ሜታ ‘ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በቀረበባቸው ክስ 18 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ

Date:

ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ሜታ በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ምክንያት በአሜሪካ ግዛቶች የቀረበበትን ከሕፃናት ደኅንነት ጋር የተያያዘ ክስ ለመፍታት ስምምነት ላይ ደረሰ።

በስምምነቱ መሠረት የቴክኖሎጂ ኩባንያው ለአሜሪካ 48 ስቴቶች፣ ለኮሎምቢያ ዲስትሪክት እና ለሦስት የአሜሪካ ግዛቶች እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንደሚከፍል አስታውቋል።

ክፍያው የሚፈጸመው በ10 ዓመት ውስጥ እንደሚሆንም ገልጿል።

በተጨማሪም ኩባንያው ፌስቡክ እና ኢንስታግራም መተግበሪያዎቹን የሚጠቀሙ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ የሚቆዩበት ዕለታዊ ገደብ ማበጀት እና በምሽት ሰዓት እንዳይጠቀሙ ማገድን ጨምሮ የተለያዩ አሠራሮችን ለመተግበር ይገደዳል።

ሜታ ይህንን ስምምነት ቢፈጽምም፣ የሠራው ስህተት እንደሌለ በመግለጽ አስተባብሏል።

ኩባንያው ክስ የተመሠረተበት በአሜሪካ በርካታ የፌዴራል እና የግዛቶችን የሕፃናት የግል መረጃ ጥበቃ ሕጎችን ጥሷል በሚል ነበር።

ክሱን የከፈቱት የአሜሪካ ግዛቶች ሜታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹን “ወጣቶች እና ታዳጊዎችን ለመሳብ እና በመጨረሻም ለማጥመድ” ተጠቅሟል በማለት ወንጅለዋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ “በአሜሪካ ወጣቶች አእምሯዊ እና አካላዊ ሁኔታ” ላይ ያደረሱትን ጉዳት ችላ እንዳለ በመጥቀስም ከስሰዋል።

ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ፣ የኮሎምቢያ ዲስትሪክት ዐቃቤ ሕግ ብሪያን ሽዋልብ “ታላቅ የሕብረተሰብ ጤና ድል” ሲሉ ጠርተውታል።

“ሜታ ለመተግበር የሚገደዳቸው የደኅንነት ገጽታዎች ወጣቶች ኢንስታግራም እና ፌስቡክን የሚጠቀሙበትን መንገድ ላይ ከመሠረቱ እና በአፋጣኝ ይለውጠዋል” ብለዋል።

በስምምነቱ መሠረት ሜታ መተግበሪያዎቹ ላይ ማስተዋወቅ ካለበት አዲስ አሠራሮች አንዱ ሕጻናት በትምህርት ሰዓት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹን እንዳይጠቀሙ መገደብ ነው።

ጠንካራ የወላጅ ቁጥጥር ሥርዓትን መተግበር እንዲሁም ከ18 ዓመት በታች በሆኑ ተጠቃሚዎች ላይ ጥብቅ የዕድሜ ማረጋገጫ ዘዴ መከተልም ከአዲሶቹ አሠራሮች መካከል ይሆናሉ።

ሜታ ባወጣው መግለጫ ቲክቶክ እና ዩቲዩብም ታዳጊ በሆኑ ተጠቃሚዎቻቸው ላይ ይህንን ዓይነት አሠራሮች መተግበር አለባቸው ብሏል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ኢራን የአሜሪካን የጦር መርከቦች ዒላማ የማድረግ አቅም እንዳላት ገለጸች

ኢራን የአሜሪካን የጦር መርከቦች ዒላማ የማድረግ አቅም እንዳላት የአገሪቱ...

ከትግራይ ዩኒቨርሲቲ ታጣቂዎች ካልወጡ ተማሪ አንመድብም

ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የሚገኙ መቐለ፣ አክሱም፣ አዲግራት እና...

ኢራን አሜሪካ የጣለችባት ዕገዳ የበለጠ የሚጎዳው ዋሽንግተንን ነው አለች

አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችው የኢኮኖሚ እና የባሕር እንቅስቃሴ እገዳ...

ግብጻዊቷ የቴሌቪዥን አዘጋጅ በዕፅ ዝውውር ወንጀል የሞት ፍርድ ተወሰነባት

የካይሮ የወንጀል ችሎት፤ ዕውቋን የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ሳራ ካሊፋን...