በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን ስለ ድርድሩ ዝርዝር ጉዳዮች በቂ መረጃ አልወጣም።
የአሜሪካ እና ኢራን ተደራዳሪ ልዑካን በኢስላማባድ የፓኪስታን ባለሥልጣናትን ለማግኘት በተቃረቡበት በአሁኑ ሰዓት አራት ቁልፍ ጥያቄዎችን እንመልከት።
በንግግሩ ማን ይሳተፋል?
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አማች ከሆኑት ልዩ አማካሪ ጃሬድ ኩሽነር እና ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በመሆን ከኢራን ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ በፓኪስታን መዲና ኢስላማባድ ገብተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ቁልፍ የኢራን መንግሥት ባለሥልጣን ሆነው ብቅ ያሉት የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባጋር ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ከንግግሩ ቀደም ብለው ማምሻውን ኢስላማባድ ደርሰዋል።
የፓኪስታን ሚና ምንድን ነው?
ሁለቱም ወገኖች በፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር እና በአገሪቱ የወታደራዊ አዛዥ አሲም ሙኒር አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ፓኪስታን በሁለቱ ተፋላሚ አገራት መካከል ቁልፍ አደራዳሪ ሆናለች። ከወዲሁ ጥርጣሬ ውስጥ የወደቀው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስም ሚና ተጫውታለች።
ንግግሩ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል?
በአጭሩ ለመመለስ ንግግሩ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ግልፅ አይደለም። ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ቁርኝነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ንግግሩ አንድ ቀን ምን አልባትም እስከ ቅዳሜ ምሽት እንደሚካሄድ ዘግቧል።
የሚጠበቁ ቁልፍ የንግግሩ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
የድርድሩ ዋነኛ ነጥቦች፤ ኢራን በመዳፏ የጠረነፈችው የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ በሊባኖስ የቀጠለው ግጭት እና ኢራን ያከማቸችው የበለፀገ ዩራኒየምን ያካትታል።
