የሀገረ-ሰብ (ካንትሪ) ሙዚቃ ንግሥት እየተባለች የምትጠራው አሜሪካዊቷ ዶሊ ፓርተን ከዚህ ዓለም መለየቷን ቃል አቀባይዋ ማርሴል ፓሪሶ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል።
በተወለደች በ80 ዓመቷ ከዚህ ዓለም የተለየችው ተወዳጇ የሙዚቃ ሰው በካንሰር ሕመም ማረፏን ቃል አቀባይዋ ገልጸዋል።የሀገሯ የአሜሪካ ባንዲራም በዚህች አንጋፋ የሙዚቃ ሰው ሞት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተደርጓል።
በጎርጎሪያኑ ጥር 19፣ 1946 የተወለደችው ዶሊ ፓርተን በሴቪየር ካውንቲ፣ ቴነሲ ውስጥ ከ11 ወንድሞችና እህቶች ጋር ነው ያደገችው። ዶሊ ያደገችው በሙዚቀኛ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን ጊታር መጫወት የተማረችው በ7 ዓመቷ ነበር። በቴሌቪዥን የመጀመሪያውን ትርኢቷን ያቀረበችው ደግሞ በ10 ዓመቷ ነበር።
በሰባት አስርተ ዓመታት የሥራ ዘመኗ ከተወዳጅ የሙዚቃ ስራዎቿ ባሻገር ፋሽን መከተል ትወድ ነበር የነበረሲሆን፤ በተለይም የፀጉር አበጣጠርን በተመለከተ መለያዋ የሆነውን ቢጫ ጸጉር እና የተለያዩ ከአለባበሷ ጋር የሚሄዱ ሰው ሰራሽ ፀጉሮችንም ታዘወትር ነበር።
ዶሊ ፓርተን፣ በተለይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በሰፊው የሚታወቀውን «ጆሊን» ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሙዚቃ ግጥሞችን ጽፋለች። እነዚህ ተወዳጅ ስራዎቿ በዓለም አቀፍ ሽያጭ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ፤በኢንተርኔት ደግሞ ከአንድ ቢሊዮን በላይ እይታዎችን አግኝተዋል።
ከቴነሲ ተራሮች ተነስታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነ መሆን የቻለችው ዶሊ ፓርተን በናሽቪል ህይወቷ ማለፉ ከተሰማ ጀምሮ በአሜሪካ እና በመላው ዓለም የሚገኙ አድናቂዎቿ ሀዘናቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።
