የጅምላ እሥር ያልበገረው ተጋድሎ
- ቀራንዮ ዳግም የተገለጠበት ስንክሳር
የኢትዮጵያ ቅድመ ጠላት ጣሊያን አንግባ ከመጣችው ኢትዮጵያን የማፍረስ ሥውር ሴራ አንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ማፍረስ ነበር፡፡ ጣሊያን በወቅቱ ምንም እንኳን ይህን ዓላማዋን ማሳካት ባትችልም ማፍረስ የሚቻልበትን ስልትና ሴራ ግን ቀይሳ ነበር ለቃ የወጣችው፡፡ በዚህም የጣሊያን የመንፈስ ተጋሪ የኾኑ ባንዳ የኢትዮጵያ ልጆች ያለፈውን ግማሽ ክፍለዘመን ይህን ሴራ እውን ለማድረግ ሲታትሩ ቆይተዋል፡፡ ከደርግ እስከ ብልጽግና ተከታትለው የመጡት መንግሥትታትም ይህችን አንዲትና ኩሏዊት የኾነች ቤተክርስቲያን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ የየራሳቸውን ጡብ እያስቀመጡ መጥተዋል፡፡ አሁን ላይም ይህን ተልዕኮ ከዳር ለማድረስ ቆርጦ የተነሳ ይመስላል፡፡ ለመኾኑ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ምን ኾነ? የሚለውን ግዮን መጽሔት ኹነቶቹን እንደሚከተለው አጠር አጠር አድርጋ ልታስቃኛችሁ ትሞክራለች፡፡
በኖርዌይ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ካህናትና ምእመናን በቅርቡ የተሞከረውን የመፈንቅለ ሲኖዶስ ሙከራ የሚያወግዝና የኢትዮጵያ መንግሥት ሲኖዶሱን ለመክፈል መከራ ላደረጉ አካላት እየሰጠ ያለውን እውቅና የሚቃወም ሰላማዊ ስልፍ አድርገዋል። ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብሎም ከሀገረ ስብከታቸው በተሰጠው መንፈሳዊ መመሪያ መሠረት ወደ አደባባይ የወጡት በመላዋ ኖርዌይ የሚኖሩ ካህናትና ምእመናን በኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ደጃፍ እና በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዘዋወር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቀኖናዋን ለማስከበር የሄደችበትን ርቀት እና መንግሥት ሰአርያነ ቀኖና የሆኑ አካላትን በመደገፍ ቤተክርስቲያናችንን አየጎዳ እንደሆነ ለኖርዌይ መንግሥት እና ለዓለም ሕዝብ አሳይተዋል።
በሌላ በኩል የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና የከተማው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጎን መሆናቸውን አሳወቁ። የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በወቅታዊ ጉዳዮችና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን የሚደግፍ ምክክር አካሒደዋል። የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በወቅታዊ ጉዳዮችና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት ባደረጉት ምክክር በከተማው የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮችና የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሃይማኖት ተወካዮች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰው ክስተት ማዘናቸውን ገልጸዋል። ቤተ ክርስቲያን ወደ ቀድሞው ሰላም እስክትመለስ ድረስ ሁሉም ቤተ እምነቶችና ምእመናን በጾምና በጸሎት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጎን እንደሚሆኑ አሳውቀዋል። ከተማ አስተዳደሩም ቅዱስ ሲኖዶሱ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት የሚጠይቁት ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ በማንኛውም ነገር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጎን መሆኑን አሳውቋል።
የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአጋርነት ደብዳቤ በፖፑ የክርስቲያን አንድነት ፕሬዝደንት በኩል ላከች፡፡ ብፁዕ ካርዲናል ኩርት ኮህ የፖፕ ፍራንሲስ የክርስቲያኖች አንድነት ፕሬዝዳንት (President Pontifical Council for Prompting Christian Unity) እንደገለጹት “በተፈጠረው ችግር እና ሁኔታ ጥልቅ ሐዘን የተሰማን ሲሆን ለቅዱስ ሲኖዶስ ያለንን አጋርነት በመግለጽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ የሚደረግ ጥረትን በሙሉ እንደግፋለን” ብለዋል፡፡ በመልእክታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንጦስ በላከው የመጀመሪያ መልእክት “አንድም ብልት ቢሰቃይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።” 1ኛ ቆሮንጦስ 12፥26 ያለውን ጠቅሰው ሕመሟ ሕመማችን ክብሯ ክብራችን ነው ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል። በመጨረሻም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ እና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እናት በምልጃዋ እጅግ የተከበረች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷና ደህንነቷ እንዲጠበቅ ታድርግልን ብለዋል።
