በሰብአዊ መብቶች፣ በጾታ እኩልነት እና በሰላም ግንባታ ላይ የወጣቶች ሚና

Date:

[ሕግ እና ትግበራው]

ዜናዬነህ ግርማ

ዳራ                                               

ወጣቶች በሰብአዊ መብቶች፣ በጾታ እኩልነት እና በሠላም ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱት እንደ ሀሳብ አመንጪ እና ፈጣሪ እንዲሁም የለውጥ ደጋፊ በመሆን፣ ያሉትን የጾታ እኩል ተጠቃሚነት ኢፍትሃዊነትን በመቃወም እና ማህበረሰብን መሰረት ያደረጉ መልካም ውጥኖችን በመምራት ነው። በግጭት አፈታት ላይ አዳዲስ አመለካከቶችን ያመጣሉ፣ ማህበራዊ ትስስርን ያራምዳሉ እና መቻቻልን ያበረታታሉ፣ ነገር ግን ውጤታማነታቸው የሚጠናከረው በትውልዶች ቅብብል እና ትብብር  አካታች ፖሊሲዎች ተሳትፏቸውን በሚደግፉ እና በስርዓተ-ፆታ ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ጐልተዉ ሲታዩ እና ሲወጡ ነው።

ስለሆነም በሰብአዊ መብት፣ በጾታ እኩልነት እና በሰላም ግንባታ ላይ ፍትሃዊ የህግ ማዕቀፍ በማቋቋም፣ ፍትህን በእኩልነት የማግኘትና ተጠያቂነት ያለባቸው ተቋማትን በማቋቋም የህግ የበላይነትን ማስፈን ወሳኝ ነው። በዚህ ማዕቀፍ ወጣቶች የመልካም አስተዳደርን በማጠናከር፣ ከአድልዎና ከአመጽ ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግ ድጋፍ በማድረግ እና ከግጭት በኋላ ለማገገም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ።

ወጣቶችን በማብቃት የህግ የበላይነት ሚና ስናነሳ ሰብአዊ መብት ለተቋማዊ ዜግነት (corporate citizenship) ማዕከላዊ ነጥብ ለመድረስ ጤናማ መነሻ መሠረት ነው፡፡ በተለይም ዛሬ ላይ የሰብአዊ መብት ጉዳይ በዓለማችን ላሉ ተቋማት ቁልፍና መሠረታዊ የሥራ አፈፃጸማቸው ማሳያ እስከመኾን ደርሷል። ባለንበት የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ፣ በሰብአዊ መብት ዙሪያ በሚነሱ ክርክሮች ረገድ ካሉ ጉልህ ለውጦች አንዱም በጾታ እኩልነት እና ሰላምን በማስቀጠል መካከል ያለውን ግንኙነት ማሳደግ ተጠቃሽ ነው። ለሁለቱም ፆታዎች ሰብአዊ መብቶች መከበር ሚናው የማይጓደልና በዋጋ ሊተመን የማይችል ማኅበረሰብ እንዲኖር እና ለውጤቱ ስምረት እንዲያግዝም በርካታ ሉላዊ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በተደጋጋሚ ይነሳል።

እንደሚታወቀው ሰላም አሉታዊ እና አዎንታዊ ተብሎ ይገለጻል፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይም ሴቶች በሰላም ሂደት ውስጥ እና ደህንነቱ በተጠበቀ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ አዎንታዊ ሰላምን እስከመጨረሻው ማረጋገጥ እንዳለባቸው ይታመናል። ሰላም ሁሌም የሰው ልጅ ትልቁ እሴት ነው። እጅግ በጣም ጎጂ የሆነው ሰላም ሳይቀር ከፍትሓዊ ጦርነት የሚሻለው ለዚህ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የግጭትን መርሆዎች በዘነጋ ሁኔታ ሰላም የሚገለጸው ተጨባጭ ግጭት (Physical Conflict) ያለመኖርን ከሰላም ጋር ለማዛመድ በመሞከር ነው።

ይህ ግን ሰላም ሳይሆን “አሉታዊ ሰላም” ነው የሚባለው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰላም ስምምነት ወይም መረጋጋት ተደርጎም ይታያል። ይህ ብየና ትክክል የሚኾነው ግን ከሰዎች የአእምሮ ሰላም ወይም መረጋጋት ጋር የተያያዘ ከሆነ ነው፡፡ በርግጥም ይሄ “አዎንታዊ ሰላም” ነው።

