
በትግራይ ክልል በግድየለሽነት እየተፈጸመ ያለው የስልጣን ወረራ የተናጠል ተግባር ሳይሆን፤ ትግራይን ለማተራመስ ሲጥር ከነበረው ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመቀናጀት የሚፈጸም ነው ሲሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲ ጥምረቶች ገለጹ።
በቅርቡ ጥምረት የመሠረቱትና በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት ውድብ ናፅነት ትግራይ፣ ባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ እና አረና ሉዓላዊ ትግራይ ፖርቲዎች፤ በክልሉ ያለውን ሕገ-ወጥ የስልጣን ነጠቃ እና የክልል አለመረጋጋትን ለመፍታት አስቸኳይ ጥሪ ያቀረቡበትን መግለጫ በትላንትናው ዕለት አውጥተዋል።
በመግለጫቸውም በክልሉ በአዲስ መልክ በተቋቋመው የክልል ጊዜያዊ ምክር ቤት ውስጥ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
“የእኛ ተልእኮ የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ እና በሁሉም የመንግሥት እርከኖች ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረግ ነው” ብለዋል።
“ነገር ግን የህወሓት ጄኔራሎች እና አጋሮቻቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ስልጣን ለመንጠቅ ሲሞክሩ፤ ትግራይ የከፋ ቀውስ ውስጥ ገብታለች” ሲሉም ገልጸዋል።
ይህ ሕገ-ወጥ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መንግሥታዊ መዋቅሮችን ከሥር እስከ ከፍተኛ እርከን በማፍረስ፤ ክልሉን ወደ ከፍተኛ አለመረጋጋት እንዲያመራ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቀዋል።
“ይህ በግዴለሽነት የሚፈጸም የስልጣን ወረራ የተናጠል ተግባር አይደለም። ትግራይን ለማተራመስ ሲጥር ከነበረው ከኤርትራ መንግሥት ጋር የተቀናጀ ነው” ያለው የጥምረቱ መግለጫ፤ የእነሱ ንቁ ተሳትፎ በምስራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን ውጥረት እያባባሰ መሆኑን ጠቁሟል።
ይህም ሰፊውን የቀጠናዊ ደህንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል አመላክቷል።
በዚህም መሠረት ዓለም አቀፍ አካላት እና ሁሉም የፕሪቶሪያ ስምምነት ዋስትና ሰጪዎች በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል።
ተጨማሪ ትርምስን ለማስቀረት እና አስከፊ ክልላዊ ቀውስን ለመከላከል የሕግ የበላይነት መከበር እንዳለበትም በመግለጫቸው አሳስበዋል።
እንዲሁም “የኤርትራን ጣልቃ ገብነት እና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ላይ አደጋ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ የውጭ አካላት ሚናን ለመግታት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ብለዋል።