በሌላ በኩል የቤተክርስቲያኒቷ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ዋና ሰብሳቢ እና ዋና ፀሐፊዋ መታሰራቸው ተገለጸ፡፡ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ፌቨን ዘሪሁን እንዲሁም ዋና ፀሐፊዋ ወጣት ብሩክታዊት ናቸው የታሰሩት። በተመሳሳይም እንዲሁ የማኅበረ ቅዱሳን ደቡብ ማዕከላት ማስተባበሪያ አስተባባሪ የሆኑት ዲ/ን መልካሙ ጸጋዬ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት ታፍነው መወሰዳቸውን የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል አስታውቋል። በተጨማሪም፤ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን እና ከደብረ ዕንቍ ልደታ ለማርያም አካባቢ ተይዘው የታሠሩት ዲ/ን ታምራት ጥጋቡ፣ ዘካርያስ ዓለማየሁ፣ ጸጋ ደምሴ እና እንዳለ ብርሃኑ የተባሉ ወጣቶች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ወጣቶቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ወደ አዋሽ 7 ተወስደዋል።
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በወቅታዊ ጉዳይ በተሰጠ መግለጫ አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁት ጳጳሳት በአንዳንድ ቦታዎች በኃላፊዎች ድጋፍ ጭምር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን መያዛቸውን፣ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ለመያዝ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ እርምጃውን ለመቃወም የወጡ ሰዎችን ለመበተን በመንግሥት ጸጥታ አባላት በተወሰደ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ እና ከጸጥታ አባሎቹ ጋር ሲተባበሩ በነበሩ ሰዎች ቢያንስ ስምንት ሰዎች በጥይትና በድብደባ መገደላቻውን ኮሚሽኑ ያረጋገጠ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ገና በትክክል ያልታወቀ ሰዎች ለተለያየ ዓይነትና መጠን የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም በርካታ ሰዎች ለተለያየ ጊዜ መጠን መታሰራቸውን፣ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኃላፊዎች በሻሸመኔ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 13 መሆኑን ለኮሚሽኑ የገለጹ በመሆኑ የማጣራት ሂደቱ እንደቀጠለ ነው)፡፡ በተለያዩ ቦታዎች አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁትን ጳጳሳት በተቃወሙ ሰዎችና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ ከቤተ ክርስቲያናት ማባረር፣ የመንቀሳቀስ መብትን በኃይል መገደብ እና ከሕግ ውጭ እስራት እንደተፈጸመ፤ እንዲሁም ሲኖዶሱ ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚታሰበውን የጾም ወቅት አስመልክቶ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ በተለያዩ ቦታዎች እስር፣ ወከባ፣ ከሥራ ቦታና አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ማግለል እንደተፈጸመ ገልጽዋል፡፡
በሌላ በኩል የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመክፈል የተደረገውን ሙከራ በማውገዝ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ። የሞስኮ እና የመላው ሩሲያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ መንበር ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የድጋፍ ደብዳቤ ልከዋል። ቅዱስነታቸው በኢትዮጵያ እየተደረገ የሚገኘውን መፈንቅለ ሲኖዶስና እርሱን ተከትሎ በኦርቶዶክሳዊያን ላይ የተፈጸመውን መንግሥታዊ ግድያ እና እስር በተመለከተ በላኩት መልእክት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በክርስቶስ የተወደደ ወንድምህ በወዳጃችን – በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰው መከራ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስም የተሰማኝን ኃዘን እገልጻለሁ ብለዋል። የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል “በነዚህ አስጨናቂ ሁኔታዎች ውስጥ ለቤተክርስቲያናቸው ታማኝ በመሆን በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” (ኤፌ 4፡3) ባለው ሐዋርያዊ ቃል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በጽናት እያሳለፉት ያለውን የመከራ ዜና ስሰማ ልቤ ያዝናል ። በመከራ የሚሰቃዩ ወገኖቻችን የሚያሳዩት የመንፈስ ጥንካሬ የክርስትና እምነት በኢትዮጵያ ምድር ህያው እና ጠንካራ ለመሆኑ ማረጋገጫ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። በተመሳሳይም በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአክሱም