ኤም-ፔሳ (M-Pesa) በቅርቡ “በኢትዮ ቴሌኮም ቁጥሮች አገልግሎቴን እንዳይጠቀሙ እገዳ ተጥሎብኛል” ሲል ላቀረበው ቅሬታ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ምላሽ ሰጥተዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ድርጊቱን “ተገቢ ያልሆነ እና የኢትዮ ቴሌኮምን ስም ያጠፋ” ሲሉ ኮንነውታል።
📌 የውዝግቡ መነሻ ምን ነበር?
ህዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም ኤም-ፔሳ ባወጣው መግለጫ፣ “M-PESA ለሁሉም” የተሰኘ በማንኛውም ሲም ካርድ የሚሰራ የሞባይል ክፍያ ሥርዓት ማስተዋወቁን ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ በኢትዮ ቴሌኮም (09) ቁጥር ተመዝግበው መተግበሪያውን ለመጠቀም የሞከሩ ደንበኞች፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዳታ በመጠቀማቸው ብቻ አገልግሎቱ እንዳይሰራ ታግዷል ሲል ቅሬታውን አቅርቦ ነበር።
🛡️ የኢትዮ ቴሌኮም ምላሽና አቋም
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ለቀረበው ቅሬታ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዋና ዋና ነጥቦችም፦
- ”ከሥርዓት ውጪ የሆነ አሰራር”፦ የኤም-ፔሳ ድርጊት የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞችን እና ቁጥሮችን ያለፈቃድና ከኢንዱስትሪው አሰራር ውጪ ለመጠቀም መሞከር ነው ብለዋል።
2. “ኔትወርክ አልዘጋንም”፦ ተቋሙ ኔትወርክ እንዳልዘጋ ገልጸው፣ ይልቁንም የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች “አብዩዝ” (ያለፍላጎታቸው መጠቀሚያ እንዳይሆኑ) እንዳይደረጉና ተቋሙ የገነባው መሠረተ ልማት እንዳይወሰድ ጥበቃ ማድረጉን አስረድተዋል። - ”ይቅርታ ሊጠየቅ ይገባል”፦ ኤም-ፔሳ ያላደረግነውን አደረጋችሁ በማለት በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮ ቴሌኮምን ስም አጥፍቷል፤ ስለዚህ በቅድሚያ ይቅርታ ሊጠየቅ ይገባል ብለዋል።
4. “የህግ ተጠያቂነት”፦ ጉዳዩን በህግ ጭምር ለመጠየቅ እንደሚችሉ የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፣ ለብሄራዊ ባንክ፣ ለኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን እና ለኢንሳ (INSA) ጉዳዩን በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
”በሌላ ሀገር አንደኛው ኦፕሬተር የሌላኛውን ደንበኛ እንደፈለገ ወስዶ አገልግሎት አይሰጥም። ኢትዮ ቴሌኮም የገነባውን Snatch አድርጎ (ያለፈቃድ ቀምቶ) መውሰድ ከሥርዓት ውጪ ነው።” ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚዋ።
ወ/ሪት ፍሬህይወት የተቋማቸውን የመንፈቅ ዓመተት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ስለ ጉዳዩ በዝርዝር ያብራሩ ሲሆን ኢትዮ ቴሌኮም ለትብብር ዝግጁ መሆኑን፣ እንዲሁም ይህ ትብብር ግን በሁለቱ ተቋማት ስምምነት እና በሙያዊ ስነ-ምግባር ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ጉዳዩን የሚመለከታቸው የመንግስት ተቆጣጣሪ አካላት ማለትም ብሄራዊ ባንክ እና የኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን በሁለቱ ግዙፍ የቴሌኮም ተቋማት መካከል ባለው የገበያ ፉክክር እና አሰራር ላይ ውሳኔ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቅዳሜገበያ
