቤቶችን ከእነ የጋራ መጸዳጃና ማብሰያ ቤቶች ለመገንባት የሚያስችል ስምምንት ከበደሌ ከተማ አስተዳደር የፈጸመ ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