ሊቀ ጳጳስና በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲና ሶማሊያ የግሪክ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊ አባ ዳንኤል በቤተ ክርስቲያናቸው ስም ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረውን ውይይት አስመልክቶ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በሰጡት መግለጫ፣ ብፁዕነታቸው እንደገለጹት “በአስቀመጥነው ቅድመ ሁኔታ መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠርተን ጥያቄያችንን አቅርበናል፡፡ ጥያቄያችንም አንድ ነው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይከበር፤ በሀገሪቱ ያለው ኦርቶዶክሳውያን መብት ይጠበቅ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ንብረት በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ንብረቷ ይጠበቅ፤ እነዚህ ካልሆኑ ወደ ሰላማዊ ሰልፍ እንሄዳለን ማለታችን ይታወሳል፡፡ በዚህም በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት በፍፁም መንፈሳዊ መሪነትና ክብር ሄደናል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረን ቆይታ በደንብ ተወያይተንበት ለጥያቄዎቻችንም መልስ ተሰጥቶናል” ብለዋል፡፡
በሌላ መረጃ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕገወጥ ሹመት የሰጡት በቀድሞ ስማቸው አባ ኤውስጣቴዎስ; አባ ዜና ማርቆስ አባ ሳዊሮስ እና እነርሱ በሕገ ወጥ መልኩ ሾመናችኋል ብለው ከሕገ ቤተክርስቲያን ውጪ አስኬማ ያቀዳጇቸው 25 ግለሰቦች እንዲሁም አቶ ኃይለሚካኤል ታደሰ የተባሉ ግለሰብ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 156 መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግቢ እንዳይገኙ በጊዜያዊነት አግዷቸዋል። ይህንን እግድ የተላለፈ ማንኛውም አካል የወንጀል ተጠያቂነት ይኖርበታል። በሐገሪቱ የሚገኙ የሕግ አስፈጻሚ አካላት እግዱን እንዲያስፈጽሙ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ቤተክርስቲያኗ በቀጣይ በሰብአዊ መብት፣ በአስተዳደር፣ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ለደረሰው ኪሣራ ተጠያቂዎችን በመለየት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በሕግ ትጠይቃለች ተብሏል።
ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም ከወጣው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ በኋላ አዲስ መመሪያ ወጥቷል። መመሪያው በየአጥቢያው ለጥበቃ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች በአስቸኳይ እንዲወረሱ የሚል ነው። በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ፖሊስ አዛዦች የአጥቢያ አስተዳዳሪዎችን እየደወሉ ባስቸኳይ አስረክቡ ማለት ጀምረዋል። በአስኮ ገብርኤል እና በአንዳንድ ቦታዎች ፖሊስ መሣሪያውን ሊረከብ ሲል ሕዝቡ ደርሶ አስቀርቶታል። የጥበቃ መሣሪያ ፈቃድ ወጥቶለት ቤተ ክርስቲያኗ ለጥበቃ አገልግሎት የምትጠቀምበት ሲሆን ከረጅም ዓመታት በፊት ጀምሮ ጥቅም ላይ ያለ ነው። በሌላ በኩል ቅዱስ ሲኖዶስ መንግሥት አሁን ላይ እስር፤ ወከባ፤ እንግልት እየተፈጸመባቸው ያሉት ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የሀገረ ስብከት ሠራተኞች፤ አገልጋይ ካህናት እና በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች ችግሩ በአስቸኳይ እንዲቆምና የታሠሩትም እንዲፈቱ፤ አገልግሎታቸውን በሰላምና በነጻነት መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል ቢልም በኦሮሚያና በአዲስ አበባ አገልጋዮችን ሰባኪያንን የሰንበት ትምሕርት ቤት እና የማኅበራት አባላትን የማሠሩ ሒደት ቀጥሏል። ሕገ ወጡን ሹመት አልቀበልም በማለቷ ምክንያት በኦሮሚያ የጸጥታ ኃይሎች በተደረገው ግድያ ውድ ልጆቿን የገበረችው የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት መናገሻዋ ሻሸመኔ ተጨማሪ ብዙ ልጆች ታሥረውባታል፡፡ እሥሩም ከወጣቶች ወደ ከተማዋ ባለሀብቶችና ሽማግሌዎች ተሸጋግሯል። በዚህም በከተማዋ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ባለ ሀብቶች፣ የከተማዋ የተከበሩ ሽማግሌዎችና እጅግ ብዙ ወጣቶች ታሥረዋል። በተጨማሪም በምእመናን ላይ የደረሰውን ሞትና አካል ጉዳት ለመሸፋፈንና ተጠያቂ እንዳይኖር ለማድረግ የመንግሥት አካላት የሚመለከታቸውን ሰዎች ሁሉ ምንም እንዳይናገሩ ለማስገደድ እየሞከሩ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል ምእመናን ወደ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን /ግቢ ገብርኤል/ እንዳይገቡ ተከልክለዋል። የጸጥታና የደኅንነት ግብረ ኃይል ሰንበትን ከንጋቱ 11:00 እስከ ረፋድ 4:00 ሰዓት ድረስ የተለያዩ የከተማዋ መንገዶች ዝግ እንደሚሆኑ ተናግሮ ነበር። የአጥቢያው ምእመናን ይህንን በማክበር ከሌሊት 10:00 ጀምሮ ወደ ደብሩ ቢሔዱም ከላይ የመጣ ትእዛዝ ነው በማለት ፖሊሶች እንዳይገቡ ከልክለዋቸዋል። የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት ባጋራው መረጃም ምእመናን በሌሉበት ሥርዓተ ቅዳሴ ተከናውኗል፡፡
