ተመስገን ገብሬ

Date:

ዓይናለም ደበበ

ተመስገን ገብሬ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በደብረ ማርቆስ ከተማ ፍቅርና ሰላም ከሰፈነባት ፣ ቸርነትና ምህረት ከሞላባት አንዲት ደሳሳ ጎጆ ግንቦት 15 ቀን 1901 ዓ.ም ተወለደ። በዚያን ግዜ በነበረው ልማድ አንድ ህፃን በተወለደ በአራት ዓመት ከአራት ወር በአራተኛው ቀኑ ላይ ትምህርቱን መከታተል ቢጀምር ስኬታማ ይሆናል ተብሎ ይታመን ስለነበር አባቱ ብላታ ገብሬም ይህችን ቀን ቆጥረው በዚያው በደብረ ማርቆስ ከተማ ርዕሰ ደብር ፀጋ ከተባሉ ሰው ጋር ከቤተክህነት በመውሰድ ትምህርቱን መከታተል እንዲጀምር አደረጉ። ህፃኑ ተመስገንም በአስደናቂ የትምህርት አቀባበል ትምህርቱን መማር ያዘ።

‹‹ሕይወቴ›› በሚል ስያሜ በራሱ በተመስገን ገብሬ በተፃፈውና በሲስተር ክብረ ተመስገን አማካኝነት ታትሞ ለሕዝብ በደረሰው ድንቅ ግለ ታሪክ መፅሐፍ ላይም ስለ ተመስገን ትምህርት አቀባበል እንዲህ ሰፍሯል። ‹‹የደብረ ማርቆስ ሰዎች ሁሉ እንደተደነቁበት በትምህርት የነበረኝ ስጦታ እጅግ ትንግርት ነበር። የተሰጠኝን የሕፃንነት አስተዋይ አእምሮ በማድነቅ መምህራችን ለብቻው አንድ ስም ሰጠኝና ኩዛ አለኝ›› ሲል ይገልጻል። ስያሜው የተሰጠው በተቸረው ብልህ አእምሮው አማካኝነት መሆኑንም ያስረዳል። ተመስገን በዚያ የሚሰጠውን ትምህርት በጥሩ ሁኔታ ካጠናቀቀ በኋላ ትምህርቱን ለመቀጠል ቢፈልግም በግዜው ቀጣይ ትምህርት የሚሰጥበት ትምህርት ቤት በደብረ ማርቆስ ከተማ ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ሌላ ሀገር እንዲሰዱት አባቱን መጠየቅ ግድ ብሎት አንድ ቀን ቢጠይቃቸው:- ‹‹ከእኛ ልትለይና ወደ ሌላ ሀገር ልንልክህ እድሜህ አይፈቅድም›› ሲሉ በመከልከላቸው እውቀት የተጠማው ህፃኑ ተመስገን የአባቱን ፍቃድ ወደ ጎን በማለት እንደርሱ ያሉ ለመማር የጓጉ አያሌ የመንደር ልጆችን አስተባብሮ በምሽት በመጥፋት በጥንታዊው ገበያ በየጁቤ አድርገው ከብዙ መከራና ረዥም ጉዞ በኋላ ትምህርታቸውን ከሚከታተሉበት ጉበን ገቡ። ግና በዚያ ትምህርታቸውን መከታተል እንደጀመሩ አንበጣ ባገሩ ላይ ተከስቶ የተዘራውን አዝመራ ሁሉ ክፉኛ ጎድቶት ነበርና ተመስገንና ጓደኞቹ ከፍተኛ ረሃብና ችግር ላይ ወደቁ።

