የአባታቸውን መገደል ተከትሎ የኢራን ጠቅላይ መሪ የሆኑት ሞጅታባ ኻሜኒ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁን ተከትሎ ሞተዋል እየተባለ የሚናፈሰውን ወሬ እንደማያምኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
በቀጥታ በተደረገ የስልክ ቃለ ምልልስ ላይ ሞጅታባ “ሞቷል ብዬ አላስብም” ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ኢራኑ መሪ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ግን ጠቁመዋል።
“የሰውነቱ ግራ ክፍል፣ እጁ፣ እግሩ ሁሉ በጣም ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። ግን ሞቷል ብዬ አላስብም” ብለዋል።
ሞጅታባ ሞተው ከሆነ ኢራን ባለሥልጣናት የሚያደርጉት ሁሌ በሕይወት እንዳሉ የማስመሰል ነው፤ ነገር ግን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንደሚያማክሯቸው እና ውሳኔያቸውን እንደሚቀበሉ ትራምፕ ጠቅሰዋል።
ጨምረውም ከአሜሪካ ጋር ድርድር ሲያደርጉ የነበሩት የቴህራን ተደራዳሪዎች ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸውን በመግለጽ፣ ኢራን ውስጥ ማንኛውም ነገር የሚከሰትበት ዕድል እንዳለ ተናግረዋል።
ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ስለማሸነፍ ያላቸውን ተስፋ በተመለከተ የተጠየቁት ትራምፕ፣ “ያለን የገንዘብ አቅም ከፍተኛ ነው፤ እናም ይህ ወደ ታላቅ ድል ይመራናል” ብለዋል።
የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት በኢራን ላይ ያለውን ማዕቀብ ለማጠናከር አዲስ ዘመቻ መጀመሩን አስታውቋል።
ኢራን ላይ መጠነ ሰፊ የምጣኔ ሀብት ጫና በመፍጠር መንግሥቱን ለመጣል የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተነግሯል።
አሜሪካ በወታደራዊ እርምጃ ይልቅ፣ ኢራን ላይ የምጣኔ ሀብት ዘመቻን ወደማጠናከር አዘንብላለች። ከቴህራን ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት ትስስራቸውን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ካልሆኑ ኢኮኖሚያዊ ቅጣቶች እንደሚጠብቋቸው አስጠንቅቃለች።
BBC