በሌላ በኩል በሕገ ወጡ ቡድን የጵጵስና ልብስ አልብሶ ሾሜዎታለሁ ካላቸው መነኮሳት መካከል ከኢየሩሳሌም የመጡት “አባ” ንዋየሥላሴ አክሊሉ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ዕድል በመጠቀም በመንበረ ፓትርያርክ በመገኘት አስኬማቸውንና አርዌ በትሩን ለሕጋዊዋ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በማስረከብ ቤተክርስቲያንንና ምእመናንን ይቅርታ ጠይቀው የነበረ ቢኾንም በማግሥቱ ደግሞ ወደሕገወጡ ቡድን በመኮብለል መልሰው ተገድጄ እንጂ ይቅርታ አልጠየቅሁም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተፈጠረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን በቤተ ክርስቲያኗ በመምህርነት የሚያገለግሉ ሰባኬ ወንጌላውያንን ጨምሮ የማኅበራት ተወካዮችን እንዲሁም የችግሩን እውነታ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚናገሩ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ታስረዋል። ለአብነትም መምህር ዐቢይ መኮንን፣ መምህር ምሕረተአብ አሰፋ፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪ ፌቨን ዘሪሁን እና ዋና ጸሐፊ ብሩክታዊት እንዲሁም የማንቂያ ደውል አገልጋዮች ዲ/ን አማኑኤል አያሌው እንዲሁም ዲ/ን ኪሩቤል አሰፋ ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሰ/ት/ቤት ሰብሳቢዎችና የመንፈሳዊ ወጣት ማኅበራት ኃላፊዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ተለያዩ አካባቢዎች ኦርቶዶክሳውያን ያለምንም ወንጀል ታስረዋል።
በሌላ መረጃ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት (EOTC TV) የኦሮሚኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ ዲ/ን ዮሴፍ ከተማ በጸጥታ ኃይሎች ታፍኖ ተወስዷል፡፡
በሌላ ዜና ፖሊስ ከሰሞኑ የያዛቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምእመናን በተመለከተ “በሽብር ተግባር እና ህገመንግስቱን በሃይል ለመናድ ኢመደበኛ አደረጃጀት ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ ይዣቸዋለሁ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ይሰጠኝ” በማለት ለችሎቱ ጥያቄ አቀረበ። በዚህም ከሰሞኑ የተደራጀው የቤተክርስቲያኒቷ የጠበቆች ቡድን 10 ጠበቆች፤ በአንድ ችሎት ብቻ ቆመው መሟገታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ረዥም ሰዓት የወሰደ ክርክር ለችሎቱ ቀርበዋል። በዚህም መሠረት ሰባት ተጠርጣሪዎች በዋስ የተለቀቁ ሲሆን፤ በመጀመሪያው መዝገብ መ/ር ምህረተአብ አሰፋ እና ኪሩቤል አሰፋ ላይ የ8 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል። በተመሳሳይ ክስ (የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ) በሌላ መዝገብ ፌቨን ዘሪሁን እና ብሩክታዊት ነብዩ እንዲሁም ፋሲል አግደው ላይ በአጠቃላይ 5 ሰዎች ላይ የ8 ቀን ጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ቀጣይ ቀጠሮ ለየካቲት 14/2015 ተቀጠረ።
በሌላ መረጃ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የሃይማኖት ጉዳይ የቤተ እምነቱ እና የአባቶች ጉዳይ ነው። ዘርና ሃይማኖትን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል ቀይ መስመርን መተላለፍ ነው ሲሉ ገለጹ። የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በማኅራዊ እንዳስነበበው የትሥሥር ገጹ እንዳሰፈረው ፕሬዚዳንቷ እምነቶች ለእኛ ለአማኞች የመጨረሻ ምሽጎቻችን ናቸው። ለጠፋው ሕይወት ሐዘኔን እገልጻለሁ ብለዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ባሏት ዘመናትን ያስቆጠሩ ባህሎቿ ሃይማኖቶቿና ታሪኳ እንኮራለን ያሉ ሲሆን ልንጠብቃቸውና ከጥቃት ልንከላከላቸው ይገባል ያሉ ሲኾን፣ ክብርት ፕሬዚዳንቷ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ጋር እሑድ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. የተወያዩ ሲሆን ስለነበራቸው ውይይት አመስግነዋል፡፡
