“ቀን ከሌት ሕሊናዬ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው”

Date:

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

አንጋፋውንና ታላቁን ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን፣ በርካታ ጀግኖቻችንን በአጸደ ሥጋ እያጣን ባለንበት ዓመት ዳግም ላናገኝ አጥተናቸዋል፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው እስከመጨረሻዋ ሕቅታቸው ድረስ ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የደከሙና አብዝተውም የጻፉ ምሑር ከመኾናቸው ባሻገር ሃሳባቸውን ዘመኑ በፈቀደላቸው መረጃን የማሰራጫ መንገዶች (Platform) ኹሉ ተጠቅመው ከማሰራጨት ወደኋላ ያላሉ ታላቅ የሀገራችን ሊቅ ናቸው፡፡ መጽሔታችን ግዮንም ከአንድ ዓመት በፊት ለተከታታይ ኹለት ዕትሞች (ቁጥር 72 እና 73) በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ቃለ ምልልስ ከሚኖሩበት ሀገረ አሜሪካ አድርጋላቸው ነበር፡፡ ለትውስታ ይረዳ ዘንድ የተወሰነውን ክፍል እንደሚከተለው ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ከደጋጎቹ ጎን ያሳርፍልን!        

ግዮን፡- ከአገር ከወጡ ከበርካታ ዓመታት በኋላ በሀገር መሪ ደረጃ ከጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ብቻ ነው የተገናኙት፡፡ ለመሆኑ ለውጡን እንዴት አገኙት? ከእርሳቸው ጋርስ በሰዓቱ ምን ነበር ያወራችሁት?

ፕ/ር ጌታቸው፡- ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ዋሽንግተን ሲመጣ እኔ ሚኒሶታ ነበርኩኝ፡፡ ግን የአቀባበል ኮሚቴ ሲዋቀር “የዚህ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሁንልን”  ብለው ሰዎች ጠይቀውኝ ነበር፡፡ “መምጣቱ ደስ ብሎኛል፤ ግን ሊቀ መንበር ልሆን አልችልም፡፡ ምክንያቱም ሊ/መንበር ስሆን ወዲያና ወዲህ እያልኩ እሱ በሄደበት ቦታ መሄድ አለብኝ፡፡ ያንን ማድረግ ስለማልችል በሀሳብ አብሬያችሁ ነኝ” አልኳቸው፡፡ ሚኒሶታ ሲመጣ ግን እዛው ስነበርኩ ተገናኘን፡፡ እግዚአብሔር ይስጠው፤በደንብ አድርጎ፣ በጨዋ መልክ ነው የተቀበለኝ፡፡ እንደውም ከመምጣቱ በፊት የጻፈውን “እርካብና መንበር” የሚለውን መጽሐፍ በሰዎች በኩል ልኮልኝ ነበር፤ በፊት ገና ሳንተዋወቅ  ማለት ነው፡፡ መጽሐፉ ግን አልተፈረመበትም ነበርና እዛ ሳገኘው “ለምንድን ነው ያልተፈረመበት መጽሐፍ የላክልኝ? በል አሁን ፈርምልኝ” አልኩት፤ ደስ ብሎት ፈርሞበት ተዋወቅን፡፡

“አንተና ለማ መገርሳ ከሰማይ እንደወረዳችሁልን ነው የምናያችሁ፡፡ የኢትዮጵያን ስም ስታነሱ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ስታነሱ ሰማሁ፡፡ 27 ዓመት ሙሉ መለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ የቀጠቀጧት ኢትዮጵያን ከፍ በማድረጋችሁ ኮርቼባችኋለሁ?” ብዬ ሀሳቤን ገለጽኩለት፡፡ በደንብም ተግባባን፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በዛ ስብሰባ የእራት ፕሮግራም ላይ ንግግር ሲያደርግና የአንዳንድ ሰዎችን ስም ሲያነሳ፤ “ቀደም ሲል ጽሑፋቸውን እወድና አደንቅ የነበረውን ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌንም በማግኘቴ ደስ ብሎኞል” ሲልም በይፋ ተናገረ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ ሲል ተገናኝተን ስናወራ “እስካሁን የምጽፈውን ከወደድከው ወደፊትም በዛው ነው የምቀጥለው፡፡ ምናልባት በአስተሳሰብ የተለያየን ከሆነ፣ መለያየቱ ከእኔ በኩል ላይሆን ይችላልና የሚሰማኝን እጽፋለሁ” አልኩት፡፡ እሱም ‹‹ግድ የለም ጻፍ›› ብሎኝ ተለያያን፡፡ ይኸው ከዛን ጊዜ ጀምሮ የማምንበትንና እውነታውን እንደፃፍኩ ነው፡፡

ግዮን፡- ከሀገር ከወጡ አርባ ዓመት አለፈዎት፤ ኢትዮጵያ አልናፈቀችዎትም?

