
በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው አራት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ሌሎች 19 ተከሳሾች፤ ጉዳያቸው የሚመለከተውን ችሎት በሰብሳቢነት የሚመሩት ዳኛ ከቦታቸው እንዲነሱ ጥያቄ አቀረቡ። የተከሳሾችን አቤቱታ በጽሁፍ የተቀበለው ፍርድ ቤቱ፤ አቤቱታውን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ለዕለቱ አሳድሮት የነበረው አንዱ ጉዳይ፤ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች “ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ወይስ አይገባም” በሚል ከዚህ ቀደም በተደረገው ክርክር ላይ ብያኔ መስጠት ነበር። ዐቃቤ ህግ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ክስ ላቀረበባቸው 51 ተከሳሾች የቆጠራቸው ምስክሮች ብዛት 96 ነው። ምስክሮቹ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ የምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡ መሆኑ በዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል ሃያ ስምንቱ ክሱ የቀረበባቸው በሌሉበት መሆኑን ያስታወሰው ችሎቱ፤ ለምስክሮች የሚደረግ ጥበቃን በተመለከተ በተደረገው ክርክር ላይ “ተከሳሾች ተሟልተው ሲቀርቡ ብይን እንሰጥበታለን” ሲል በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ ቀርቷል። ፍርድ ቤቱ ለዕለቱ ቀጠሮ ከሰጠባቸው ጉዳዮች ሌላኛው፤ ያልተያዙ ተከሳሾችን የፌደራል ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ የሰጠውን ትዕዛዝ በተመለከተ ፖሊስ የሚሰጠውን ምላሽ ማድመጥ ነበር። ፍርድ ቤቱ ባለፈው የችሎት ውሎ ያስተላለፈው ይህ ትዕዛዝ ዘግይቶ እንደደረሰው የገለጸው ፌደራል ፖሊስ፤ “በቀጣይ ለማቅረብ እንድንችል ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን” ሲል ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ ይህን የፖሊስን አቤቱታ ተቀብሎ፤ የተከሳሾችን አቤቱታ ወደ መስማት ተሻግሯል።
ተከሳሾች አቤቱታቸውን በአንደኛ ተከሳሽ በኩል ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ እንዲያቀርቡ ቢፈቀድላቸውም፤ ተከሳሹ የጉዳዩን ጭብጥ ከአንድ አንቀጽ በላይ ማንበብ ሳይችሉ ቀርተዋል። የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት አቶ ረቡማ ተፈራ ከዳኝነት እንዲነሱ የሚጠይቀው የተከሳሾች አቤቱታ በሁለት ገጽ የተዘጋጀ ነበር። በዶ/ር ወንድወሰን መቅረብ ጀምሮ የነበረውን አቤቱታ ያቋረጡት ሰብሳቢ ዳኛው፤ “ይሄን አንሰማም። አቤቱታችሁን በጽሁፍ አቅርቡ” ሲሉ ለተከሳሾቹ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ዶ/ር ወንድወሰን “በችሎት እንዲነሱልን የምንጠይቀው እርስዎን ነው። ምክንያታችንን ቤተሰቦቻችን እና ሚዲያ እንዲሰማ እንፈልጋለን” ሲሉ ለዳኛው ትዕዛዝ ምላሽ ሰጥተዋል። የችሎቱ የግራ ዳኛ፤ በሰብሳቢ ዳኛው እና በዶ/ር ወንድወሰን ሙግት መሃል ጣልቃ ገብተው “አቤቱታው በጽሁፍ ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ ይቅረብ” ሲሉ ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ሆኖም አንድ ተከሳሽ፤ “ቅሬታ የቀረበባቸው የመሃል ዳኛ ሊያቋርጡን አይገባም” ሲሉ የተከሳሾች አቤቱታ ሙሉ ይዘት ሊደመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህ በተከሳሾች እና በዳኞች መካከል የነበረው የቃላት ምልልስ፤ ለደቂቃዎች ያለማቋረጥ ቀጥሏል። በመጨረሻም የግራ ዳኛው “ጥያቄያችሁ፣ አቤቱታችሁ በጽሁፍ መቅረብ አለበት። የምንቀበለው በጽሁፍ ሲቀርብ ነው። በቃል እንዲቀርብ አንፈቅድም” ሲሉ ችሎቱ የተከሳሾች አቤቱታ በንባብ እንዲቀርብ እንደማይፈቅድ በአጽንኦት አስገንዝበዋል። እርሳቸው ይህን ቢሉም ተከሳሾች የመናገር ዕድል ሳይጠይቁ፤ የችሎቱን ውሳኔ የሚቃወሙ ንግግሮችን አድርገዋል።
ከተከሳሾች መካከል አንዷ የሆነችው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዋ መስከረም አበራ፤ “በጣም ትንሹን የመናገር መብት ነው እየጠየቅን ያለነው” ስትል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቃውማለች። ሌሎች ሁለት ተከሳሾች በበኩላቸው “የታሰሩት ወንጀል ሰርተው ሳይሆን በማንነታቸው ምክንያት እንደሆነ” ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። ተከሳሾች ቅሬታቸውን እየገለጹ ባለበት ወቅት፤ በጽሁፍ ያዘጋጁትን አቤቱታም በችሎት አስተናባሪ በኩል ለዳኞች ሰጥተዋል። የተከሳሾች አቤቱታ፤ ችሎቱን በሰብሳቢነት የሚመሩት ዳኛ “በገለልተኝነት እና በፍትሃዊነት ጉዳዮን ያዩታል” የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለጹበት ነው። ተከሳሾች ለዚህ አቤቱታቸው በምክንያትነት የጠቀሱት ዳኛው “አማራ ጠል ናቸው” የሚል ነው። ለዚህ ማሳያ ይሆናል በሚልም፤ ዳኛው “በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው አጋርተዋቸዋል” ያሏቸውን መልዕክቶች ቅጂ ከአቤቱታቸው ጋር በአባሪነት አያይዘዋል።