በዚህም ከደብረ ማርቆስ ከተማ በአንድነት ሆነው የመጡት ባልንጀሮቹ ተስፋ ቆርጠው ትምህርታቸውን በማቋረጥ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ ሲገደዱ፣ ላያስችል አይሰጥምና ተመስገን ግን በህፃንነቱ ያደረበት የመማር ፍቅር መከራና ችግርን እንዲቋቋም አስችሎት ትምህርቱን ቀጠለ። ይህንንም ሲያብራራ:- ‹‹…ማለዳ ከእንቅልፌ በነቃሁ ግዜ ከስድስት ባልንጀሮቼ ዓለሙ የተባለው ብቻ አብሮኝ ሲቀር የቀሩትን ሁሉ ከአልጋቸው ላይ አጣኋቸው። ከወላጆቻቸው በሌት ጠፍተው እንደመጡ እንዲሁ ደግሞ ከእኔ በሌት ጠፍተው ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ ተመልሰው ሄዱ። በዚያ ተስፋ በሚያስቆርጠው ረሃብ እንኳ ትምህርቴን በፅናት እንድቀጥል የሚረዳኝ ጠንካራ ልብ ነበረኝ። ብረት ልብ እንዳለኝ ባልንጀሮቼ ያውቁ ነበርና እንመለስ ብለው አላማከሩኝም ነበር››  በማለት ተመስገን ሁኔታውን በግለ ታሪኩ ላይ ገልጿል። ታድያ በእንዲህ ባለ መንገላታት ውስጥ ሆኖ ወደ ጉበን የመጣበትን ዓላማ ፈፅሞ ሲያበቃ ደብረ ማርቆስ ከተማ ከቤተሰቦቹ ዘንዳ ተመለሰ። ከዚያም በኋላ ቅኔ የመማር ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ቢያድርበት የርሱንና የመሰሎቹን የእውቀት ጥማት ለማርካት ታልሞ እዛው ደብረ ማርቆስ ከተማ በእውቁ ሊቅ በርዕሰ ደብር ኑሬ በተቋቋመው አዲስ የቅኔ ትምህርት ቤት ቅኔ መማር ጀመረ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የጀመረውን የቅኔ ትምህርት እየተከታተለ ትንሽ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ሞጣ አቅንቶም በዚያ የቅኔ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ገና በልጅነቱ በልቡ ባደረበት የመማር ፍላጎት ተምሮ አልጠገበም ነበርና ቅኔ ተምሮ እንደጨረሰ እንደገናም ፍትሐ ነገሥትን በዚያው በሞጣ ጀምሮ ቢቡኝ ከተባለ ወረዳ ከሚገኝ ትምህርት ቤት ተምሮ አጠናቀቀ።

በዚያን ግዜ እውቀት የሚገበየው እንደዛሬው ዘመን ለመማር ማስተማር ሂደት በጀት ተመድቦ አልነበረምና ተማሪ ትምህርቱን ለመከታተል ከፍተኛ ስቃይና መከራ ላይ ይወድቅ ነበር። በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ አያሌ ተማሪ ይወድቅ ነበር። ልጁን ተማሪ ቤት ልኮ ተምሮ ይመጣልኛል እያለ ሲጠባበቅ ልጁ የውሃ ሽታ ሆኖ የሚቀርበት ወላጅ ቁጥርም የትየለሌ ነበር።

‹‹ተማሪ በሞተ በሰባት ዓመቱ፣

ተምሮ ይመጣል ትላለች እናቱ›› የተባለውም በዚያን ግዜ ነበር።

ተመስገን ግን እድሉ የተቃና ሆኖ ካገር ሀገር እየዞረ በተማረባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ የገጠመውን እልህ አስጨራሽ የህይወት ፈተና ተቋቁሞ ውጥኑን አሳካ። በዚህ ሁኔታ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም በጎጃም ክፍለ ሀገር ከራስ ኃይሉ ዘንዳ የፍትሕ አገልግሎት አካል በመሆን በፅህፈት ስራ በአፍላ የወጣትነት እድሜው ላይ ስራ ጀመረ።

መቼም ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከመሬት ነውና ለዚህ ዓለም ያልተገባ ድሎት ከማድላት ከህሊና ጋራ መከራን መጋራት የሚመርጠው ተመስገን በስራው ላይ ውሎ ሲያድር ቀድሞ በነበረው በተለመደው አሰራር ደስተኛ ሊሆን አልቻለም ነበር። ባለጉዳይ ሲንገላታ፣ ድሃ አለቅጥ ሲበደል፣ ሹመኞች የደሃውን መከራና ስቃይ ወደጎን በማለት በመከራ ላይ መከራ በስቃይ ላይ ስቃይ ሲደርቡበት ሲያይ በተለመደው ብልሹ አሰራር ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አደረበት። የሹመኞችንና የጭፍሮቻቸውን ገደብ አልባ ጭካኔንና ራስ ወዳድነትንም አጥብቆ መኮነን ያዘ። ‹‹ተሹሞ ያልበላ ተጠንስሶ ያልፈላ፣ ሹሙም ሹም ጥንስሱም ጥንስስ አይደለም›› በሚለው የግዜው የአደባባይ ንግግርም በእጅጉ አፈረ። ቢሆንም ግን የያዘው ዓላማና ያነገበው ሃሳብ በተቆረቆረለት ሕዝብም ሆነ በሹመኞች ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ ከመሆኑ አልፎ ለህይወቱ የሚያሰጋ አደገኛ ጎዳና ላይ መገኘቱን ባወቀ ግዜ ለግዜውም ቢሆን ህይወቱን ለማቆየት ወደደ። በጎ ሃሳቡ ካስከተለበት መከራና እንግልት በኋላም ከራስ ኃይሉ ቤት ለመሰናበት ወሰነ። በዚህ ግዜ እድሜው አስራ ስምንት ዓመት ደርሶ ነበር። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በንግዱ ዓለም ጥቂት ወራትን ቢያሳልፍም ለርሱ ጠባይ የተመቸ ስራ አልነበረምና ስራውን ትቶ ስራ አጥ ሆኖ በችግር ረዥም ግዜን አሳለፈ።