ፕ/ር ጌታቸው፡- እንዴት አይናፍቀኝም ፤ ቀን ከሌት ሕሊናዬ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ሚኒሶታ በነበርኩበት ጊዜ ጥሩ ጎረቤቶች ነበሩኝ ፣ መ/ቤቱ ደግሞ ከፍ አድርጎ በአክብሮት ነው የተቀበለኝ፤ በመሆኑም ከእነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ፡፡ ከዚያ ውጭ የአሜሪካ ፖለቲካን በፍፁም ዞር ብዬም የማየው አይደለሁም፤ የኢትዮጵያ ላይ ነው አዕምሮዬ ያለው፡፡

በምሠራበት መ/ቤት የማነባቸው መጽሐፍት ከኢትዮጵያ ገዳማት የመጡ ስለሆኑ ቁጭ ብዬ ሳነብ አንዳንድ ጊዜ ደብረ ሊባኖስ ያለሁ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደብረ ሐይቅ ያለሁም ይመስለኛል፡፡  በታሪክ በኩል ከጥንት ጀምሮ የተጻፉ መጽሐፍትን ሳነብ፤ ሊቃውንቱ በየቦታው እየዞሩ ሲያስተምሩ ምን እንዳጋጠማቸው፣ ምን እንዳዩ፣ ምን እንዳደረጉ ሳነብ ከእነሱ ጋር አብሬ ያለኹ ያህል ነው የሚመስለኝ፡፡

ያን ጊዜ ኢትዮጵያ በአካል የምትናፍቀኝ ሁኔታ ላይ አልነበረችም፡፡ እነ መለስ ዜናዊ በጣም አጎሳቁለዋታል፣  ያ መጎሳቆል በጣም ይሰማኝ ነበር፡፡ በኋላ ዶ/ር ዐቢይ መጥተው “ኢትዮጵያ አገራችን፣ ኢትዮጵያ ታሪካችን” ሲሉ ብዙዎቻችን በደስታ ጨፍረናል፡፡ ያለፈው ጊዜ የጨለማ ዘመን ነበር ብለው ከተናገሩ፣ የብርሃን ዘመን ከፊት ለፊት ይመጣል ማለታቸው ነው ብለን በደስታ ሰከርን፡፡ “አገሪቱን የቀን ጅቦች ናቸው ሲገዟት የነበሩት” ከተባለ ፣ የሌሊት ጅቦች ይመጣሉ ብለን አላሰብንም፡፡

በቤተክርስቲያን ደረጃ እዚህ አቡነ ይስሃቅን ተከትለን “አግዙን” ሲሉ እናገለግላለን፡፡ አጠገቤ ቤተክርስቲያን አለ፣ ሌሊት መነሳቱና ለእኔ የሚሆን መኪና ማግኘቱ ጭንቅ ቢሆንም፤ ካጋጠመኝ ግን ቅዳሴም ላይ እገኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ ስብሰባ ሲደረግ ፣ እገዛ ሲያስፈልግ አቅሜ የሚችለውን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ ከዚሁ በዘለለ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሀሳብ አልነበረኝም ፤ አሁን ግን አገሬን ለማየት ፈልጌያለሁ፡፡ እዚህ የምኖረው በኢትዮጵያ ፓስፖርት ነው ፤ የአሜሪካ ፓስፖርት የሚገኘው አሜሪካዊ ሲኮን ብቻ ነው፡፡ እኔ እዛ ድረስ አልሄድኩም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እመለሳለሁ በማለት በኢትዮጵያዊነት ነው ጸንቼ የቆየኹት፡፡ ወደ ፊት ግን ኢትዮጵያ ሣልመጣ አልቀርም፡፡

ግዮን፡- ብዙ ችግሮች በየቦታው እየታዩ ነውና ቀጣዩ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ?

