የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በዓላትን መሰረት ተደርገው ለገበያ የቀረቡ የምግብ ምርቶች ጤናማ መሆናቸውን ለማረጋገጥና ችግር በተገኘባቸው ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከማዕከል እና ከቅርንጫፍ ጽ/ቤት ባለሙያዎችን በማዋቀር የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም የዶሮ መሸጫ አካባቢዎች ላይ ንፅህናው በጎደለው ቦታ ላይ የዶሮ እርድ ሲከናወን እና በማሸጊያ ታሽጎ ሲሸጡ የሚገኙት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ የባለስልጣኑ የምግብና ጤና ነክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
ንፅህናው በጎደለው ቦታዎች ላይ እርድ በሚያከናውኑ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ እና ህብረተሰቡን ዶሮ በሚታረድባቸው ቦታዎች ላይ እርድ ማከናወን እንደሌለባቸው ባለስልጣኑ አስታዉቋል።
የቁጥጥር ስራው እስከ ጥምቀት በአል እንደሚቀጥል ባለስልጣኑ የገለጸ ሲሆን ህብረተሰቡ የበአል ሸመታዎችን ሲያካሂድ ከባለስልጣኑ የብቃት ማረጋገጫ ከወሰዱ ተቋማት እንዲሸምት እንዲሁም የምርቶችን የአገልግሎት ጊዜ አለማብቃቱን በማረጋገጥ እንዲገበያይ አሳስቧል።
በግብይት ወቅት የሚከሰቱ ህገወጥ አሰራሮች ሲመለከቱ በተቋሙ ነፃ የስልክ መስመር 8864 በመደወል እንዲሁም በአቅራቢያ ለሚገኝ ደንብ ማስከበር ጥቆማ ሊሰጡ ይገባል ሲሉ አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
