
በአዲስ አበባ ሕዝብ የተሰበሰበበት ቦታ፣ መንገዶች እና የተለያዩ ተቋማት ውስጥ እንደፈለጉ ትንባሆን የሚያጨሱ ሰዎች እየቀነሱ ስለመምጣታቸው የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።
ይህም የሆነበት ትንባሆ እንዳይጨስ የሚከለክለው ሕግ ተግባራዊ በመደረጉ እንደሆነ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የምግብ ተቋማት ቁጥጥር ባለሙያ ጀማል ሙሳ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ከሚደረገው ክትትል በተጨማሪ የመግዛትና የመጠቀም ፍላጎትን ለመቀነስ የትንባሆ ምርቶች በፍሬ እንዳይሸጡ መወሰኑን በማንሳት፤ ይህንንና በአጠቃላይ ተቋማት ላይ የተከለከሉ ሕጎችን በማያከብሩ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ትንባሆን መጠቀም እንዳልተከለከለ ያስታወሱት የቁጥጥር ባለሙያው ‘ነገር ግን አንዱ በሚያጨሰው ምክንያት አካባቢው ከተበከለ ሳይፈልጉ የሚጠቁበትን መንገድ ለመቀነስ ሲባል’፤ ማጨስ የሚቻለው ሰዎች በማይበዙበትና በግል ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ እንደበፊቱ ሁሉም ቦታ በድፍረት የሚያጨስ ሰው እንደሌለ በመግለጽም፤ በዚህም መሰረት በትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ሆቴሎች፣ ሆስፒታሎችና መሰል ተቋማት ዙሪያ በቅርበት ማጨስ እንደማይቻል ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የቀነሰውን ደረጃ ሙሉ ለሙሉ በማጥፋት በከተማዋ ውስጥ የትኛውም ቦታ ላይ ትንባሆ እንዳይጨስ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዓለም ላይ በሲጋራ ማጨስ ምክንያት በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕይወት እንደሚያልፍ የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ባወጣው መረጃ ያስታወቀ ሲሆን፤ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የማያጨሱ ሰዎችም ለሚያጨሱ ሰዎች ባላቸው ቅርበት ምክንያት እንደሚሞቱ ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያም 17 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች መንስኤቸው የትንባሆ ምርትና የትንባሆ ጭስ በሆኑ የካንሰርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በየዓመቱ ሕይታቸው እንደሚያጡ ይገመታል፡፡
@አሐዱ