ፕ/ር ጌታቸው፡- አሁን በአገሪቱ የሚታየው ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛ ሕዝቡ በእውነት ይሄንን መከፋፈል ይወደዋል ወይ? የሚለው ነው፡፡  ሕዝብ እንደ መሪው ስለሚሄድ ነው የሚያስቸግረው፡፡ መሪ ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ አንድነት ይቀድማል ካለ ሕዝቡም ያንን ነው የሚያስተጋባው፡፡ መሪው ስለ ብሔርና መከፋፈል ካነሳ፣ ሕዝብም ያንን ቋንቋው ያደርገዋል ፤ ዕምነቱም ያደርገዋል፡፡ የሚቀጥለው ምርጫም በዚህ ጉዳይ ላይ ወሳኝ ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ ምርጫው ክፍት ነው መሆን ያለበት፡፡ ክፍት ተደርጎ ፤ የምርጫ ሳጥኑን ጠባቂዎች፣ የአካባቢው ሰዎች ከሆኑ አጠራጣሪ ቢሆንም በቂውን ጥንቃቄ  አድርጎ፤ “ምርጫውን በፈለጋችሁት በሃይማኖት፣ በዘር ሆነ በአይዶሎጂ ተከራከሩና፣ ሕዝብ የፈለገውን ይምረጥ” ብሎ መፍቀድ ይገባል፡፡

 መንግሥት  ያንን ካደረገ ምናልባት እኔ እንደሚመስለኝ የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈለገው ብዙ ነውና ውጤቱ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን በደቡብ፣ በሲዳማና በወላይታዎች የሚቀርበው የመንግሥትነት ጥያቄ፤ “ሌላው ሲሆን እኛስ ለምን ይቀርብናል” የማለት ነው እንጂ አስፈላጊ ሆኖ አይደለም፡፡

ዶ/ር ዐቢይ አሜሪካን የመጣ ጊዜ ፤ ያ ሁሉ ህዝብ የመጣው እኮ ኢትዮጵያውያን በሙሉ አንድ ነን ስላለ ነው፡፡ ሰኔ 16 አዲስ አበባ ላይ ሊያመሰግነው የወጣውም ሕዝብ ከዚህ ስሜት በመነሳት ነበር፡፡ አሁንም ስለኢትዮጵያ አንዳንድ ነገሮችን በተናገረ ቁጥር ሕዝብ በጣም ነው የሚያጨበጭብለት ፡፡ ስለመከፋፈላችን ቢያነሳ ኖሮ ይሄንን ዕድል እንደማያገኝ ግልጽ ነው፡፡  በመሆኑም ጠ/ሚኒስትሩ በብሔር የተከፋፈሉ ፓርቲዎች እንዲበዙ፣ ጠንካራና ሀገራዊ ፓርቲ እንዳይመሰረት ከጨከነ ተበታትነን ነው የምንቀረው፡፡ ምናልባት እንደአውሮፓውያን ዩኒየን ፓርላሜንት ሊኖር ይችላል፤ እንደ ጎረቤታማች ሀገር ሁሉም እርስ በርሱ ጎረቤት ሆኖ ይኖራል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ “ይሄ ክልል ለእኔ ተሰጥቶኛልና አንተ እንግዳ ነህ” ዓይነት ነገር ነው እየተስተዋለ ነው ያለው፡፡

ደቡብ ውስጥ ላሉ ትግሬዎች የሚያስበው የትግራይ መሪ፣ ጋምቤላ ውስጥ ላሉ አማሮች አይዟችሁ የሚለው የአማራ መሪ እየሆነ ነው፡፡ ይሄ የትና ወዴት እየሄድን እንደሆነ ያሳያል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በየክልሉ የሌላ ብሔር ተወላጅ ሲመጣ፤ በገዛ አገሩ ላይ በእንግድነት ነው ሊያስተናግዱት  የሚፈልጉት፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው መሪዎች ባመጡት ነገር ነው ፤ መለስ ዜናዊ ይሄንን ባያመጣ ኖሮ፣ ፈፅሞ እንዲህ ያለ አደጋ ውስጥ አንወድቅም ነበር፡፡

ግዮን፡- ደቂቀ እስጢፋኖስ የተሰኘው መጽሐፍዎ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የታተመ ጊዜ መግቢያውን ስለ እርስዎ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ነበር የፃፉት እሱ ነገር እንዳይወጣ ቢከለከልም ታትሟል፡፡ ለምንድን ነበር እንደዛ የሆነው?

