መንግሥትን እና ባለድርሻውን ያገናኘው የምክክር መድረክ

Date:

ባሳለፍነው ሐምሌ 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና ፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በጋራ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ በስካይ ላይት ሆቴል ተካሒዷል፡፡ በመድረኩ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ ቱሪዝም እና ኢ-ኮሜርስ ችግሮች የመነሻ ጥናት ቀርቦ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ከመንግሥት ተወካዮች ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡ 

መድረኩን በንግግር የከፈቱት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት/ም/ቤት ፕሬዚደንት፣ ምክር ቤታቸው ‹‹የግሉን ዘርፍ ጥቅም ለማስከበር የተመሰረተና ከ75 ዓመታት በላይ የዘለቀ አንጋፋ ተቋም›› መኾኑን ጠቅሰው ‹‹በአዋጅ ቁጥር 341/95 የተሰጠውን ምርትና አገልሎቶች እንዲተዋወቁና ገበያ እንዲያገኙ በማድረግ ንግድና ኢንቨስትመንትን የማስፋፋት ተግባራት፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን እንዲሁም የምርምርና አድቮኬሲ ሥራዎችን በመስራት በመንግስትና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል እንደ አገናኝ ድልድይ ሆኖ›› እንደሚሰራ አውስተዋል፡፡

ለንግዱ ማኅበረሰብ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት አካባቢን በመፍጠር ረገድ ምክር ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ‹‹የፖሊሲና አሰራር ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ለማሰባሰብና ችግሮችም ደረጃ በደረጃ እንዲቀረፉ ለማድረግ በተለይም ሀገራዊ በሆኑና ምክክር በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ዙሪያ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ምክክር መድረክ ማመቻቸት›› አንዱ መኾኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ‹‹ከመንግሥት፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከልማት አጋሮችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በአጋርነት›› እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በብሔራዊ ደረጃ የግሉን ዘርፍ በመወከል ከመንግስት ጋር እንደ ድልድይ ሆኖ በሚሰራው በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሚዘጋጀዉ አገር አቀፉ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ ‹‹በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ መካከል በሰከነ መንፈስ የመመካከር እና ለሚቀርቡት ችግሮች የጋራ መፍትሄ የማፈላለግን ባህል በእጅጉ ያሳደገ ነው›› ሲሉ ንግግራቸውን የቀጠሉት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፣ ‹‹ይህ አገር አቀፍ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ ባለፉት ሶስት ዓመታት በሃገሪቱ በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም በንግድ እና ኢንቨስትመንት በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመቅረፍም ባሻገር ቀድሞ የነበረውን የመወቃቀስ ባህል በማስወገድ በጥሩ የምክክር ባህል የቀየረ እና ለችግሮች የጋራ መፍትሄ የመፈለግ አሰራርን እያጎለበተ ያለ መድረክ ነው›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር አገር አቀፍ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ የሚሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ማለትም በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በቱሪዝምና በኢ ኮሜርስ ወይም ዲጂታል ማርኬቲንግ ዘርፎች ላይ የጥናት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን በማስታወስም፣ በነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያም ይህንን የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

ኢንጂነር መላኩ የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ለተመጣጠነ ምግብ እንዲሁም ለወጭ ንግድና ለመሳሰሉት የላቀ አበርክቶ እንዳለው፣ ኾኖም የጥሬ እቃ አቅርቦት፣ የማቀነባበርና አስተሸሸግ፣ የገበያ አማራጮች፣ የአገልግሎት መሰረተ ልማት አለመሟላትና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ግን ማነቆዎች እንደኾኑበት የጠቀሱም ሲኾን፣ ከኤሌክትሮኒክስ ግብይት አንጻር ደግሞ፣ ዘርፉ እያደገ ቢሆንም የኢንቨስትመንትና ፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር፣ ምቹ የክፍያ ስልቶችና አሰራሮች አለመኖር፣ የክፍያ ስርዓት ቅንጅት እጦት፣ የሸማቹ በቴክኖሎጂው ላይ እምነት ማጣት፣ ያላደገ ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ፣ ደረጃውን ያልጠበቀ የኢንተርኔት መሰረተ ልማትና የኢንተርኔትና ማህበራዊ ሚዲያ በየጊዜው መዘጋትና መቆራረጥ አሁንም ለዘርፉ እንቅፋቶች መሆናቸውን ጥናቶች እንደሚያሳዩ አንስተዋል፡፡

