የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ አመራር አቶ ግርማ ሰይፉ የተጻፈው ከኢህአዴግ ውድቀት ጀምሮ የነበረውን የለውጥ ሒደት የሚያስዳስስ “ለውጥ እና ነውጥ፤ የአትክልተኛው ማስታወሻ” የተሰኘ ባለ 280 ገጽ መጽሐፍ በ1 ሺህ ብር የሽፋን ዋጋ ለንባብ በቅቷል።
የመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
በ6 ዋና ዋና ክፍሎች የተዋቀረው መጽሐፉ ሰላማዊ የዴሞክራሲ ሽግግርን፣ ምርጫን፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን፣ ቀጣናዊ ጉዳዮችን እና ዘላቂ ሰላምን ይዳስሳል ተብሏል።
በምረቃው ወቅት አቶ ግርማ “በሀገሪቱ የሚታዩ የፖለቲካ ችግሮች እና ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች ወደ ውይይት በመቅረብ ለውጥ ማምጣት ይቻላል” ብለዋል።
ደራሲው አክለውም፤ መጽሐፉን በማንበብ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግና ሐሰተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን በጋራ መመከት እንደሚገባ ተናግረዋል።
መጽሐፉ ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ የተከሰቱ ችግሮችን፣ የከተሜነት እና የአዲስ አበባ የልማት ሥራዎችን ዳስሷል ተብሏል።
