
አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ከ1975 ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትያትር ጥበባት በቢኤ ዲግሪ ተመርቆ ሀገር ፍቅር ቴአትር ተመደበ። የወጣትነቱንና ጉልምስና እድሜውን በዚያ አሳለፈ። ሀገር ፍቅር ቴአትር ለኪሮስ ኃ/ሥላሴ መ/ቤቱ ብቻ ሳይሆን ትዳሩም ሕይወቱም ጭምር ነው። ከባለቤቱ አርቲስት ፀዳለ ግርማ ጋር ትዳር የመሰረተውና ልጆች ያገኘው ከሀገር ፍቅር ቴአትር ነው።
ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ከመደበኛው ስራ ጡረታ ይውጣ እንጂ ዛሬም ሀሳብና ውሎው፣ ማህበራዊ ሕይወቱ ሀገር ፍቅር ቴአትር ነው። “ሳልሳዊው ባልንጀራ ” ፣ “የቬኑሱ ነጋዴ ” ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ ” ፣ “ጣውንቶቹ ” ፣ “አሉ ” ፣ “ባልቻ አባነፍሶ” ን የመሳሰሉ ትያትሮች ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል። በርካታ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተውኗል። ሀገር ፍቅር ቴአትር እና የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮን በተለያዩ ጥበባዊ ሀላፊነቶች መርቷል። በሚሊኒየሙ ጊዜ የአዲስ አበባ ሚሊኒየም ጽ/ቤትን በሊቀመንበርነት መርቷል ።
ኪያ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር የተመደበበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትያትር ጥበባት በመጀመሪያ ዲግሪ ማስመረቅ እና በየጥበብ ቤቶች መመደብ የጀመረበት ወቅት ስለነበረ በወቅቱ በነባሮቹ አንጋፋ የጥበብ ሰዎችና በወጣቶቹ ምሩቃን መካከል የተፈጠረውን መጓተት ለማርገብና ዘመናዊውን እውቀት በልምድ ከካበተው ችሎታ ጋር አቀናጅቶ ለመስራት የኪሮስ ሚና ትልቅ ነው።
በአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ኃላፊነቱ ወቅትም ወጣቶች የተለያዩ የትያትር ክበባትና ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ተሰጥኦዋቸውን ወደ መድረክ እንዲያመጡ የኪያ አበረታች አቀራረብ ግዙፍ ነው። ከወጣቶች ጋር እንደ ወጣት፣ ከአዛውንቶቹ ጋርም እንደ እነሱ መሆን የሚችል በሁሉም የተወደደና የተመሰገነ ብቁ የጥበብ ሰው ነው። በዚህም “ኪሮስ” የሚለው ስሙ ቀርቶ በወዳጆቹ ዘንድ “ኪያ” መጠሪያ ስሙ ሆኗል።
ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ እና የኪሮስ ኃ/ሥላሴ ልጆች ሕብረት ፈጥረው የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9:30 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ደማቅ የክብርና የምስጋና መርሐ ግብር አዘጋጅተውለታል።
በዕለቱ ፦
ሙዚቃ ( በሀገር ፍቅር ቴአትር እና መሐሪ ብራዘርስ ባንድ ) ከታዋቂ ድምጻውያን ጋር ፤
በስሙ የተዘጋጀና በታዋቂ ተዋንያን የሚቀርብ አጭር ድራማ ፤
በፖሊስ ሰራዊት የማርሽ ባንድ ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎች ፤
ዶኩመንታሪ ( ሕይወቱንና ስራዎቹን የሚዘክር ) እና ሌሎች መርሐ ግብሮች ይቀርባሉ ተብሏል።
@አዲስ አድማስ