“ለ40 ዓመታት ሃብቴን በሙሉ ትቼ መጅሊሱን ሳገለግል ኖሪያለሁ”ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ

Date:


ይህ ቃለ ምልልስ ግንቦት 2011 ዓ.ም ከግዮን መጽሔት ያደረጉት ሲሆን ምንም ማስተካከያ ያልተደረገለት መሆኑን እናስታውቃለን ።


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንግግራቸው፣ በሃገራዊ ጉዳይ ባላቸው ተሳትፎ፣ሰዎችን በሙሉ በአንድ የሚመለከት አስተሳሰባቸው፣ በአጠቃላይ በሁለንተናቸው አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማራኪ የሆኑ የሃይማኖት አባት ብቅ ብለዋል፡፡

የእኚህ አባት ረጋና ለስለስ ያለ አንደበት ውስጥን በሚያድሱ ቃላት የታጀበ ነው፡፡ እሳቸው ሲናገሩ መንፈስ ይታደሳል፣ሰላም ይነግሳል፣ልብ ይረሰርሳል፡፡ እኚህ አባት ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ይባላሉ፡፡ “ሙፍቲ” የሃይማኖታዊ ማእረግ ስያሜያቸው ነው፡፡ በሃገራችን በጣት የሚቆጠሩ ሙፍቲዎች ነው ያሉት፡፡ ሐጂ በቅርቡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን በበላይነት የሚቆጣጠረው የዑለማዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው መጅሊሱን በማደራጀት ላይ ይገኛሉ፡፡


የግዮን መጽሔት ባልደረባ ሁሴን ከድር በሥራቸውና በሕይወት ታሪካቸው ዙርያ እንዲሁም ስለ አዲሱ የእስልምና ጉዳዮች አሰራር በተመከለከተ ከሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቦታል ፡፡


በወሎ ክ/ሀገር ለጋምቦ ወረዳ፣ ገነቴ በምትባል መንደር ጠላት ኢትዮጵያን በወረረ በሁለት ዓመቱ ግንቦት 21ቀን 1929 ነው የተወለዱት፡፡ አባታቸው አቶ ኢድሪስ ዘለቀ፣ እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ መነን ሽፋው ይባላሉ፡፡ ገና በለጋ እድሜያቸው የእውቀት ፍቅር በልባቸው ሰርጾ፣ ገበሬ አባታቸውን አስፈቅደው የእስልምና እውቀትን ለመሰብሰብ መንገድ ጀመሩ፡፡


በሐጂ ዑመር የልጅነት ዘመን እውቀት አሳሽ፤ በቀላቢ አሊያም ዞሮ መንደርተኛን በመጠየቅ ነበርና ስንቁን የሚቀለበው፣ እሳቸውም በለጋነት እድሜያቸው ለቀላቢያቸው ከብት በማገድ፣እንጨት በመፍለጥ የጉልበት አገልግሎት እየሰጡ፤ ባላቸው ቀሪ ሰዓት እውቀትን ይሰበስቡ ጀመር፡፡

ይህ አስደናቂና ለብዙዎች ትምህርት የሚሆነው የልጅነት ታሪካቸው ቢዘረዘር መሽቶ ይነጋል እንጂ በቀላሉ አያልቅም፡፡ በጽናት ያውም የቤተሰብ የሞራልም ሆነ የስንቅ ድጋፍ ሳይደረግላቸው፣ እሳቸውን ከእውቀት ገበታ ለማስተጓጎል በትዳርና በግብርና እንዲታሰሩ ቢደረጉም ከዓላማቸው ውልፍት ባለማለት ያጋጠማቸውን ፈተና በሙሉ በጽናትና በብልሃት በመወጣት ካሰቡበት ለመድረስ ችለዋል፡፡


ሐጂ ዑመር ከ50 ዓመታት በፊት አዲስ አበባ የመጡት ኡስታዛቸውን/መምህራቸውን/ በመፈለግ ነበር፡፡ ደሴ የወ/ሮ ስህን ት/ቤት መምህር በነበሩት፣ በደርግ ዘመን የእስልምና ጉዳዮች ሊቀመንበር በሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ጀምረውት የነበረውን ትምህርት ለመቀጠል እንጂ አዲስ አበባ ለመኖር አልነበረም፡፡