በቱሪዝም ዘርፉ ረገድ ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሸኝ ጫና፣ ከግብር ህግና የኦዲት አሰራሮች ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ መንገድን ጨምሮ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የመዳረሻ ስፍራዎች ከደረጃ በታች መሆንና በፌደራልና በክልል ደረጃ የሚካሄዱ ያልተናበቡ እንቅስቃሴዎች፣ የተሻለ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖርና የቱሪዝም መረጃ አያያዝ፣ ዘርፉ እንዳያድግ እንቅፋት መኾናቸውን በማንሳት፣ የተዘጋጀው መድረክ በሦስቱም ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ያለውን የሥራ አማራጭ አስመልክቶ ግልጽ ማብራሪያ እንደሚያስቀምጥና በመንግሥት በኩል የተዘጋጁ ማበረታቻዎችን በተመለከተም ግንዛቤ የሚፈጠርበትና በጋራ መስራት የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸትም እድል የሚፈጥር እንደሚሆን ያላቸውን ዕምነት ተናግረዋል፡፡

ከእርሳቸው በመቀጠል መድረኩን በንግግር የከፈቱት፣ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተሻለ በድሉ ሲኾኑ፣ በመልዕክታቸውም ‹‹ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ ችግሮች እልባት አግኝተው ለአፈጻጸማቸው ክትትል የሚደረግበት ስርዓት እንዲኖር እና በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን የልማት ግንኙነትና አጋርነት በይበልጥ ለማጎልበት እንዲቻል በማሰብ በቀድሞው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒሰቴር እና የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መካከል በተደረገ ስምምነት ሐምሌ 01 ቀን 2002 ዓ.ም. የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የጋራ ምክክር መድረክ እንዲመሰረት›› መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በሚኒሰቴር መሥሪያ ቤታቸው እና በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት መካከል የተቋቋመዉ ይህ የአገር አቀፍ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክም፣ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ‹‹በየግዜው የሚመረጡ የአገሪቱ ክቡራን ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ክቡራን ሚኒስትሮች፣ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት ጥቂት የማባሉ ብሔራዊ የቢዝነስ ኮንፈረንሶችን እና ከተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በርካታ የምክክር መድረኮች›› መካሔዳቸውን በመጥቀስም፣ በእነዚህ የምክክር መድረኮችም ከዚህ በፊት አያሌ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢውን ለማሻሻል የሚያግዙ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎ በአብዛኞቹ ላይ የጋራ መፍትሄ መደረሱንና የተደረሰባቸውን የውሳኔ ሀሳቦች በማስፈጸም ረገድም ከፍተኛ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ይህ የምክክር መድረክም በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ መካከል በቅን ልቡና የመመካከር እና ለችግሮች የጋራ መፍትሄ የማፈላለግን ባህል በእጅጉ ያጎለበተ እንደኾነና ከዚህ አንጻር መድረኩ በዴንማርክ አገር መጋቢት 2007 ዓ.ም. በተደረገው የዓለም ዓቀፍ የምክክር መድረኮች ውድድር በዘላቂ ዉጤታማነት (longstanding achievement) ዘርፍ ተሸላሚ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ፍትሓዊና የተሳለጠ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር፣ የወጭ ንግድ እድገት እንዲያስመዘግብ፣ ቀጠናዊ ትስስር እንዲጎለብትና የንግዱ ማህበረሰብ በተሻለ መልኩ የንግድ ስራውን እንዲሰራ፣ በዘርፎቹ ላይ የሚጡ አገልግሎቶችም ፈጣንና ምቹ እንዲሆኑ በተለይም የድጋፍና ክትትል አግባቦች የተሻሉ እንዲሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አበክሮ ይሰራል›› ያሉት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተሻለ በድሉ፣ ‹‹የተተገበሩ አሰራሮች በትግበራ ሂደታቸው የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች በተሻለ አሰራር እንዲስተካከሉ፣ የፖሊሲ ማዕቀፍ የሚያስፈልጋቸው ደግሞ ፖሊሲ እንዲቀረጽላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችንን ጨምሮ የመንግስት ተቋማት ብቻ ሳይሆን የግሉ ዘርፍም ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በጋራ መምከርና ውጤታማ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ የቱሪዝም መዳረሻ ሀገራት አንዷ መኾኗን በንግግራቸው ያወሱት ሚኒስትር ዲኤታው፣ ‹‹አሁን በትኩረት እየተሰራበት ካለው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት/AfCFTA ጋር በተያያዘ ቱሪዝም ዋነኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ በመሆኑ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ተዋናዮች ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር በጋራ የሚሰሩበትንና እንደሀገርም ተጠቃሚ የምንሆንበትን ስልት መቀየስ አስፈላጊ ነው›› ብለዋል፡፡ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚን አስመልክተውም፣ ‹‹ድህነትን ማስወገድ ዋነኛው የኢኮኖሚያችን ግብ እንደመሆኑ መጠን የግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍን ማልማት የግል አልሚውም ሆነ መንግስት ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ አንዱ ዘርፍ ነው›› በማለት ‹‹የወጭ ንግድን ማበረታታት፣ ጥራቱን የጠበቀ የጥሬ እቃ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸት፣ የምርት እሴትን መጨመር፣ የጥራት መመዘኛና ማረጋገጫ ስርዓቶችን ማመቻቸትና የመሳሰሉትን አሰራሮች መተግበር እንደሚገባ›› ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ያለውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የዲጂታል ኢኮኖሚ ወይም ኢ-ኮሜርስ ጉዳይን አስመልክተው ደግሞ ‹‹የዘርፉን በፍጥነት ማደግ ያክል ምቹና በቂ የአሠራር ሥርዓትና የመሠረተ ልማት አቅርቦት አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም›› ያሉ ሲኾን ‹‹ፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ የተመቻቸ የመክፈያ መንገዶች አለመኖር፣ የአከፋፈል ቅንጅታዊ አሰራር፣ ሸማቹ በቴክኖሎጂው አስተማማኝነት ላይ አለመተማመን፣ በቂና አስተማማኝ የህግ ማዕቀፍ፣ የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ ከፈቃድ አሰጣጥና ከሎጂስቲክስ ጋር የተያያዙ  ችግሮችም አሁንም የሚጠቀሱ›› መኾናቸውን በማንሳት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ የበኩሉን እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ከመክፈቻ ንግግሮቹ በኋላ በመድረኩ የተዘጋጁት ጥናቶች ቀርበው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጥያቄ እና አስተያየት መርኀ ግብር ተካሒዷል፡፡ በዕለቱ በጥናታዊ ጽሑፎች ያልተገለጹና መንግሥት ትኩረት አድርጎባቸው ሊያስተካክላቸው ይገባል ተብለው ከተጠቀሱ የተለያዩ ጉዳዮች መካከል፣ ከፋይናንስ አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡

በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚታዩ አንዳንድ አሠራሮች ማስተካከያ ካልተደረገባቸው፣ የዋጋ ንረቱን እንደሚያባብሱ ያመላከቱት የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ በተለይ ከብድር የወለድ ምጣኔና ከአገልግሎት ዋጋ ጋር በተያያዙ እየታዩ ያሉ አሠራሮች ለዋጋ ንረት መንስዔ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህ ጉዳይ አስተያየት ከሰጡ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት መካከል፣ አምራች ዘርፍን ወክለው የተገኙት የሸሙ ግሩፕ ቦርድ አባል አቶ ጀሚል ሽብሩ፣ የባንኮች ብድር የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ መሆን አሁን እየታየ ላለው የዋጋ ንረት አንዱ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በተለይ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፉን በተመለከተ በቀረበው ጽሑፍ ውስጥ፣ ይህ ጉዳይ ሊካተት ይገባል ያሉት እኚሁ ተሳታፊ፣ ያልተገደበ የወለድ ምጣኔ አሁን ያለውን የዋጋ ንረት እንዲባባስ እያደረገ ነው፡፡

ከብድር ወለድ ምጣኔ ባሻገር አንድ አምራችም ሆነ አስመጪ የሚፈልጉትን ጥሬ ዕቃ ለማስመጣትም ሆነ ሌሎች ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ሌተር ኦፍ ክሬዲት ሲከፍቱ፣ ለባንኮች የሚከፈለው የአገልግሎት ክፍያ መወደድም እንደ ችግር ተነስቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሌተር ኦፍ ክሬዲት ባንኮች የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ 12 በመቶ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጀማል፣ ይህ ምጣኔ ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር ከፍተኛ የሚባል በመሆኑ እንዲህ ያሉ የማምረቻ ወጪን የሚጨምሩ የአገልግሎት ዋጋዎች ገደብ ሊኖራቸው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ወለድ ምጣኔው ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ አምራቾችም ሆኑ አስመጪዎች ጥሬ ዕቃም ሆነ ሌሎች ሸቀጦችን ለማስመጣት ሌተር ኦፍ ክሬዲት ሲከፍቱ የሚጠየቁት የአገልግሎት ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ችግር እየፈጠረ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡ በነፃ ገበያ ሰበብ የአንዳንድ አገልግሎት ዋጋዎችን ዝም ብሎ መልቀቅ የዋጋ ንረቱን የሚያባብስ ስለመሆኑም ያስታወሱት አቶ ጀማል፣ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በነፃ ገበያ ስም ዝም መባል እንደሌለበትና መንግሥት ጉዳዩን እንዲመለከተው ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአብዛኛው ባንኮች የብድር የወለድ ምጣኔ እስከ 22 በመቶ መድረሱን ያመለከቱት አስተያየት ሰጪው፣ በዚህን ያህል የብድር የወለድ ምጣኔ በሚገኝ ፋይናንስ የሚካሄድ ቢዝነስ የማምረቻ ዋጋንም ሆነ የመሸጫ ዋጋን በመጨመር መጨረሻ ላይ ተጠቃሚው እንዲሸከም መደረጉም አግባባ እንዳልሆነ ሳይጥቅሱ አላለፉም፡፡

