በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ መካከል በፍሎሪዳ በሚገኘው የማር-አ-ላጎ መኖሪያ የተካሄደው ስብሰባ በሰላም ድርድሩ ላይ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን በሚያበስሩ መልዕክቶች ተጠናቋል።
ሁለቱ መሪዎች ከንግግሩ በኋላ ወዲያውኑ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፥ የሰላም ስምምነቱ ከምንጊዜውም በላይ መቃረቡን አፅንዖት ሰጥተዋል።
አስቸጋሪ ጥያቄዎች
ትራምፕ ድርድሩ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ቢናገሩም፣ ገና ያልተፈቱ “አንድ ወይም ሁለት በጣም አስቸጋሪ እና ስሱ ጉዳዮች” መኖራቸውን አምነዋል። “በጣም ጥሩ እየሰራን ይመስለኛል።
ምንም እንኳን አንዳንድ በጣም ከባድ ጉዳዮች ቢቀሩም፣ ወደ ስምምነት በጣም ልንቃረብ እንችላለን። ዛሬ ትልቅ እርምጃ ተራምደናል፤ ነገር ግን እውነተኛ መሻሻል የታየው ላለፉት ወራት ነው። ጉዳዮቹ እጅግ ውስብስብ በመሆናቸው ይህ በአንድ ቀን ውስጥ ሊጠናቀቅ የሚችል ሂደት አይደለም” ብለዋል ትራምፕ።
አክለውም በትናንት በምሽት ከዘለንስኪ ጋር በመሆን የብሪታንያ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያን፣ የጀርመን፣ የፊንላንድ፣ የፖላንድ እና የኖርዌይ መሪዎችን እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት መሪዎችን ማነጋገራቸውን ገልጸዋል።
”እነሱም በዚህ ውስጥ እንዲሳተፉ አስፈላጊ መሆኑን አምነንበታል። ንግግሮቹ እጅግ ግሩም ነበሩ፤ ጦርነቱን ለማቆም የሚያስፈልጉትን ጉዳዮች ወደ 95 በመቶ የሚሆኑትን ሸፍነናል ማለት እችላለሁ” ሲሉ ትራምፕ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ከእሳቸው በመቀጠል ዘለንስኪ ለመገናኛ ብዙሃን ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት “እጅግ አስፈላጊ ስብሰባ” በማለት አመስግነዋል።
”ዛሬ ስለ ሰላም ማዕቀፉ ገጽታዎች በሙሉ ተወያይተናል። ባለ 20 ነጥብ የሰላም እቅዱ አሁን ላይ በ90 በመቶ ገደማ ስምምነት ላይ ተደርሶበታል” ብለዋል ዘለንስኪ።
ቁልፍ አካል
በተለይም የደህንነት ዋስትናዎች የጠቅላላው ሂደት ቁልፍ አካል መሆናቸውን ጠቁመዋል። “ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የደህንነት ዋስትናዎች ወሳኝ ምዕራፍ መሆናቸውን ተስማምተናል። ቡድኖቻችን በሁሉም ክፍት ጉዳዮች ላይ መስራታቸውን ይቀጥላሉ” ብለዋል የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት።
ከስብሰባው በኋላ በትራምፕ እና በዘለንስኪ የተላለፉት መልዕክቶች የዩክሬን ጦርነት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ሊገባ ይችላል የሚለውን ተስፋ የበለጠ ቢያጠናክሩም፣ የቀሩት እንቅፋቶች በቀላሉ የሚታለፉ እንደማይሆኑ ግን መሪዎች አፅንኦት ሰጥተውበታል።
