ቡድኑ ጥቃቱ “ሆን ተብሎ እና በግልፅ የታወቁ የዕርዳታ ሰራተኞች ላይ ያነጣጠረ” እንደነበር አረጋግጫለሁ ብሏል
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ ዕርዳታ ድርጅት ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ፣ እ.ኤ.አ. በ2021 በትግራይ ክልል ሶስት ባልደረቦቹ የተገደሉበትን አሰቃቂ ሁኔታ አስመልክቶ የሰራውን የውስጥ ግምገማ ይፋ አድርጓል።
ግምገማው ጥቃቱ “ሆን ተብሎ እና በግልፅ የታወቁ የዕርዳታ ሰራተኞች ላይ ያነጣጠረ” እንደነበር ያረጋገጠ ሲሆን፣ ቡድኑ ከአራት ዓመታት በኋላም ከኢትዮጵያ መንግስት አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ ጠቁሟል።
ሰኔ 24 ቀን 2021 ማሪያ ሄርናንዴዝ ማታስ (ስፔናዊት)፣ ቴድሮስ ገብረማርያም እና ዮሐንስ ሀለፎም (ሁለቱም ኢትዮጵያውያን) የተባሉ ሰራተኞቹ በማዕከላዊ ትግራይ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ በግልጽ ምልክት በተደረገበት ተሽከርካሪያቸው ውስጥ ተገድለዋል።
የቡድኑ የውስጥ ግምገማው በርካታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪዎች ሰራተኞቹ በተገደሉበት መንገድ ላይ በወቅቱ እንደነበሩ በግልፅ አረጋግጧል።
የመከላከያ ሰራዊት ተሳትፎ ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ እንዲሆን የጠየቀዉ ብድኑ ከዚህ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አሳሳቢ የምስክርነት ቃላትም መቀበሉን አስረድቷል።
የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ፕሬዝዳንት ፓውላ ጊል እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ቃል ቢገቡም፣ ከአራት ዓመት በኋላም ቢሆን ቡድኑንም ሆነ የሟቾቹ ቤተሰቦች ምንም ዓይነት አጥጋቢ መልስ አላገኙም። ጊል “የተጠናቀቀውን የምርመራ ውጤት ለመግለጽ በቂ የፖለቲካ ፍላጎት እንደሌለ ብቻ መገመት እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ቡድኑ ይህን ግምገማ ይፋ ያደረገው መንግስታት ሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎችን እና የሕክምና ተቋማትን እንዲከላከሉ እና ተጠያቂዎችም እንዲቀጡ ለመጠየቅ ነው።
ድርጅቱ በሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየጨመሩ መሆናቸውን እና መንግስታት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ ጥሰቶችን የመመርመር ግዴታቸውን ችላ እያሉ መሆኑን አሳስቧል።
CapitalNews
