‹‹ሜሪ ስቶፕስ ኢትዮጵያ›› እና ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን›› የወጣቶች ጾታዊ እና ሥነ-ተዋልዶ የጤና አገልግሎቶችን በማጠናከር እና በመላ ሀገሪቱ በወጣቶች ሁለንተና ላይ የሚካሔዱ የልማት ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የአምስት ዓመት የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ አርብ ታህሳስ 3- 2018 ዓ.ም ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሁሉንም ወጣት የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማብቃት እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸውም ዐቅማቸውን ለማጎልበት ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን የሁለቱም ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ተገኝተው የተፈራረሙ ሲሆን፣ በሜሪ ስቶፕስ ኢትዮጵያ በኩል ዶ/ር አበበ ሽብሩ፣ በዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን በኩል ደግሞ የፋውንዴሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዜናዬነህ ግርማ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ፣ ወጣቶችን በመረጃ ከማንቃትና ማሳወቅ አንስቶ፣ ተገቢውን እገዛ በማድረግ በሕብረተሰቡ ውስጥ ንቁ ለውጥ ፈጣሪ ይኾኑ ዘንድ በጋራ ቁርጠኝነት ለመሥራት ትልቅ ምዕራፍ እንደሚኾን ተገልጽዋል፡፡
በፊርማው ሥነ-ሥርዓት ላይ ዶ/ር አበበ ሽብሩ የሜሪ ስቶፕስ ኢትዮጵያን የቀደሙ ማኅበራዊ ተሳትፎዎች በአርአያነት አጉልተው የጠቀሱ ሲሆን፣ ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ በነበሩት እንደ አየር ንብረት ለውጥ፣ ወረርሽኞች እና በለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ ምክንያት የሚያጋጥሙ ተፅእኖን በምን መልኩ ተቋቁሞ መቀጠል እንደቻለ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ሜሪ ስቶፕስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሌሎችም ዓለም አቀፍ ቀውሶች ወቅት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች እንዴት በተሳካ ሁኔታ መሻገር እንደቻለ በማስታወስ፣ የወጣቶችን የጾታና የሥነ ተዋልዶ አገልግሎቶችን በማሳደግ ረገድ ከሁኔታዎች ጋር የሚስማሙ አካሔዶችን በመከተል ረገድ ያለውን ልምድ አስረድተዋል፡፡
የዩዝ ኤንድ ካልቸራል ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዜናዬነህ ግርማ በበኩላቸው፣ ፋውንዴሽናቸው በወጣቶች የጤናም ኾነ የባሕል ልማት ረገድ ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት በመግለጽ፣ ከሜሪ ስቶፕስ ኢትዮጵያ ጋር የፈጠረው አጋርነት ቀጣይነት ያለው የወጣቶችን የጾታና ሥነ ተዋልዶ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና የለውጥ ተፅእኖ ለመፍጠር የሚኖረው ጠቀሜታ ትልቅ መኾኑን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት፣ ወጣቶች በጾታ እና ሥነ ተዋልዶ ረገድ የሚያጋጥሟቸውን መሰናክሎች በጋራ ለመፍታት፣ የተቀናጀ ተግባር ከማድረግ በዘለለም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እና የማኅበረሰብ ተቋማትን ጨምሮ ተጨማሪ ባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ እቅድ የተያዘበት መኾኑ ገልጽዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በጋራ የመሥራታቸው ዓላማም ወጣቶች ትክክለኛ መረጃን፣ ጥራት ያለው አገልግሎትን እንዲሁም የአመራርነት እና የተሳትፎ እድሎችን የሚያገኙበት አስቻይ ሁኔታ መፍጠር መኾኑ ተወስቷል፡፡