ፕ/ር ጌታቸው፡- እሱ ከሆነ ትንሽ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖታል፡፡ ብዙ ወደ ዝርዝሩ ባይገባም መቅድሙ ላይ ፕ/ር መስፍን ነበር የፃፈልኝ፡፡ ያንን አይቶ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ማሣተም ፈራ፡፡ ለነገሩ ዩኒቨርስቲው ሄዶ መንግስትን መጠየቅ ይቻል ነበር፡፡ ይሄንን መጽሐፍ ልናሳትም ነውና ቅሬታ አለህ ወይ ብሎ መጠየቅ ይቻል ነበር ያንን ባለማድረጋቸውና በደፈናው ዩንቨርስቲው በመፍራቱ መቅደሙን ሌላ ሰው ፃፈው፡፡ በዛን ወቅት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ቅር እንዳው ይገባኛል፡፡

ነገር ግን ጭቆና እንዳለ፣ እሱ ይታገልለት የነበረው የመፃፍ ነፃነት እንደቀጠለ እንደማስረጃ ሊወስደው ይችል ነበር፡፡ ፕ/ር ሽፈራው መቅድሙን ፃፈልኝ እንደገና ታተመ መጽሐፉ በኋላ መጽሐፉ ከወጣ በኋላ ዩንቨርስቲው ፈርቶ ያስቀረውን የፕ/ር መስፍን መቅድም (መግቢያ) ጋዜጦች ናቸው ይፋ ያደረጉት፡፡

ግዮን፡- ይህ መጽሐፍዎ በብሔራዊ ቴአትር ሲመረቅ ኦቦይ ስብሃት ነጋ ተገኝተው ውዝግብ ሁሉ ተፈጥሮ ነበር  እስቲ ስለ እሱ ይንገሩን

ፕ/ር ጌታቸው፡- አቦይ ስብሃት መጽሐፌ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ይቃወም ነበር መጽሐፉ እንዳይታተም ብሎ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉን ሰምቻለሁ እኔ ሰውየው ማን እንደሆነ ራሱ ትዝ አይለኝም፡፡ ደግሞ ደቂቀ እስጢፋኖስ መኖሩን ነው እንጂ፣ መጽሐፉን ራሱ ለመተርጎም አስቤ ራሴ አላነበብኩትም ነበር፣ አልታተመም፡፡ ደቂቀ እስጢፋኖስን ማንም አያውቀውም ነበር እኔ ነኝ ፈልጌ ያሣተምኩት፡፡

እነሱ የመሰላቸው አንድ የአማራ ንጉሥ አፄ ዘረያዕቆብ የሚባል የትግራይ ካህናትን ይጨቁን ነበር ብለው ለማስረጃ ለመውሰድ ነው፡፡ ገና አዲስ አበባ እንደመጡ ኮፒውን ፈልጉልን ብለው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መጥተው ነበር፡፡ በመጽሐፉ እንደተገለፀው አንደኛ ነገር ዘረ ያዕቆብ እናቱ ትግሬ ነች፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ ንጉሶች የኢትዮጵያ ነገሥታት ናቸው እንጂ የትግሬ ነገሥታት የአማራ ነገስታት አይደሉም፡፡ ደብረብርሃን ላይ መንግሥቱን ስላደረገ አማራ ነው ማለት አይደለም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

ሁለተኛና ዋናው ነገር እዚያ ውስጥ ረብሻ ያነሣሉ የነበሩት የትግሬ ካህናት ናቸው፡፡ ለንጉሱ ሄደው ደቂቀ እስጢፋኖስ አንተን ሊያጠፉ ይፈልጋሉ እኛንም ገዳማችንን ሊያዘጉብን ነው መነኮሳቱን እያሳከዱ ባዶ እጃችንን አስቀሩን ለአንተ አይሰግዱልህም አንተን አያከብሩህም፡፡

