በጋምቤላ ክልል በአንድ ቀን ውስጥ ቢያንስ 47 ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ

Date:

በጋምቤላ ክልል በተቀሰቀሰ ግጭት በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ቢያንስ 47 ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ፤ ዓለምአቀፉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በዚያው ዕለት ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎችን ማከሙን አስታውቋል።

ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ታርፓም ንዑስ ከተማ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 47 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የጤና ባለሙያ እንደተናገሩት ከሆነ፣ “ይህ ቁጥር በመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊያሻቅብ ይችላል”።

“በሰማሁት መረጃ መሠረት 47 ሰዎች ሞተዋል” ያሉት ምንጩ፤ “በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ የተቃጠሉ አንዳንድ ሰለባዎች እስካሁን በሟቾች ቁጥር ውስጥ ሳይካተቱ ሊቀሩ እንደሚችሉ” አክለው ገልጸዋል። አክለውም “ነዋሪዎች አሁንም ሟቾችን እየቀበሩ ነው” ብለዋል።

“በቀጠለው የጸጥታ ችግር እና መንገዶች በመዘጋታቸው ምክንያት፣ በርካታ ቁስለኞች ጋምቤላ ከተማ በሚገኙ የሕክምና ተቋማት መድረስ አልቻሉም” ያሉት ግለሰቡ አያይዘውም “ወደ ጋምቤላ የሚመጡበት ምንም መንገድ የለም፤ መንገዱ አሁንም እንደተዘጋ ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም አንዳንድ ተጎጂዎች ጥቃቱ ከተፈጸመበት ቦታ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ወደሚገኘው የዓለምአቀፉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን የኩሌ የሕክምና ማዕከል መወሰዳቸውን የጤና ባለሙያው አክለው ገልጸዋል።

ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በበኩሉ ትናንት ታህሳስ 15/ 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ በጋምቤላ ክልል ያለው ግጭት ከትናንት ማለዳ ጀምሮ መጠናከሩንና ተቋሙ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎችን መቀበሉን አስታውቋል። ግጭቱ የሚቀጥል ከሆነ በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ ተጎጂዎች ሊመጡ እንደሚችሉም አስጠንቅቋል።

ተቋሙ እንደገለጸው ከሆነ፣ የተጎጂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው ለአንድ ሳምንት ያህል ዘልቆ በቆየው ግጭት ምክንያት ነው። በዚህም ታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ላይ በኩሌ ስደተኞች መጠለያ በሚገኘው ማዕከሉ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ መስጠት መጀመሩን ገልጿል።

በመጀመሪያዎቹ 48 ሰዓታት ውስጥ 19ኙ በጽኑ የቆሰሉትን ጨምሮ ወደ 50 ለሚጠጉ ሰዎች ሕክምና መስጠቱን ጠቅሶ ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ ደግሞ ከ150 በላይ የቆሰሉ ታካሚዎችን ማከሙን አስታውቋል።

የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የሕክምና አገልግሎት የማግኘት ዕድል በእጅጉ መስተጓጎሉን አስጠንቅቋል።

የውጭ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት ከአንድ ሳምንት በላይ ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፣ ታካሚዎችን ወደ ተሻለ ሕክምና የመላክ ሥርዓትም በመስተጓጎሉ ሊቀሩ የሚችሉ ሞቶች እንዳይከሰቱ ሥጋት መፍጠሩን ገልጿል።

ድርጅቱ የጤና ሚኒስቴር ለሚያደርገው ምላሽ ድጋፍ እንዲሆን ለጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ለጋምቤላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የአደጋ ጊዜ የሕክምና ቁሳቁሶችን እየላከ መሆኑንም አመልክቷል።

ሌላኛው የአካባቢው ምንጭ እንደገለፁት፤ ታህሳስ 15 ቀን ጥቃቱ የተፈጸመው በታርፓም ንዑስ ከተማ የመኖሪያ መንደር ውስጥ በሌሊት ነው። በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል ሴቶች፣ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙበት ምንጩ ገልፀዋል።

በተጨማሪም መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውንና ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የገለፁት እኚሁ ምንጭ፤ ጥቃቱ ከድንበር ተሻግረው ባሉ ግለሰቦች አማካኝነት የተቀናጀ ሳይሆን እንዳልቀረም ጠቁመዋል።

አንድ የአከባቢው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ጥቃቱ መፈፀሙን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል፤ ይሁን እንጂ ባለሥልጣናቱ እስካሁን የተረጋገጠ የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥር እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ጥቃቱ ከድንበር ማዶ በመጡ አካላት የተፈጸመ ነው የሚለውን መረጃ “ክስ” ሲሉ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ወደ ጋምቤላ ከተማ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና ሕክምና ፍለጋ የሚመጡ ሰዎች ጭምር መገደባቸውን አረጋግጠዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ስለደረሰው የጉዳት መጠንና ስለተከሰተው ግጭት ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል ጥረት ቢያደርግም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም።

የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ የፀጥታ ችግር በሚስተዋልባቸዉ የክልሉ አካባቢዎች ከትናንት ጀምሮ ከምሽት 2:00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን ማስታወቁ ይታወሳል።

የክልሉ መንግሥት ታኅሳስ 15/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በክልሉ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በተጠቀሰው ጊዜ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ የተሽከርካሪም ሆነ የሰው እንቅስቃሴ የተከለከለ መሆኑን ገልጿል።

መግለጫው ከተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ውጪ የትኛውም ቦታ ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም ገልጾ፣ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተጣሉ ክልከላዎችን በማክበርና በማስከበር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስቧል።

የአሁኑ ግጭት የተከሰተው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተፈጸሙ ተከታታይ ግድያዎችን ተከትሎ ነው። ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ታህሳስ 1 ቀን 2018 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ በተከፈተ ተኩስ ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ የአራት ሰዎች ሕይወት አልፏል። ይህንንም ተከትሎ የሌሊት የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሎ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በበኩሉ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ስደተኞችን ኢላማ በማድረግ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጨ ያለው ሀሰተኛ መረጃ አሳሳቢ መሆኑን ገልጾ፣ ሁኔታው በአስቸኳይ እልባት ካልተሰጠው ውጥረቱን ሊያባብስ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ኤጀንሲዉ ታኅሳስ 14/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ የአሳሳች ትርክት ስርጭት በስደተኞች እና በአስተናጋጅ ማኅበረሰቦች ላይ አደጋ እንደሚፈጥር በመጠቆም፣ ለሁኔታው ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ጥሪ አቅርቧል።

አክሎም እንዲህ ዓይነት ንግግሮች በንጹሐን ዜጎች ላይ አደጋ እንደሚፈጥሩና አብሮ የመኖር እሴትን እንደሚጎዱ የገለጸው መግለጫው፣ ሁሉም አካላት ከጥላቻ ንግግር እንዲታቀቡ አሳስቧል።

የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽኑ በሁኔታው መባባስ የምግብ እና የውሃ አቅርቦትን ጨምሮ አንዳንድ ሰብአዊ አገልግሎቶችን ለጊዜው ለማቋረጥ መገደዱን ገልጿል።

ስደተኞች ከሀገራቸው ጥቃት ሸሽተው ደህንነት ፍለጋ የመጡ በመሆናቸው፣ በጅምላ  ተጠያቂነት ሊፈረጁ አይገባም ሲልም አሳስቧል። ኤጀንሲው  የሲቪል እና ሰብአዊ ባህሪ ያለው ጥገኝነት “ለድርድር የማይቀርብ መርህ” መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።

ይህ  መግለጫ የወጣው፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በክልሉ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ መደፍረስ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የፌዴራል እና የክልል ባለሥልጣናት በአስቸኳይ በቂ የጸጥታ ኃይል እንዲያሰማሩ ጥሪ ባቀረበ ማግስት ነው።

ኮሚሽኑ ታኅሣሥ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡመድ ኡጁሉ መገደላቸውን ተከትሎ፣ በከተማዋና በአካባቢው ወረዳዎች የተቀሰቀሰውን ግጭትና የተኩስ ልውውጥ መከሰቱን አስታውቋል።

ኢሰመኮ፤ ከኅዳር 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በጋምቤላ ወረዳ (አቦል)፣ በጋምቤላ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭትና የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና ሥጋቶችን እየተከታተለ እንደሚገኝም ገልጿል።

በተከሰተው የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና የአካል ጉዳት መድረሱን፣ የሰዎችን እና የመጓጓዣ አማራጮችን እንቅስቃሴ የሚገድብ የሰዓት እላፊ በክልሉ መንግሥት መጣሉን፤ ባንኮችንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ማቋረጣቸውን መገንዘቡን አስታውቋል።

ኢሰመኮ በመግለጫው በተከሰተው የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና የአካል ጉዳት መድረሱን፣ የሰዎችን እና የመጓጓዣ አማራጮችን እንቅስቃሴ የሚገድብ የሰዓት እላፊ በክልሉ መንግሥት መጣሉን፤ ባንኮችንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ማቋረጣቸውን መገንዘቡን አስታውቋል።

መግለጫው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭትና የሰላም መደፍረስ በፍጥነት በማስቆም በሰዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር፣ የንብረት፣ የሥራ እንዲሁም ሌሎች ሰብአዊ መብቶች ላይ ተጨማሪ ጥሰቶች እንዳይደርሱ ለመከላከል በቂ የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ እንዲሰማሩ እንዲደረግ አሳስቧል።

በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ወደፊት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥታት ተገቢ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚገባም አስገንዝቧል። አስ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አዲስ አበባ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ...

የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የ5 በመቶ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ክፍያን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና...

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ለኢራን ህዝብ – “እኛ ከእናንተ ጋር ነን”

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ፥ የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ...

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና...