ትራምፕ እንደተናገሩት “ይህ ነዳጅ ዘይት በገበያ ዋጋ ይሸጣል፣ ገንዘቡንም እኔው ራሴ አስተዳድረዋለሁ” ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ትሩዝ ሶሻል” በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ እንደገለጹት፤ የቬንዙዌላ ባለስልጣናት ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ለአሜሪካ ለማስረከብ ተስማምተዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፣ እነዚህን የነዳጅ የዘይት በርሜሎች በመሸጥ የሚገኘው ገንዘብ በአሜሪካ እጅ ይቆያል።
ትራምፕ ሲጽፉም፦ “የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ባለስልጣናት ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ከፍተኛ ጥራት ያለውና ማዕቀብ ተጥሎበት የነበረ የነዳጅ ዘይት ለአሜሪካ ለማስረከብ መስማማታቸውን ስገልጽ በደስታ ነው። ይህ በገበያ ዋጋ የሚሸጥ ሲሆን፣ ገንዘቡ ለቬንዙዌላ እና ለአሜሪካ ህዝቦች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ እኔው ራሴ እንደ አሜሪካ ፕሬዝዳንትነቴ አስተዳድረዋለሁ” ብለዋል።
አክለውም የኢነርጂ ሚኒስትሩ ክሪስ ራይት ይህንን እቅድ እንዲያስፈጽሙ መመደባቸውን ገልጸዋል።
”ነዳጅ ዘይቱ በማከማቻ መርከቦች ተጭኖ በቀጥታ ወደ አሜሪካ የማውረጃ ወደቦች ይደርሳል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