እሳቸው መምህራቸውን የፈለጉትን ያህል ደሴ ውስጥ ያስተምሯቸው የነበሩ የእሳቸው ተማሪዎችም አሳቸውን ፍለጋ ተከትለዋቸው መጥተዋል፡፡ ሆኖም ለዓመታት የሰበሰቡት እውቀት ሌሎችን ለማስተማር ከበቂ በላይ መሆኑን የተረዱት ሐጂ ሳኒ፤ በአንዋር መስጂድና በመስጂድ ኑር /በተለምዶ በኒን መስጅድ በሚባለው/ እንዲያስተምሩ ተመደቡ፡፡

እሳቸውም ግማሽ ቀኑን ለራሳቸው እውቀትን ሲሰበስቡ፣ ቀሪውን የቀን እኩሌታና ምሽት ደግሞ በማስተማር ያሳልፉ ጀመር፡፡
ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከማስተማር ባሻገር ከ50 በላይ ሃይማኖታዊ መጽሐፍትንም ጽፈዋል፡፡ ቅዱስ ቁርአንንም ተርጉመዋል፡፡ በቅርቡ የቁርአን ትርጉም ሥራቸው በሲዲ ተሰራጭቷል፡፡ በ50ዓመታት የአዲስ አበባ ቆይታቸው ቅዱስ ቁርአንን ከ300 ጊዜ በላይ ትርጉም አስተምረዋል፡፡ ከጻፏቸው መጽሐፍት የሕትመት ብርሃንን ያገኘው አንድ ብቻ ነው፡፡


ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በተመረጡባቸው ቦታዎች ሙስሊሙን ሕብረተሰብ በቅንነትና በፍትሕ ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ ያላቸው የእውቀት ደረጃ ከፍተኛነትን የተመለከተው ከ25 ዓመታት በፊት የነበረው የአዲስ አበባ የመጅሊስ ምክር ቤት፣ ማንኛውንም ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች በመላው ሀገሪቱ ቢመጣ የመመለስ አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ የሙፍቲህነት ማእረግ ሰጥቷቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ኃይማኖታዊ አለመግባባቶችንና እውቀት አጠር ግጭቶችን ፈትተዋል፣ አስታርቀዋል፡፡


በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን ከመሰረቱት ሰዎች መካከል አንዱም ነበሩ፡፡ በ1967 የምክር ቤቱ አባልና የዑለማ ሊቀመንበር በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በተከታታይ ለነበሩ በርካታ ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሠርተዋል፡፡ ከ10 ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ፣ በሙስሊሞች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይትና በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት የበኩላቸውን ከፍተኛ ጥረት አበርክተዋል፡፡

ግዮን፡- ባሳለፉት ረዥም ዘመን “ሳልሰራው በማለፉ ቆጭቶኛል” ብለው የሚጸጸቱበት ነገር ይኖራል?


ሐጂ ዑመር፡- በሕይወቴ ሁሉንም ሥራ ሞክሬያለሁ፡፡ ከብቶችን እያገድኩ ነው ያደግሁት፡፡ ከዚያም ወደ እርሻ፣ ቀጥሎም በንግድ ነው የተሰማራሁት፡፡ በጃንሆይ ዘመን 60ሺህ ብር የተገዛ መሬት ነበረኝ፣ ትልቅ ሃብትም ነበረኝ፡፡ በግ፣ ፍየል፣ በሬና ላሞችም በብዛት ነበሩኝ፡፡ ኪታብ እየቀራሁ ነው ይህንን ሁሉ እሠራ የነበረው፡፡ ግን ይሄን ሁሉ ሃብት ለወላጆቼ ተውኩላቸው፡፡ ማንኛውንም ሥራ አውቄ የተውኩት ቢሆን እንጂ፣ ይህንን ሳልሰራ ነው የቀረሁት ብዬ የምቆጭበት፣ የምጸጸትበት የሥራ ዘርፍ የለም፡፡