እነሱ ንጉሥ አለማክበር ሣይሆን ለንጉሥና ለእግዚአብሔር ያለ አክብሮት የተለያዩ ናቸው፡፡ ለማርያም የሚሠጣት አክብሮ እንደ እናትነቷ እንጂ እንደ አምላክ አይደለም እያሉ ነበር ደቂቀ እስጢፋኖስ የሚናገሩት እኔም ብሆን ያሳተምኩት እሳቸው ያሉት ትክክል እንደሆነና እንዳተሳሳቱ ደግሞም በሀገራችን እንዲህ ያሉ ጠንካራ ሰዎች እንደነበሩ ለማሣየት ነው እንጂ መጀመሪያው ጥፋቱ የነበረው የትግሬዎቹ መነኮሳት ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ መጽሐፉን ያነበበ ሰው ሊረዳው ይቻላል፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያውያን ኦንላይን እየተሰበሰባችሁ፣ በቋንቋ፣ በባኅልና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ትጽፋላችሁ ሰምና ወርቅ በሚል ርዕስ እሱ ነገር አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው

ፕ/ር ጌታቸው፡- አንድ ፋንታሁን የሚባል ኢትዮጵያዊና በጣም ጎበዝ ሰው አለ፤ እሱ ነው ይሄን ፕሮግራም የሚያካሄደው የሚያሳተስመው፡፡ አዲስ ባወጣው ቁጥር እኔንም እያጋበዘኝ አንዳንድ ተሳትፎ አደርጋለሁ ጸሐፊዎችን ከየቦታው እየፈለገ ነው የሚያጽፈው እኔንም ኤዲቶሪያል  ቦርዱ ውስጥ ያስገባኛል ይመስለኛል፣ ሳስበው ጊዜ ሲኖረኝ ደስ እያለኝ ነበር የምጽፍላቸው፡፡

ግዮን፡- ምን ያህል ዓመት ሆነው?

ፕ/ር ጌታቸው፡- እየወደቀ እየተነሳም ነው በሥራ ላይ ግን ስንት እንደሆነው አሁን ላይ በርግጠኝነት  አላስታውስም፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያ ብዙ ምሁራን ቢኖሯትም በተገቢው መንገድ ዕውቀታቸውን ለሀገራቸው አልሰጡም ይባላል፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ፕ/ር ጌታቸው፡- ምሁሮች የኢትዮጵያን ታሪክ ይጽፋሉ በየቦታው እየተገኙ በስብሰባዎችና በኮንፍረንሶች ላይ የሚያውቁትን ይናገራሉ፡፡ ምሁር ማለት ወታደርነት አይደለም፤ ወይንም ጠመንጃ ይዞ ወጥቶ መታኮስ አይደለም፡፡

ብዙ ጊዜ ምሁሮች ሲወቀሱ እናያለን ግን ኢትዮጵያ ዩንቨርሲቲ ያሉትን 40 ምሁራን በአንድ ቀን ከሥራ ወጥታችኋል ያሏቸው ወያኔዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ጊዜያቸውን በሙሉ ትምህርታቸው ላይ ያተኮሩ ናቸው እንጂ እንደ ነጋዴዎች ሀብት ያካበቱ አይደለም፡፡ እነዛ ሰዎች ልጆችና ሚስቶቻቸውን እንኳን በቅጡ በማይዙበት ደሞወዝ እየሰሩ ከሥራ ወጥታችኋል ሲባሉ የት እንደሚሄዱ አስበው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ምሁርነት የሚያስጎመጅ ወይም የሚያስመኝ ነገር አይደለም፡፡ ለፖለቲካ ዓላማ ሲባል እነዚህ ሰዎች ምን በወጣቸውና ይበደላሉ፣ ስለዚህ አሁንም ያሉት ዝም ቢሉ በዝምታ ሀገራቸውን ጎድተውት ይሆን እንጂ በዝምታ የተጎዱ የሉም፡፤ በርግጥ የሚተባበሩ ምሁራንም  አሉ፡፡ እንደ ዘመኑ ሁኔታ ከደርግም ጋር ሆነ ከወያኔ ጋር የተባበሩ አሉ፡፡ እነሱ ሊወቀሱ ይገባል ሌሎቹ ግን ዝም ያሉት ምሁራንም የሚወቀሱ አይመስለኝም፡፡ የተቻላቸውን ያህል ያደርጋሉ፣ የሚፃፈውን ይጽፋሉ፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...