በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ላይ ለመሰማራት የሚመጡ ኢንቨስተሮች መሬት ለማግኘት እንዳይቸገሩ በጥናት ላይ የተመሰረተ የመሬት ልየታ እንዲኖር ጥሪ ቀረበ።
የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘዉዴ እንደገለጹት፣ የመሬት ችግር በዘርፉ ካሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች አንዱ ነው። ችግሩን ለመቅረፍ በጥናት ላይ የተመሰረተ የመሬት ልየታ አስፈላጊ ነው። ይህ አካሄድ ለሆርቲካልቸር ተስማሚ የሆኑ መሬቶችን ለይቶ በማቅረብ ኢንቨስተሮች በቀላሉ መሬት እንዲያገኙ ያስችላል።
ይህ የተገለፀዉ በኢዲስ አበባ ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ለማካሄድ በታሰዉ 9ኛዉ ሆርቲፎራ ኤክስፖ ላይ በተሰጠዉ መግለጫ ነዉ። ይህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት የኢትዮጵያን የሆርቲካልቸር ዘርፍ ለማሳየት፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ዘላቂነትን ለማበረታታት ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ከአለም አምስት ዋና የአበባ ላኪዎች አንዷ ስትሆን በዘርፉ ከ200,000 በላይ ቀጥተኛ የስራ እድሎችን ፈጥራለች። በጥናት ላይ የተመሰረተ የመሬት ልየታ ተግባራዊ ቢደረግ ዘርፉን በእጅጉ ሊያሳድገው እንደሚችል በመድረኩ ተገልጿል።