ባይሆን የምጸጸትበት ሌላ ነገር አለ፡፡ በ1950 አዲስ አበባ የመጣሁት ለመኖር አልነበረም፡፡ ደሴ ላይ በሐጂ ሳኒ ሐቢብ ቂርአት /ትምህርት/ ጀምሬ ስለነበር፤ እሱን ለመቀጠል እሳቸውን ፍለጋ ነበር የመጣሁት፡፡ ከእሳቸው ኪታብ ቀርቼ ተመልሼ ለመሄድ አቅጄ ነበር አመጣጤ፡፡ የእኔ ፍላጎት የነበረው እንደጥንቶቹ መሻኢኾች አገር ቤት ሆኜ እየቀራሁ/እየተማርኩ/፣ እየዘከርኩ/ፈጣሪዬን እያላቅሁ/ መኖር እንጂ፣ ከተማ የመቀመጥ ፍላጎት ፈጽሞ አልነበረኝም፡፡

በዚህ እጸጸታለሁ፡፡ የገጠር ሸኽ እሆናለሁ እንጂ አዲስ አበባ እቀመጣለሁ ብዬ አላውቅም፡፡ ሆኖም ከኔ በላይ ስለኔ የሚያውቀው ፈጣሪዬ አላህ የተሻለ ነው ያለውን አደረገ፡፡ እኔ በመቅራትም፣ በማቅራትም በዳእዋም፣በንግድም አልሰራሁትም ብዬ የምጸጸትበት ምንም ነገር የለም፡፡


ሌላው የሚያጸጽተኝ፡- ሀገሬ ሃብታም ነበርኩ፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ከመቅራት ውጪ ሌላ ሥራ አልሰራም ብዬ ስቀመጥ ደረሶቼ ተጨነቁ፡፡ መጀመርያ አላገባም፣ አልወልድም ብዬ ቆርጬ ነበር ከሃገሬ የወጣሁት፡፡ አንድ ጓደኛዬ ሚስት ፈልጎ “እንዲህ ያለች ሴት ለምኜልሃለሁ እና አግባ” አለኝ፡፡ “መርሃባ አንተ ትሆናለች ካልክ ይሁን” ብዬ አገባሁ፡፡ ካገባሁ በኋላ ኑሮ ከበደኝ፣እንግዳ በዛብኝ፣ ልጆችም ተወለዱ፡፡ ይሄኔ /በደርግ ዘመን/ መነገድ ጀመርኩ፡፡


በኬ የምትባል ከሰንዳፋ እልፍ ብሎ የምትገኝ ምሥር የሚዘራበት ቦታ አለ፡፡ አንድ ቦታ ስምንት ሺህ ካሬ ሜትር፣ ሌላ ቦታ ደግሞ 2700ካሬ ሜትር ቦታ ነበረኝ፡፡ ከ30 በላይ ሠራተኞችንም አስተዳድር ነበር፡፡ እኔ በመጅሊስ ጉዳይ ላይ ታች ስል የሚከካው ምሥር በስብሶ ተበላሸ፣ሠራተኛም በተንኩ፡፡


ግዮን፡- በጊዜው ልጆችዎ አልደረሱም ነበር?


ሐጂዑመር፡- ልጆቼ ገና ነበሩ፡፡ ቢደርሱም የአዲስ አበባ ልጅ ጥቅሙ ያነሰ፣ ልፋቱ የበዛ ሥራን አይፈልግም፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ መሥራትም አይፈልግም፡፡ እነዛ ቦታዎች ዛሬም አሉ፡፡ ኃላፊዎች ካርታውን ለማደስ በምሄድ ግዜ መሬቱን እንቀንስብሃለን፣አትቀንሱብኝም እያልኩ እየተከራከርኩ ነበር፡፡

የዛሬ 40 ዓመት ገደማ ነው መጅሊስ የገባሁት፡፡ መጅሊስ በመግባቴ ምክንያት ይህንን ሥራዬን አስተጓጉዬዋለሁ፡፡ ሁለቱንም በአንድ ላይ አብሮ ማስኬድ በሸሪዓ አይፈቀድም፡ ላለፉት 40 ዓመታት የነበረኝን ሃብት በሙሉ ትቼ ፤ መጅሊሱ ሳገለግል ነው የኖርኩት፡፡


ግዮን፡- የሸሪዓው ህግ የሚለውን ለአንባቢያን በግልጽ ያስቀምጡልን እስኪ?