በሌላ መረጃ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጭሮ ማዕከል አገልጋይና በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ ጭሮ ካምፓስ መምህር የሆነው ዶ/ር እንደሻው ዘርፉ ታሰረ። በተመሳሳይ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና የሚገኝበት ደብረ ጽዮን ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በሕገ ወጡ ቡድን መያዙን ተከትሎ ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሔዱ አለመሆናቸው ተገለጸ። በተጨማሪም የአድባራት አገልጋዮች ሕገ ወጡ ቡድን እርሱን ደግፈው እንዲያገለግሉ ስለሚያስገድዳቸው ከአካባቢያቸው እየሸሹ መሆናቸውም ነው የተነገረው።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድነትን የሚሸርሽር ድርጊት ነው የተባለው የሕገ ወጥ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት፣ ወይም ራሱን “የኦሮሚያ እና ብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” ብሎ የተነሳው አካል ያስነሳው ውዝግብ መቀጠሉን እና ጉዳዩ እየተካረረ መምጣቱን ተከትሎ፣ መንግሥት ከኹለቱም አካላት ጋር ውይይት አድርጎ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ ተሰማ፡፡ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ የካቲት 3/2015 ከመንግሥት ጋር ባደረገው ውይይት፣ በእስር ላይ ያሉ ካህናትና ምዕመናንም በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ማስታወሱ የሚታወቅ ሲሆን፣ ካህናትም አገልግሎታቸውን በነጻነት መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ መደረሱ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ከሰምምነቱ በፊት የታሰሩት ሰዎች መፈታት ሲጠበቅ፣ እስርና ወከባ በአስቸኳይ እንዲቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል ከተባለ በኋላም ታዋቂ የቤተክርስቲያን መምህራን ታስረዋል፡፡ ይህ ሁኔታ መንግሥት የቤተክርስቲያኗን ጥያቄ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የገባውን ቃል እንደመሻር የሚያዩት አካላት ተፈጥረዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት፣ መንግሥት የቤተክርስቲያኗን አንድነትና ቀኖና እንደሚያከብርና በቤተክርስቲያኗ ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን እንዲያስቆም ሙሉ በሙሉ ስምምነት ተደርሷል ተብሏል፡፡ ራሱን “የኦሮሚያ እና ብሔር ብሔረሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ” ብሎ የጠራው አካል፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ የተቀየረ አቋም እንደሌለው አስታውቋል፡፡ በየትኛውም መንገድ ለዕርቅ ዝግጁ ብሆንም፣ በያዝኳቸው አገረ ስብከቶችና በሾምኳቸው ኤጲስ ቆጶሳት አልደራደርም ብሏል፡፡ በአንጻሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያየው የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከመንግሥት ጋር በተደረገው ውይይት የቤተክርስቲያኗን አንድነት፣ ቀኖና፣ ሕገ ቤተክርስቲያንና አስተዳደራዊ መዋቅር ሙሉ በሙሉ እንዲከበር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡ ከመንግሥት ጋር በተደረገው መግባባት መሰረት ሁኔታዎች የማይፈጸሙ ከሆነ፣ ቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ ተጋድሎዋን እንደምትቀጥል አስታውቃለች፡፡
ነዋሪነታቸው በኔዘርላንድስ እና ቤልጅየም የሆኑ ኢትዮጵያውያን ብራሰልስ ቤልጅየም ውስጥ ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ መንግሥት የቤተክርስቲያንን ነጻነትን እንዲያከብር ጠየቁ። ሰልፈኞቹ ከሰሞኑ ሃይማኖትን መሰረት ባደረገ መልኩ በቁጥጥር ስር የዋሉ ታሳሪዎች ይለቀቁ ዘንድም ጠይቀዋል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ለመንግሥት ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት በቤልጅየም ለኢትዮጵያ አምባሳደር ኂሩት ዘመነ አቅርበዋል። አምባሳደር ኂሩት በዚሁ ጊዜ የሰልፈኞቹን ጥያቄ ለመንግሥታቸው እንደሚያቀርቡላቸው ቃል ገብተዋል።
በሌላ መረጃ ከ1997 – 1999 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሪፓርተርነት እንዲሁ በዓይናችን ፕሮግራም ላይ ለተወሰነ ጊዜ በጋዜጠኝነት ያገለገሉትና ተወልዶ ባደጉበት በአምቦ በሰንበት ትምህርት ቤት ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቁት መጋቤ አእላፍ አበበ ያረጋል ታሰሩ። የመታሠራቸው ምክንያት “ለመምህር ምሕረተ አብ ስልክ ደውለህ ሊታሰር እንደሆነ እና እንዲሸሽ ነግረኸዋል” የሚል ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አያሌው ቢታኔ እስካሁን ባላቸው መረጃ ከ200 በላይ ምዕመናን መታሰራቸውን ተናግረዋል።