እዚህ ጋር የሰብአዊ መብት የማዕዘን ድንጋይ የሆነው የጾታ እኩልነት ጉዳይ ለአዎንታዊ ሰላም መከበርና መስፈን ብሎም ለሰላምን ግንባታ እና ቀጣይነት ወሳኝ ሚና አለው። በርካታ የሰላም ውይይቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳይሳኩ ቁልፍ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱም ሴቶችን ከሰላም ስምምነት እና አስፈፃሚ አካላት ድርድር የማግለል አካሄዶች መኖራቸው ነው። ለአብነት እንኳን ሩቅ ሳንሄድ በሀገራችን በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር አካላት ሥርዓተ-ፆታ ላይ ባለው የተዛባ አመለካከት ሳቢያ ሴቶች እና ልጃገረዶች የበታች እንደነበሩ እና አሁንም እንደኾኑ መታዘብ እንችላለን። የሚያስገርመው ጉዳይ ግን እንዲህ ያለው ያፈጠጠ እውነታ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ቀጥተኛ ምክንያት እንደሆነ እንኳን እስካሁን እውቅና ያልተሰጠው መኾኑ ነው።

ሰብአዊ መብቶች ተዋረዳዊ (Vertical) ተጽዕኖ ስላላቸው በመንግሥት እና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት ይወስናሉ፡፡ በአግድሞሽ (Horizontal) ተጽዕኖው ደግሞ በዜጎች መካከል ያለው ግንኙነት በእኩልነት መርህ ላይ እንዲሆን ያዛል። ከዚህ በመነሳት ታዲያ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገቡ የተለያዩ ምሁራን እና ፖለቲከኞች አዎንታዊ ሰላም ይቅርና አሉታዊ ሰላም መኖሩን እንኳን ይጠራጠራሉ። ጥያቄውም ኢትዮጵያ ለሰብአዊ ልማት ቁልፍ እና የማይነቃነቅ ህብረተሰብ ፈጥራ አዎንታዊ ወደሆነ ሰላም እንዴት ትሸጋገራለች? የሚል ኾኗል፡፡ በአናቱም ለሰላም ግንባታ ዋና ተዋናዮች እነማን እንደሆኑ፤ ሰላምን ለማስቀጠል የሰብአዊ መብቶች መሠረታዊ ጉዳዮች ምን ምን እንደኾኑ መረዳትን ስለሚፈልግ ወደ አዎንታዊ ሰላም የሚደረግ ጉዞ የብዙ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተዋንያን ጣልቃ ገብነትን ከግለሰባዊ ባህሪ እና ገጸ-ባህሪ ጋር እንደሚጠይቅ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ለማጠቃለል፣ የሁሉም ዜጋ ሙሉ ተሳትፎ ከሌለ በተለይም የወጣቶች ንቁ እና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሳይኖር በአንድ ሀገር ውስጥ ሰላምን ማስቀጠል አይቻልም፡፡ ስለዚህ የወጣቶችን በሰላማዊ ውይይቶች እና ድርድሮች ላይ በንቃት የመሳተፍ አስፈላጊነት ከግምት ማስገባት ይገባል፡፡ ይኽ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ መንግሥትም የሰብአዊ መብት ጥበቃን በተመለከተ አዎንታዊ እና አሉታዊ ግዴታዎቹን መወጣት መቻል አለበት፡፡

—————

ዜናዬነህ ግርማ በዩዝ ኤንድ ካልቸራል ደቨሎፕመንት ፋውንዴሽን (YCDF) ዋና ዳይሬክተር ስትራቴጂክ መሪ ናቸው። በ ወጣቶች እና የማህበረሰብ ለዉጥ በማምጣት እና ቁርጠኝነታቸዉን በማሳየት  ከ 20 ዓመት በላይ ተጽእኖአቸዉን ማሳረፍ ችለዋል። አስተያየቶን በ info@ycdfet.org ወይም zenayeneh.g@ycdfet.org ሊያደርሷቸው ይችላሉ፡፡

—————-

ዩዝ ኤንድ ደቨሎፕመንት ፋውንዴሽን (YCDF) ግጭትን ለመከላከል፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት እና ሰብአዊ ክብርን ለማጎልበት እ.ኤ.አ በ2013 የተቋቋመ በወጣቶች ላይ ያተኮረ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው።

ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር  227

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...