ሐጂ ዑመር፡- የሸሪዓው ሕግ “አንድ በኃላፊነት የተቀመጠ ሰው ከራሱና ከቤተሰቡ ጉዳይ በፊት ኃላፊነት የተጣለበትን የሕዝብን ጉዳይ ማስቀደም አለበት፡” ነው የሚለው፡፡


የመሬቱን ካርታ እንኳ ያወጣሁት በመሃል ከመጅሊስ በወጣሁበት ጊዜ ነው፡፡ የሚቆጨኝ ቤተሰቤን፣ ልጆቼን መሠረት እንዲይዙ ያንን በራሴ ንብረት ማድረግ ስችል፣ በኃላፊነት ምክንያት ምንም ማድረግ አለመቻሌ ነው፡፡ በሃይማኖት አስታክኬ ጥቅም ፈልጌ አላውቅም፡፡


ለአዲስ አበባ ሙስሊም ካርታ የሌላቸው ከ360 መስጅዶች ተመዝግበው ለ87ቱ ካርታ እንዲኖራቸው ብዙ ሠርቻለሁ፡፡ 20 ዘመናዊ መስጅዶች እንደ ኑር ያሉት የተሠሩት እኔ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ኃላፊ በነበርኩበት ጊዜ ነው፡፡

ይህን ሁሉ ሳደርግ ልጆቼንና ራሴን ጥዬ ነው፡፡ ለምኖርበት ቤት ካርታ ያወጣሁትም ቅድም እንዳልኩህ ከመጅሊስ በወጣሁበት ጊዜ ነበር፡፡ ጀሞ አካባቢ ያለኝ መኖርያ ቤትም ካርታ ስጠይቅ “440 ካሬ ሜትር ካርታ እንሰጥሃለን፤ የቀረው መሬትህ ወደ መሬት ባንክ ይገባል” አሉኝ፡፡ አሁን ግን ካርታ ተሰጥቶኛል፡፡


ግዮን፡- ትርፍ የሚባል ጊዜ አልዎት ማለት ነው?


ሐጂ ዑመር፡- ምንም የተረፈ ጊዜ የለኝም፡፡ እቤቴ ከ50 እስከ 60 የሚሆኑ ደረሶች ዛሬም ድረስ ይቀራሉ/ በኔ ይማራሉ/ አሁን በረመዳኑ ቀንሰዋል፡፡ ለመጅሊስም፣ለቤተሰቤም ለደረሳዎቼም፣ በመስጅድ ሕዝብን ማስተማርም፣ በመንግሥት ስብሰባዎች መገኘትም ጊዜዬን የምሰጠው ስራዬ ነው፡፡


ግዮን፡-የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ጉዳይ መያዝ ከጀመሩ ወደ 45 የሚጠጉ ዓመታትን በተለያዩ ሓላፊነቶች ውስጥ ተሳትፈው አሳልፈዋል፡፡ ከነዚህ ጊዜያት ለእርስዎ አስቸጋሪና ፈታኝ የነበረው ወቅት የቱ ነበር?


ሐጂ ዑመር፡- መጥፎ ነገር አጋጥሞኛል የምለው ከ25 ዓመት በፊት በየሃገሩ እየዞርኩ ፈትዋ/ለሃይማኖታዊ ጥያቄ፣ ሃይማኖታዊ ምላሽ/ እሰጥ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ባህርዳር ላይ ዘጠኝ የአካባቢው ባለሥልጣናት ባሉበት ፈትዋ እየሰጠሁ፤ እዚያ ቦታ ላይ አንዱ ተነስቶ “እርስዎ የኛ ሙፍቲ አይደሉም” አለ፡፡

“የእኔ ሙፍቲነት አያጣላም፣ ከኔ የተሻለ ሲመጣ ለእሱ እለቃለሁ፡፡ አሁን የተሰባሰብነው ስለ ሰላምና ስለ አንድነት ለመነጋገር ነው” አልኩት፡፡ በዚህ ትንሽ ችግር አጋጥሞኝ ነበር፡፡


