Aኬሮግራፈር ተመስገን መለሠ (ልጅ ተመስገን) 17 ብሔር ብሔረሰቦችን የዳሰሰ አዲስ የሙዚቃ አልበም ለአድማጮች ሊቀርብ እንደሆነ እውቁ ብሏል።
በዳንስ ጥበብ ዘርፍ “የተመስገን ልጆች” የተሰኘውን ቡድን በማቋቋምና በቅርቡም “ንህነ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በማብቃት የሚታወቀው ባለሙያው፤ አሁን ደግሞ በሙዚቃው ዘርፍ አዲስ ፈጠራ ይዞ ብቅ ብሏል።
በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለለት ይህ “ኢቲዲኤም ቢትስ” አልበም፣ የኢትዮጵያን የተለያዩ ባህላዊ የሙዚቃ ቅኝቶች ከዘመናዊ የሙዚቃ ዘውጎች ጋር በማዋሃድ የተሰራ ነው።
አልበሙ በአጠቃላይ የ17 ብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ ሙዚቃዎች ከዘመናዊ ቢቶች ጋር አቀናጅቶ የያዘ ሲሆን፣ በውስጡም 13 የተለያዩ ትራኮችን አካትቷል።
ከእነዚህም መካከል ለሁለቱ ሙዚቃዎች የቪዲዮ ስራቸውን ማጠናቀቁ ታውቋል።በሙዚቃ ቪዲዮ አዘጋጅነት ሰው መሆን ይስማው ተሳትፏል።
የአልበሙ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን እምቅ የባህል የሙዚቃ ሀብት ለዓለም አቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ማስተዋወቅና የባህል ውክልናን ማሳየት እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ አልበም በመጪው አርብ ጥር 8 ቀን 2018 ዓ.ም በሁሉም የሙዚቃ ማሰራጫዎች ለሙዚቃ አድማጮች እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
