ሦስት ጊዜ ትሞታለህ፣ በአራተኛውም ታርፋለህ
የተወለደው ፍልስጤም ልዩ ስሟ “ልዳ” ውስጥ በ277 ዓ.ም ጥር 20 ነው፡፡ አባቱ የልዳ መኳንንት ዞሮንቶስ፣ እናቱ ቴዎብስታ ይባበላሉ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፡፡ የስሙ ትርጓሜ “ኮከብ ብሩህ፣ ፀሐይ” ማለት ነው፡፡ በዐሥር ዓመቱ አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ወስዶ በጦር ኃይል አሰልጠኖ አሳደገው፡፡
በሃያ ዓመቱም መስፍኑ የ15 ዓመት ሴት ልጁን ሊያገባው ሲያስደግስ ጌታችን ለዚህ አላጨውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ኀዘኑን ጨርሶ ወደ ቤሩት ከተማ ሄደ፡፡ በዚያም የሚመለክና ሴት ልጆቻቸውን የሚገብሩለትን ደራጎን ገድሎ ሕዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል፡፡
ወደ ፋርስም ሲሔድ ንጉሱ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት ሲያመልኩ ቢያገኛቸው በነገሥታት ፊት የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ፡፡
ንጉሱም የቅዱስ ጊዮርጊስን ማንነት ከተረዳ በኋላ “አንተማ የኛ ሰው ነህ በዐሥር አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ” አለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም “አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን ላንተ ሹመት ስል አልክደውም” አለው፡፡
ዱድያኖስም እጅግ ተቆጥቶ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን አደረሰበት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ግን ጌታችንን “ይህን ከሃዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰዳት” በማለት ለመነው፡፡ እግዚአብሔርም ጽናትን ሰጥቶታል፡፡ የደረሱበት እጅግ አሠቃቂ መከራዎች የሰው ኅሊና ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸው ናቸው፡፡
በእንጨት ላይ ሰቅለው ሥጋውን በመቃን አስፈተተው፣ ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምተው ሂድ አሉት፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል፡፡ ሰውነቱን በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ሲነሰንስበት ሥጋው መሬት ላይ ወደቀ፡፡
ዳግመኛም በሰባ ችንካሮች አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ ፈወሰውና “ገና ስድስት ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ በ4ኛውም ታርፋለህ፣ በመከራህም ሁሉ አልለይህም አለው፡፡
ዱድያኖስም ቅዱስ ጊዮርጊስን “ለሚያሸንፍልኝ ብዙ ወርቅ እሰጠዋለሁ” አለ፡፡ አንድ መሰርይ መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞበት ለቅዱስ ጊዮርጊስ አጠጣው። ሰማዕቱም ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል፤ ጠንቋዩ ማረኝ ብሎ ከእግሩ ሥር ወደቀ፡፡
ንጉሱም ጊዮርጊስን በመንኰራኩር አስፈጭቶ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ዘግቶ አትሞበት ሄደ፡፡ ጌታችንም የተፈጨውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥጋ በእጁ ዳስሶ ፈውሶታል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስም ወደ ንጉሡ ተመልሶ “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” በማለት መሰከረ፡፡ በፊቱም ሙት ማስነሳትና በርካታ ድንቅ ተአምራት አድርጎ ቢያሳየውም አላመነም ይልቁንም በተደጋጋሚ አሰቃው ጌታችንም ሦስት ጊዜ ከሞት አስነሣው፡፡
በመጨረሻም ሚያዝያ 23 ወታደሮች ሥጋውን ፈጭተው በደብረ ይድራስ ተራራ በትነውት ወደ ንጉሡ ሲመለሱ በመንገድ ከኋላቸው ሄዶ “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” ሲላቸው በጌታችን አምነው በመመስከርም በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስም በሰይፍ አንገቱን ተመቶ ሲሞት ሰባውን ነገስታት አጥፍቷቸዋል፡፡
ስለ ክርሳቶስ ፍቅር ሲሉ ዓለምን የናቁ ገዳማውያን ይህን አብነት አድርገው ይጸናሉና ጸሎታቸው ኃይልን ታደርጋለች፡፡ እኛም ገዳማቸውን ስንደግፍ በዓታቸውን ስናጸና የበረከታቸው ተሳታፊ እንሆናለን፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ 1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ 141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444