ሌላው የዛሬ 11 ዓመት ገደማ አንድነትን ለማምጣት ከዶክተር ጀይላን ጋር ቡድን መሥርተን ነበር፡፡ በወቅቱ ወሃብያና ሱፍያ በሚል ዑለሞችም/ልሂቃን/ ሕዝቡም ተከፋፍሎ ነበር፡፡ ይህ ልዩነት ለሃይማኖትም፣ ለመንግስትም፣ለሕዝብም አልጠቀመም፤እስቲ እኛ እንነጋገር፡፡ ያለው ልዩነት ምንድነው? ልዩነቱን እንዴት ማጥበብ እንችላለን? ብለን ለመመካከር ተሰባሰብን፡፡

ዑለሞቹ እኔን አንድ አድርገህ ምራን ብለው መጡ፡፡ በወቅቱ የሃገር አቀፉ ዑለማ ም/ቤት መሪ እኔ ነበርኩ፡፡
የወቅቱ የመጅሊስ ጠቅላይ ምክርቤት ሊቀመንበር እነኤልያስ ሬድዋን ነበሩ አማከርኳቸው፡፡ “በአራቱ መዝሃብ /አራቱ መዝሃብ የእስልምና የአስተሳሰብ አቅጣጫዎች ናቸው/ እንሠራለን ካሉ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ተለምኖም አይገኝ” አሉ፡፡ ጓደኞቼንም አማከርኩ፣”እነሱም ጥሩ ነው ባይሆን ተፈራረሙ” አሉ፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ለዘጠኝ ወራት እየተሳሳቅን፣ እየተግባባን ሰራን፡፡

ችግር አለባቸው የተባሉ ሃሳቦችን በመምዘዝ ደህና መሥመር እንዳስያዝን፤ የወሃብያና ሱፍያ አንድነት መምጣት ያበሳጫቸው የመንግሥት አካላት በኛ ሰዎች አማካይነት ጣልቃ ገብተው “ስምምነታችሁን አቁሙ” አሉን፡፡ እኔን ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ኃላፊነት አንስተው ወደ ጠቅላይ ምክርቤት አዘዋወሩኝ፡፡ በዚህ ስምምነት ብዙ ችግር አጋጥሞኛል፡፡ አንድነትን በማይወዱ አካሎች ችግር ደርሶብኛል፡፡ በዝርዝር ለማስቀመጥ ደስ አይልም፤ እገሌ እገሌ ማለትም አያስፈልግም፡፡


ከዚያ ወዲህ ገጠመኝ የምለው ችግር የለም፡፡ ኢትዮጵያን በሙሉ ፈትዋ በማድረግ /ሃይማኖታዊ ብይን በመስጠት/ ዞርያለሁ፡፡ በምሰጠው ብይን ሌላው ቀርቶ ሁለት ሰዎች እንኳ ተለያይተውበት አያውቁም፡፡ ለሃይማኖታዊ ጥያቄ፣ ሃይማኖታዊ ምላሽ ከምንጩ ነው የምሰጠው፡፡ ሰዎች በመልሱ ከተለያዩ እስኪረዱኝ አስማምቼ አስታርቄ ነው የምመለሰው፡፡ ባለፈው 11 ወራትም ከኮሚቴዎቹ ተስማምተን፣ ተግባብተን ነው የሠራነው፡፡

ግዮን፡-ባለፉት አሥራ አንድ ወራት በነበራችሁ የዘጠኝ ኮሚቴዎች ውጣ ውረድ አስቸጋሪ ጊዜ የሚባል አልነበረም?


ሐጂ ዑመር፡- ምንም ችግር አላጋጠመኝም፡፡ በመሠረቱ ሱፍያና ሰለፍያ መሠረቱ አንድ ነው፡፡ ሰለፊያ ማለት ሰለፎችን ተከታይ ማለት ነው፡፡ ሰለፎች የነብዩ ተከታዮችን ተግባር እግር ከእግር የሚከተሉ ባልደረቦቻቸው መጠርያ ነው፡፡ ሰለፍ የሚባሉት ከሂጅራ (የአረብኛ የዓመት አቆጣጠር ጅማሮ) ነብያችን ከመካ ወደ መዲና ከተሰደዱ ጊዜ ጀምሮ፣ እስከ 300ኛው ዓመት የነበሩ ሕዝቦች ናቸው፤ ሰለፍ የሚባሉት፡፡ ሱፍያውም ሰለፍይ ነው፡፡ ሰለፍይ ያልሆነ ሱፍያ የለም፡፡ እኔ በሱፍያ ነን ከሚሉም ሰለፍያ ነን ከሚሉም ወገኖች ችግር አላጋጠመኝም፡፡ ሁሉም የምላቸውን ይሰማሉ፡፡