በመድረኩ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አጠቃላይ አገራዊ ችግር ሆኖ መቀጠሉን ያመለከቱት ተሳታፊዎች፣ ይህንን እጥረት ለመቅረፍ አፋጣኝ መፍትሔ ያሻልም ተብሏል፡፡ የመሬት አቅርቦት ችግርም የዘርፉ ሌላው ችግር ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ከታክስ ጉዳዮ ጋር በተያያዘም መንግሥት በተወሰኑ ታክስ ከፋዮች ላይ የሚያሳርፈውን ጫና ለማቃለል የታክስ ቤዙን ማስፋት ይኖርበታልም ተብሏል፡፡ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ተዋንያኖችን ወደ ታክስ ሥርዓቱ ማስገባት ተገቢ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ከንግዱ ኅብረተሰብ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀረቡ ተጨማሪ አስተያየቶች፣ በመንግሥት የሚወጡ ወጪዎችን ተናቦ አለመሥራትና ፈጣን ምላሽ አለመስጠት እንደ አንድ ችግር ተነስቷል፡፡ አስፈጻሚ አካላት ሕግን በማስከበር ሰበብ የሚወስዷቸው አንዳንድ ዕርምጃዎችም ቢዝነሶችን እየጎዳ፣ መንግሥትንም ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እያሳጣ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

በውይይቱ ዲጅታል ኢኮኖሚን በአገራችን ለማሳደግ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመረዳት በቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማምጣት የሚረዱ ሀሳቦችም የተነሱ ሲኾን በዘርፉ ላይ እንቅፋት ናቸው ከተባሉ ጉዳዮቾ መካከል የግንዛቤ፣ የክፍያና የግብይት ስርዓቱ የተጣመረ አለመሆን፣ በኢ ኮሜርስ አነስተኛ ኢንቨስትመንት መኖርና መሰል ችግሮች ተጠቃሽ ተደርገው ተጠቅሰዋል።

የኤሌክትሮኒክ ግብይት የተሳለጠ የንግድ መስተጋብር እንዲኖር፣ የንግድ ግልጽነትን ለማምጣትና ሙስናን ለመዋጋት እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለማስተዳደር ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ መንግስትና የግሉ ዘርፍ ሊሰሩበት እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን በኤሌክትሮኒክ ግብይት ልማትና ተጠቃሚነት ላይ የግሉ ዘርፍ የአንበሳውን ድርሻ እንዲወስድ መንግሥት አመቺ ፖሊሲ፣መሰረተ ልማት፣ ፋይናንስ ማቅረብና ግብይቱ ቀዳሚ ተጠቃሚ በመሆን በዘርፉ የተማሩ የንግድ ተቋማትን በመደገፍ የኤሌክትሮኒስ ግብይት ስትራቴጂ በመቅረጽ የላቀ ሚናውን መወጣት እደሚገባው በመድረኩ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እንዳመለከቱት፣ በሁለቱ ቀናት የውይይት መድረኮች በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኢኮሜርስና በቱሪዝም ዘርፎች ላይ ያሉ ችግሮችን የሚጠቁሙ ጥናቶች ቀርበው ከመንግሥት አካል ምላሽ የሚሰጥባቸው እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ መድረኩ አሉ የሚባሉ ችግሮችንም ለመቅረፍ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡ በዚህ ደግሞ የተጀመረው የግሉና የመንግሥት የምክክር መድረክ በርካታ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የገለጹት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተሻለ በልሁ፣ እንዲህ ያሉ መድረኮች የሚበረታቱ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከባድ ሙስና የተከሰሱትን 4 ተከሳሾችን፤ ፖሊስ ፍርድ ቤት ማቅረብ ሳይችል ቀረ

በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው በፖሊስ የ'ይፈለጋሉ" ማስታወቂያ የወጣባቸው...

ስለመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ውጥረት እስካሁን የታወቁ ጉዳዮች

🔸 ትላንት ምሽት ከኢራን ግዛት የተተኮሰ የሮኬት ጥቃት በሰሜናዊ...

የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕጉ በጋዜጣ እስኪታተም ረቂቅ ሰነዶችን ከመጠቀም እንዲቆጠብ የፍትሕ ሚኒስቴር አሳሰበ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር አዲሱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ...

ፔንታጎን የእስራኤል ስለላ እንደሚያሳስበው ተገለጸ

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ፔንታጎን እስራኤል ከፍተኛ ልዑኮችን ጨምሮ የአሜሪካ...