በሌላ መረጃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ። በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እየተመራ ወደ ሩሲያ ያቀናው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልዑካን ቡድን ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ተወያይቷል። በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኩል ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የቤተ ክርስቲያኗ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ፣ ብፁዕ አቡነ ሊዮኒድ በአፍሪካ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ሌሎች ልዑካን በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል። ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተወክለው ለሔዱት አባቶች በሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ስም የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። በመቀጠልም የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ያለችበት ቀውስ ከኢትዮጵያ ጋር ይመሳሰላል ያሉት ሊቀ ጳጳሱ ውጫዊ ግፊት ባለበት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያኗን በዘር ለመክፈል የተደረገው ሙከራ ቤተ ክርስቲያኗን ጎድቷል ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጎን ናት ሲሉ ገልጸዋል።
በሌላ መረጃ በቤተክርስቲያኒቷ የተወገዙት በቀድሞ ስማቸው እነ አባ ሳዊሮስ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ተገኝተው የይቅርታ ደብዳቤ አስገቡ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው የተለዩት በቀድሞ ሥማቸው እነ አባ ሳዊሮስ በዛሬው ዕለት በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ተገኝተው የይቅርታ ደብዳቤ አስገቡ። በቤተ ክርስቲያኒቱ የገጠመውን ፈተና ለመፍታት የኹለቱ ወገን አባቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአገር ሽማግሌዎች በጋራ ምክክር አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት፤ አንድነትን የሚያጸና እና አገልግሎትን የሚያሰፋ መንገድ መከተል ተገቢ መሆኑን በማመን ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ከየካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተፈጸሙ እስሮችን በተመለከተ፦ የአዲስ አበባን፣ የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስና የጸጥታ አካላት፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን፣ ምስክሮችን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በማነጋገር እንዲሁም በአዲስ አበባ የተለያዩ ማቆያ ቦታዎችን በመጎብኘት ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ። የተወሰኑ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በፍርድ ቤት ወይም በፖሊስ ጣቢያ ዋስትና እየተለቀቁ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ያረጋገጠ ቢሆንም አሁንም ብዙ ሰዎች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ “በተለያየ ዓይነት ወንጀል ተጠርጥረዋል” በሚል ዋስትናም ተከልክለው በእስር ላይ ይገኛሉ ተብሏል። ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር ተያይዞ የዚህ ዓይነቱ እስር የዘፈቀደ እስር ሊሆን ስለሚችል የመንግሥት የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት በሙሉ በበቂ ምክንያት በወንጀል የተጠረጠረን ሰው በሕጉ መሠረት ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ በተለይም በቅድመ ምርመራ ወቅት የዋስትና መብት አጠባበቅ ሥርዓትን ባከበረ መንገድ ምርመራ ከማድረግ ውጪ ተገቢ ያልሆነ እስር እንዲያስወግዱ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አሳስበዋል፡፡
በሌላ መረጃከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር በወቅታዊ ጉዳይ በተሰጠ መግለጫ፡- የኢትዮጵያ መገናኛ ብፀኃን ባለሙያዎች ማኅበር ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጠረውን ችግር በአንክሮ እየተከታተለው እንደሚገኝ ገልጾ ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ሕግ ባይፈቅድም፣ በመንግሥት ድጋፍ እንዳላቸው በሚታወቁ መገናኛ ብዙኃንም የቤተ ክርስቲያኗን፤ የሲኖዶሱንና የቅዱስ ፓትርያርኩን መግለጫዎች ሳይዘግቧቸው እንዳለፉ መረዳት ተችሏል። ከዚህ ሌላም የተፈጠረውን ችግር ምክንያት በማድረግ ወደ ከረረ ፖለቲካዊ እሳቤዎች ሙያዊ እና ሥነ ምግባራዊ ደንቦችን በጣሰ መልኩ የሚዘግቡ ሚዲያዎችንም ታዝበናል። ማኅበሩ፤ ምንም እንኳን ይህንን ዘግቡ፣ ይህንን ደግሞ አትዘግቡ የማለት ሥልጣን ባይኖረውም፣ አነጋጋሪ፣ ወቅታዊና በሕዝብ እሴት ላይ ተጽዕኖ ያላቸው ጉዳዮች መዘገብ እንዳለባቸው ግን ያምናል ብሏል።