የሚቸኩሉ ነበሩ፡፡ ተመለሱ በእርጋታ ሂዱ እያልኩ 11ወራትን ተዋውጠን አሳልፈናል፡፡ በድምጽ ብልጫ እንኳ ወስነን አናውቅም፡፡ መጨረሻው ላይ ምርጫው አካባቢ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንድ አንድ ችግር አይጠፋም፡፡ ይህም ቢሆን እኔ ላይ የደረሰ ችግር የለም፡፡


ባለፉት አርባ ዓመታት የመጅሊስ ቆይታዬ ከሕዝብ፣ከሥራ በኩል ያጋጠመኝ ችግር የለም፡፡ አሁን አሥመራ የተመደበው የኢህአዴግ ባለሥልጣን የነበረው ፤ከነዶክተር ጄላን ጋር ለአንድነት ሥንሰራ መጥቶ “ሐጂ ከላይ ከመጨረሻው ነው የመጣሁት ስሙኝ አለኝ፤ ‹ተመለስ ማለቱ ነው› እርስዎ በአነጋገርም፣ በአመራርም፣ በችሎታም ምንም የሚወጣሎት ነገር የለም፡፡ የእርስዎ ጥፋት ተብሎ የተቆጠረው አንድነት ብለው መነሳትዎ ነው” አለኝ፡፡

“አንድነት ለሙስሊሙ አይጠቅምም?፣ለሀገር አይጠቅምም?ለመንግሥት አይጠቅምም?”” ስለው፤ “ይጠቅማል፣ ግን እርስዎ ታዋቂ ሱፍያ በመሆንዎ ወሃብዮቹ በእርስዎ ተንጠልጥለው ሥልጣን ለመያዝ ይሞክራሉ፡፡” አለኝ፡፡


“እንደሱ ካሰባችሁ ሱፍያውን ማሰልጠን እንጂ አንድነታችንን ለምን ትቃወማላችሁ?” አልኳቸው፡፡ ይህን ሃሳብ ይዘው ሰንዳፋ ኢማሞችንና መሻኢኾችን እነሱ የሚፈልጉትን እንጋታችሁ አሉ፤ ሆኖም አልተሳካላቸውም፡፡


ግዮን፡-ባለፉት አሥራ አንድ ወራት የለፋችሁለት እና መጨረሻው ያማረው አንድነት ባይሳካ ኖሮ የኢትዮጵያ ሙስሊም እጣ ፈንታ ምን ላይ ይወድቅ ነበር?


ሐጂ ዑመር፡- እኔ የበኩሌን ለፍቻለሁ ሥሰራ የነበረው ያ እንዳይመጣ ነበር፡፡ ሌት ተቀን እሮጥ የነበረው ለኔ ጥቅም አልነበረም፡፡ ወደ መጨረሻ ላይ ችግር የፈጠሩ ሙስሊሙን ለማሰናከል ፈልገው አልተሳካላቸውም፡፡ ተንኮል እመንገድ ይቀራል፡፡እነዚህ ሰዎች ወደፊትም ይሳካላቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አሁንም ከተደራጀ በኋላ ችግር ለመፍጠርና ለመከፋፈል የሚፈልጉ አሉ፡፡ ከተሳካላቸው እናያለን፤ ግን ፈጽሞ አይሳካላቸውም ቢበላሽ ኖሮ ላልከው እኔ ዑመር የአቅሜን ስለለፋሁ ምንም አልጸጸትም ነበር፡፡


ግዮን፡- ሙስሊሙ በሀገር ደረጃ ሀገሩን ለማሳደግ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ? ቀጣዩን ክፍል ነገ ዕረቡ ጥቅምት 12-2018 ዓ.ም ጠብቁን

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...