ተከሳሾች ይህንን የጽሁፍ አቤቱታቸውን በንግግር ለማቅረብ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፤ ችሎቱ አቤቱታውን በጽሁፍ ተቀብሎ “ተገቢውን ትዕዛዝ” እንደሚሰጥ በመግለጽ በድጋሚ ሳይቀበለው ቀርቷል። ከዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ ተከሳሾች የችሎቱን ውሳኔው የሚቃወም ቅሬታ ማቅረብ በመቀጠላቸው፤ የግራ ዳኛው “ችሎቱን ለማቋረጥ እንገደዳለን” በሚል ወደ ትዕዛዝ እና ተለዋጭ ቀጠሮ ወደ መስጠት ገብተዋል። በዚህም መሰረት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ የፌደራል ፖሊስ ያልተያዙ ተከሳሾችን በአድራሻቸው ተከታትሎ ለቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም የችሎቱን ሰብሳቢ ዳኛ በሚመለከት ተከሳሾች ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት፤ ፍርድ ቤቱ ለሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 15፤ 2016 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
‹‹ከለውጡ ብዙ የጠበቅናቸው ግን ደግሞ ምላሽ ያላገኘንባቸው ችግሮችና ስሜቶች ይኖራሉ››
አቶ ደመቀ መኮንን
የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተባባሰ የመጣውን የፀጥታ ችግር አስመልክተው በማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ‹‹ከለውጡ ብዙ የጠበቅናቸው ግን ደግሞ ምላሽ ያላገኘንባቸው ያላረኩንና ሌሎች ችግሮችና ስሜቶች ይኖራሉ›› ያሉ ሲኾን፣ ‹‹ለእነዚህ ጉዳዮች ቆም ብለን በማሰብ በሰላሙ መንገድ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው›› ሲሉም መክረዋል። በመሠረቱ ብዙ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ይኖራሉ ያሉት አቶ ደመቀ፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን ጠቃሚው መንገድ ሰላማዊና የውይይት አግባብ ነው ሲሉ መክረዋል። ‹‹ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ›› እንደ አቶ ደመቀ አገላለፅ፦ የጥያቄዎችን መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ፣ ያለንን የሚያሳጣ እና በዘላቂነት ሊታዩ ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ አካሄድ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ አቶ ደመቀ ይኽንን መልዕክታቸውን ከማስተላለፋቸው አስቀድሞ ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ‹‹የጸጥታ አካላት በክልሉ ሕግን ለማስከበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ህዝቡ ድጋፍ በማድረግ የተለመደ ትብብሩን ያሳይ›› ሲሉ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ጥሪያቸው በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ሰላማዊውን ሕዝብ በማወክና መንገድ በመዝጋት ችግር የሚፈጥሩ አካላት የክልሉን ልማትና የሕዝቡን አንድነት እየጎዱ በመሆናቸው ከእዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል። የአገር መከላከያ ሠራዊት ሕግን ለማስከበር ወደ ተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የሚደረግ ትንኮሳ መቆም እንዳለበት የገለጹት ዶክተር ይልቃል፤ መላው የክልሉ ሕዝብም ለሠራዊቱ ድጋፍ በማድረግ የተለመደ ትብብሩን እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይ ከቀናት በፊት መግለጫ ሰጥቶ የነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በበኩሉ ‹‹በፋኖ ሥም እየተንቀሳቀሱ የአገር ሰላም ለማወክ በሚሰሩ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል›› ሲል አስታውቆ ነበር፡፡ መግለጫውን የሰጡት የሰራዊቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፤ ‹‹ሃሳብ ሲነጥፍ ነፍጥ አንግቤ እዋጋለሁ” የሚል አካል ላይ ሰራዊቱ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ገልጸዋል። ሰራዊቱን መቋቋም ያልቻሉ አካላት በሰራዊቱ ላይ ሰፊ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ላይ እንደሚገኝ ኮሎኔል ጌትነት ተናግረዋል። በተለይ አሁን ላይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ፤ በኦሮሚያ ክልል ሸኔ የመደምሰስ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።