በሌላ መረጃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የራሳቸውን ሲኖዶስ አቋቁመናል ካሉ የቀድሞ አባቶች ጋር የደረሰችው ስምምነት መጣሱን አሳወቀች። ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ የምንሰማቸው ነገሮች ሁሉ እንደገና ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል አባቶችን ከልጆች ልጆችን ከአባቶች የሚያሻክሩ ነገሮችን እየሰማን ሲል ተደምጧል። ከሁለት ቀናት በፊት በተፈጸመው ስምምነት ሰላም ቢፈጠርም አሁን ግን ሃይማኖቱንም ሕጉንም መልሰው መላልሰው ጥሰውታል፤ ሹመታቸው ሕጋዊ እንደሆነና በምንም ይሁን በምን የማይሻር መሆኑንም መልእክት አስተላልፈዋል። ሻሚና ተሻሚ በአስተሳሰባቸውም ሆነ በአነጋገራቸው ሁሉ በእኩል ደረጃ እንደሆኑም ተናግረዋል፤ 25 የተባሉትም የትናንትና ካህናት አገልጋዮች አሁንም ኤጲስ ቆጶሳት እንደሆኑ ተደርጎ ተንጸባርቋል። በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ነገሩን ለማጥራት ብንጠብቅም ቀኑን ሙሉ አንመጣም ሲሉ ዉለው 10 ሰዓት ላይ ግን ለማንም ለማን መጣን ሳይሉ በቤተ ክህነት ግቢ በሚገኘው ማረፊያ ቤታቸው ገብተዋል። ሆኖም ግን በስምምነቱ መሠረት የብሔር ብሔረሰቦች ኤጲስ ቆጶሳት ሿሚዎች ነን ያሉ 3 ሊቃነጳጳሳት የሰጡትን መግለጫ እስካላስተባበሉ ድረስ ከቤተክህነት እንዲወጡ ይደረጋል ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል።
በሌላ ዜና ዐሥሩን ነጥቦች ያለመሸራረፍ ለመተግበር ስምምነት እነ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተስማሙ። በተጨማሪም ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የፓሊስ አባላት ተመድበው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የጥበቃ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተገለጸ። በመግለጫውም “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አሕመድ በተገኙበት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ/ም በተደረገው ውይይት የተስማማንባቸውን (፲) ዐሥር ነጥቦች ያለመሸራረፍ ለመፈጸም እንዲሁም ቀጣዩን ተግባር በተመለከተ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ለማከናወን ተስማምተናል” በማለት ይፋዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ከመግለጫው በኋላም ወደ ማረፊያ ቤታቸው ገብተዋል። የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትም የአባቶችን መመለስ ተከትሎ የጸጥታ ሥራው አስተማማኝ መሆን ይችል ዘንድ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በሕጋዊ መልኩ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ በማመንና ጸጥታውን አስተማማኝ ለማድረግ እንዲሁም የጥበቃ ሥራውን ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚያከናውኑ የፌደራል ፓሊስ አባላት እንዲመደቡለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ስላገኘ ከፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን የፓሊስ አባላት ተመድበው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የጥበቃ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ ተብሏል።
በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት የአርሲ ነጌሌ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቀሲስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከእስር አለመፈታታቸው ተገለጸ። ሕገ ወጡ ቡድን በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እየታገዘ ባደረገው ወረራ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና መቀመጫ በሆነችው ሻሸመኔ ከ40 በላይ ኦርቶዶክሳውያን የተገደሉ ሲሆን የሀገረ ስብከቱን ሠራተኞች ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ መታሠራቸው ተዘግቧል። በወቅቱ በነጌሌ ወረዳ ቤተ ክህነት የቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ የአራት አድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም በርካታ ምእመናን ታሥረዋል። በእስር ላይ የሚገኙት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ዮሐንስ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል።
