ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ ተጨማሪ መሬት በየዓመቱ ለቡና ልማት እየዋለ እንደሚገኝም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በሻይ እና በተለያዩ ቅመማ ቅመም ዓይነቶች ምርትና ምርታማነት ላይ በስፋት እየሠራ እንደሚገኝም ገለጸ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ዘንድሮ ወደ ውጭ ሀገር የላከችው ቡና በመጠንም ሆነ በገቢ አዲስ ሪከርድ ተመዝግቧል። ምርታማነት፣ ጥራትና ገበያን በማስፋፋት በተሠሩ ሥራዎች መሆኑን አመልክተዋል። ከ 200 ሺህ ሄክታር በላይ ተጨማሪ መሬት በየዓመቱ ለቡና ልማት እየዋለ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 326ሺህ ቶን ቡና ኤክስፖርት በማድረግ፤ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ፤ 469 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡ ገቢው ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር አብላጫ አለዉ ብለዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት 300ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፣ ቀደም ባሉት አመታት መንግሥት ከቡና ከ600 እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኝ ነበር።
ከለውጡ በፊት በዓመት ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና መጠን 200 ሺህ ቶን ነበር፤ አሁን ላይ ወደ 469 ሺህ ቶን አድጓል ፤ ገበያን ከማስፋፋት ጋር በተሠራው ሥራም የቡና መዳረሻ ሀገራት ቁጥር 66 መድረሱን አስታውቀዋል።
አርሶ አደሩ የቡና ምርቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የገበያ ትስስር ተደርጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በ2017 በጀት ዓመት አርሶ አደሮች ቡና ምርታቸውን በቀጥታ በዓለም ገበያ ላይ በማቅረብ 8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከእዚህ በፊት አርሶ አደሩ የቡና ምርቱን በማሳ ላይ ለመሸጥ ይገደድ እንደነበረ አስታውሰው፤ በተደረገው በግብርና ፖሊሲ ለውጥ አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በቀጥታ በዓለም ገበያ ላይ እያቀረቡ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
ቡና እንደ ሀገር ከሚገኘው የውጪ ንግድ ገቢ 40 በመቶ የሚሸፍን መሆኑን ጠቁመው ፤ በቀጣይ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የቡና ምርት እና ምርታማነት ላይ የተጠናከረ ሥራ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡
ቡና ጉንደላ፣ አዳዲስ ቡና በስፋት መትከልና ሌሎችም ሥራዎች በትኩረት ይሠራባቸዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከስድስት ዓመት በፊት ከአንድ ሄክታር ስድስት ኩንታል ቡና እንደሚሰበሰብ ጠቁመዋል። በተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ሄክታር ዘጠኝ ኩንታል ቡና ምርት ይገኛል።
የቡናን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ግብዓቶች፤ ቡና መትከያ ቦታዎች ማረሻና መጎንደያ መሣሪያዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ከጥራት ጋር በተያያዘም እንዴት መታጠብና ማድረቅ እንዳለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
