የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ አፈፃፀሙን መገምገሙን አስታውቋል፡፡ በዚህም የወቅታዊ ምዝገባ ሽፋን 90 በመቶ ለማድረስ የታቀደ ቢሆንም፣ ከዕድሮች፣ ከሀይማኖት ተቋማት እና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር በተደረገ ቅንጅታዊ ሥራ ከእቅድ በላይ 99 በመቶ አፈፃፀም መመዝገቡን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሴ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ስድስት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና አፈፃፀሞች የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በተመለከተ 236ሺ874 ልደት ምዝገባ ተደርጓል።41ሺ194 ህፃናት እንደተወለዱ የተመዘገቡ ሲሆን 13ሺ974 ህፃናት በተወለዱ በ90 ቀናት እንዲሁም 101ሺ519 ህፃናት ትምህርት ቤቶች ላይ በተደረገ ንቅናቄ የተመዘገበ መሆኑን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ21 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
19ሺ 800 ጋብቻ ምዝገባ የተደረገ ሲሆን 5ሺ444 በወቅቱ፣1ሺ738 በአንድ ዓመት ውስጥ ተከስተው የተመዘገቡ ናቸው። በተጨማሪም 12 ሺ618 የጊዜ ገደቡ ባለፈ የተመዘገበ ጋብቻ ሲሆን 655 የሚሆነው በሸሪዓ ፍርድ ቤት ቅርንጫፍ የተመዘገበ ወቅታዊ ጋብቻ ነው ብለዋል።ባለፉት ስድስት ወራት 182 ጉዲፈቻ ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን 99 በወቅታዊ፣51 የጊዜ ገደቡ ባለፈ እንዲሁም 19 በዘገየ የተመዘገቡ ናቸው ፡፡
የወቅታዊ የኩነት ምዝገባ አፈፃፀም 90 በመቶ ማከናወን ተችሏል። በዘገየ የኩነት ምዝገባ ደግሞ 78 በመቶ ፣የግዜ ገደቡ ባለፈበት 136 በመቶ ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ የተመዘገበው ምዝገባ ከ2017ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር ወቅታዊ ልደት 31በመቶ ጭማሪ እንዲሁም ጋብቻ 10 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አቶ ዮሴፍ ንጉሴ ለብስራት ሬዲዮ ጨምረው ተናግረዋል።
