የሶማሊያ፣ የግብፅ፣ የቱርክ እና የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን የአገርነት እውቅና በይፋ አወግዘዋል።
የአራቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን እውቅና ሙሉ በሙሉ እንደሚቃወሙና እንደሚያወግዙ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም ለሶማሊያ ግዛታዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት ታማኝነት ያላቸውን ሙሉ ድጋፍ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ይህ የተነገረው የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሶማሊያ፣ ከቱርክ እና ከጅቡቲ አቻዎቻቸው ጋር በስልክ ከተወያዩ በኋላ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መሆኑን ዘ ጀሩሳሌም ፖስት በዘገባው አመልክቷል።
ይህ የተገለፀው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው የሶማሊላንድ ሪፐብሊክን እንደ ነጻ እና ሉዓላዊት ሀገር በይፋ መቀበሏን መግለፃቸውን ተከትሎ ነው። ይህም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ለውጥ መሆኑ ተገልጿል።
ኔታንያሁ ዛሬ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ዕውቅናው የተረጋገጠው ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር እና ከሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን መሐመድ አብዱላሂ ጋር በጋራ በተፈረመ “የሁለትዮሽ ስምምነት” አማካኝነት ነው።
ጠ/ሚሩ በመግለጫቸው ቀደም ሲል በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አነሳሽነት የተፈረመውን “የአብርሃም ስምምነት” መንፈስን የተከተለ መሆኑን ገልፀዋል።
ኔታንያሁ ፕሬዝዳንት አብዲራህማንን “ታሪካዊ መግለጫ” ባሉት በዚህ ስምምነት ላይ እንኳን ደስ ያለዎት ያሏቸው ሲሆን፤ ለሰላም እና ለመረጋጋት ላሳዩት ቁርጠኝነትና አመራር ምስጋና አቅርበውላቸዋል። በተጨማሪም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት በእስራኤል ይፋዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ አቅርበውላቸዋል።
ኔታንያሁ እንደገለጹት፤ እስራኤል በግብርና፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች በሚደረጉ ሰፊ ትብብሮች አማካኝነት ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስፋፋት አቅዳለች።