በሌላ መረጃ በኦሮሚያ ክልል አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ወልዳ ዳንዲ አቦቲ (ማኅበረ ፍኖተ አበው) በወቅታዊ ጉዳይና በስምምነቱ አተገባበር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ሊያዘጋጅ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ እሑድ የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 7:00 ሰዓት ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ የሚካሔድ ሲሆን ብፁዓን አባቶች እንደሚከናወን ተገልጿል። ወልዳ ዳንዲ አቦቲ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በሰላሌ ሀገረ ስብከትና በደቡብ ምእራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኙ ማኅበረ ካህናትና ምእመናን፣ ሰባክያን፣ መዘምራን በዕለቱ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሌላ ዜና በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል ለሁለተኛ ጊዜ የሁለትዮሽ ውይይት ከቅዳሜ የካቲት 4 ቀን እስከ የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሩሲያ ሞስኮ መደረጉን ተከተሎ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ክርስትናንና ክርስቲያኖችን መከላከል፣ በዘመናዊው ዓለም ክርስቲያናዊ ዕሴቶች እንዳይጠፉ መጠበቅ፣ በሚዲያ አማካኝነት የልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ በትምህርት ዘርፍ መደጋገፍን ጨምሮ በአስራ ሁለት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ፈጽመዋል። አብያተ ክርስቲያናቱ በጋራ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገው በጋራ ድምፃቸውን ለማሰማት የተስማሙ ሲሆን የመነኮሳት ልዑካንም ወደ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት እንዲሔዱና በሁለቱም በኩል ያለውን የገዳማውያን ሕይወት እንዲመለከቱም ዕቅድ ይዘዋል። በተጨማሪም የሞስኮ የነገረ መለኮት አካዳሚና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ በትብብር እንዲሠሩ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ልዑክ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲንና ሌሎች የኢትዮጵያ ቦታዎችን እንደሚጎበኝም ተጠቅሷል። ከዚህ ባለፈም የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ያሉ ቅዱሳን ቦታዎችን መጎብኘት እንዲችሉ ለማድረግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር ለመሥራት ተስማምተዋል።
በሌላ በኩል መምህር ምህረተአብን ጨምሮ ሌሎችም በእነ ፌቨን ክስ ስር የተካተቱት እንዲሁም ጋዜጠኛ ዮሴፍ ከተማ ከእስር ተፈተዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተፈጠረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን በቤተ ክርስቲያኗ በመምህርነት የሚያገለግሉ ሰባኬ ወንጌላውያንን ጨምሮ የማኅበራት ተወካዮችን እንዲሁም የችግሩን እውነታ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚናገሩ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች መታሰራቸው ይታወሳል። ለአብነትም በእስር ላይ ከሚገኙት መካከል መምህር ምሕረተአብ አሰፋ፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪ ፌቨን ዘሪሁን እና ሌሎችም መታሰራቸው ይታወሳል። በተጨማሪም ዲ/ን ዮሴፍ ከተማ (ጋዜጠኛ እና ደራሲ) በጸጥታ ኃይሎች ተወስዶ መታሰሩ ይታወሳል።
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የምዕራብ አርሲ፣ የሲዳማ፣ የጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተዋል። በውይይታቸውም በስምምነቱ መሠረት ሕገ ወጡን ሹመት ተከትሎ የታሠሩ ኦርቶዶክሳውያን እንዲፈቱ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት አካላትን እንድታሳስብ ብፁዕነታቸው ጠይቀዋል። በተጨማሪም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በሻሸመኔ ወደ ተገደሉት ሰማዕታት ቤተሰቦች እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ወደሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን በመሔድ እንዲያጽናኑ ጠይቀዋል። በውይይቱ ላይ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ብርሃኑ ወልደ ዮሐንስ የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በጅማ ከተማ ታስረው የነበሩ የሀገረ ስብከቱን ዋና ፀሐፊ ጨምሮ፣ የመንፈሳዊ ማኅበራት አስተባባሪዎች እና ካህናት አባቶች ከእስር ተፈተዋል። በእስር ላይ ከቆዩት ኦርቶዶክሳውያን መካከል ከጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታሰሩ ሰዎች የነበሩ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ሁሉም እስረኞች በዋስ መፈታታቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በጅማ ከተማ ታስረው የነበሩ የሀገረ ስብከቱን ዋና ፀሐፊ ጨምሮ፣ የመንፈሳዊ ማኅበራት አስተባባሪዎች እና ካህናት አባቶች ከእስር ተፈተዋል፡፡