ግዜው አውሮፓውያኑ ክፉ ፍላጎታቸውን ባገኙት ቀዳዳ አሾልከው ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ ያለኃፍረት በፊት ለፊት የሚራኮቱበት ግዜ ነበር። ተመስገን ከህፃንነት እድሜው አንስቶ በገበየው እውቀትና ባሳለፈው የህይወት ውጣ ውረድ በፅኑ መሰረት ላይ የተቀመጠ ዓላማና ንፁህ ህሊና የተቸረው እንደመሆኑ ለሀገር ምንም አይነት ጥቅም የማይሰጥ ‹‹ተልካሻ›› ስራን እንኳን ለመስራት እንዲህ ያለውን ስራ ስራ ብለው በሚቋቋሙት ተቋማት እንዲሁም በግልጽም ይሁን በስውር፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሀገር ስትጠፋ፣ የጠላት ሀሳብና ፍላጎት ሲሰፍን በዝምታቸው በሚተባበሩት ሹማምንት በእጅጉ ይብከነከን ነበር። በዚህም ያገኘውን ስራ ሁሉ ከመቀበል ሆዱን ንቆ ከህሊናው እያደረ ገሸሽ በማድረግ ረዥም ግዜን ስራ አጥ ሆኖ በችግር አሳለፈ።

ከዚህ ተቆርቋሪነቱ የተነሳም በሃይማኖትና በቋንቋ እያመካኙ የሚያለሙ መስለው ሀገር የሚያጠፋትን ሚስዮኖችን ከነችግሩ በመጋፈጥ ለማስቆም አስቦ የሀገር ፍቅር ማህበርን በመወጠን በየአደባባዩ ስለ ሀገር ፍቅር ማስተማር ጀመረ። በዚህም የብዙሃኑን ትኩረት ማግኘት ችሎ ከቀን ቀን ዝናው እየናኘ ሄደ። በቆመበት መድረክ ሁሉ በሚያሰማቸው ስብከቶች የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ልብ በሀገር ፍቅር ስሜት አነደደ። ታድያ በዚህ ሁኔታ የሕዝቡን ልብ በማሸፈቱ የተደናገጡት መሳፍንቱና መኳንንቱ ያሴሩበት ያዙ። በሀገሩ ፍቅር ተቃጥሎ ሀገሩ ላይ በሚሰራው ደባ ተንገብግቦ ኢትዮጵያ ከታሪኳና ከሊቃውንቶቿ እውቀት እንዲሁም ከጠቢቦቿ የጥበብ አሻራ እንዳትቋደስ ከእጇ እየጎረሱ የሚነክሷትን፣ ከርሷ ተጠግተው ጋሬጣ እየሆኑባት የሚጋርዷትን፣ ጉድጓድ እየማሱ የሚያደናቅፏትን፣ ጦር እየሳሉ የሚወጓትን ጠላቶቿን ቢያወግዝ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ ቅር ተሰኙ። ከቅሬታም አልፈው ተመስገን የግል በደሉንና ችግሩን ንቆ የሚሰብከውን የሀገር ፍቅር እነርሱ ከስልጣናቸውና ከሆዳቸው አነፃፅረው በዛቻና ማስፈራሪያ ቀየሩት።

ያላለውን ብለሀል ያልሆነውን ሆነሀል እያሉ፣ ያላየውን አይተሀል ያልሰማውን ሰምተሀል እያሉ ወነጀሉት። ከመሰል ጓዶቹ ጋር ስለሀገሩ ለበጎ የዘራው እውን ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን ክፉ እንዳበቀለ ክፉ ገበሬ ኮነኑት። አስኮነኑት። እዚህና እዚያ በተንከራተተባቸው የውጪ ተቋማት ቀድሞ የደረሰበትን ያገኘውን የነርሱን ክፋት ለሕዝቡ ቢያሳውቅ፣ አደጋውን ለመቋቋም እንዲያስችል ባንድነት መቆም እንደሚገባ ቢያስጠነቅቅ፣ ክብሩን የማያስነካ፣ ሀገሩን የማያስደፍር ዜጋን ለማፍራት በየአደባባዩ እየዞረ ቀደምት ኢትዮጵያውያን የሰሩትን ታሪክ እያጣቀሰ ስለ ሀገር ፍቅር ቢያስተምር ከክህደት ቆጠሩበት ።

ይቀጥላል…

በቸር ያቆየን!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...