
በፍቅር አጋሩ ቀነኒ አዱኛ ግድያ ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኘው ድምጻዊ አንዱአለም ጎሳ በዛሬው ዕለት በአራዳ ምድብ ችሎት ለሦስተኛ ጊዜ የቀረበ ሲሆን፤ ፖሊስ በችሎቱ “የፌደራል ፖሊስ ፎረንሲክ የምርመራ ውጤቶቹ አሁንም አልደረሱኝም” በማለት 14 ቀን ተጨማሪ ቀናት ጠይቋል።
በዛሬው ዕለት በችሎቱ የፖሊስ የምርመራ ውጤት ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ የ15 ሰዎች መረጃ ማሰባሰቡን በመግለጽ፤ ነገር ግን ፎረንሲክ የምርመራ ውጤቶቹ ስላልደረሱት ተጨማሪ ቀናትን ጠይቋል።
የአንዱዓለም ጠበቃ በበኩሉ የቀነኒ ዲያሪ እሱ ጋር እንዳለ ጠቅሶ፤ ቀነኒ ሯሷን ለማጥፋት በተደጋጋሚ መድኃኒት ወስዳ እንደነበር ተፅፎ ማግኘቱን አስታውቋል።
“ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መፈቀድ የለበትም! አንዱዓለም የዋስ መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል” ብሎ ተከራክሯል።
በተጨማሪም “ከእስር ወጥቶ የሙዚቃ ስራውን ለፋሲካ ያቅርብ የሚለው የዩቲዩብ ዘገባ የተሳሳተ ነው ሊታረም ይገባል” ብሏል።
ፍርድ ቤት የሁለቱን ክርክር በመስማት የክርክሩን ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ማክሰኞ ጠዋት ቀጥሮ ሰጥቷል።