የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ታኅሣሥ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ባከናወነው የዓመት መጨረሻ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ፣ የአንድ የአሜሪካ ዶላር የጨረታ አማካይ ዋጋ 154.47 የኢትዮጵያ ብር መሆኑን አስታውቋል።
ባንኩ 150 ሚሊዮን ዶላር ባቀረበበት በዚህ ልዩ ጨረታ ላይ በአጠቃላይ 23 የንግድ ባንኮች ተሳታፊ በመሆን የውጭ ምንዛሬ ማሸነፍ ችለዋል።
ይህ ውጤት ካለፈው የጨረታ አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ልዩነት አሳይቷል። ባንኩ ታኅሣሥ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው 12ኛው ዙር ጨረታ የአንድ ዶላር አማካይ ዋጋ 154.7747 ብር ነበረ። ከዛሬው ውጤት ጋር ሲነጻጸር የዶላር ምንዛሬ በ0.19 በመቶ (0.29 ሳንቲም) ገደማ ቅናሽ አሳይቷል።
50 ሚሊዮን ዶላር በቀረበበት እና ከ 11 ቀን በፊት ብሔራዊ ባንክ ባደረገዉ በዚህ ጨረታ የውጭ ምንዛሬ አግኝተው የነበሩት ባንኮች ቁጥር 13 ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በዛሬው ልዩ ጨረታ ግን ቁጥራቸው ወደ 23 ከፍ ብሏል።
ይህ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የተካሄደው የዓመቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ሲሆን፣ በገበያው ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ለማርካት እና የምንዛሬ ተመኑን ለማረጋጋት ያለመ መሆኑ ተመልክቷል። ባንኩ ቀጣይ ጨረታዎችንም አስቀድሞ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚያከናውን ገልጿል።
