የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የሆነው ቻትጂፒቲ፣ ለአንዳንድ ተጠቃሚዎች ማስታወቂያ ማሳየት ሊጀምር እንደሆነ አስታውቋል።
የቻትጂፒቲ እናት ኩባንያ የሆነው ኦፕንኤአይ እንዳስታወቀው፤ የመጀመሪያ ሙከራውን በአሜሪካ ባሉ በነፃ በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ ያደርጋል።
ቻትጂፒቲን ከፍለው የሚጠቀሙ ሰዎች ያሉ ሲሆን፤ ዝቅተኛ ዋጋው በወር 8 ዶላር ነው።
ኦፕንኤአይ እንዳለው፤ ሰዎች ቻትጂፒቲን በሚጠቀሙ ጊዜ አስፈላጊ የሚባሉ ማስታወቂያዎች ይመጡላቸዋል። ለምሳሌ ሜክሲኮ ውስጥ የሚጎበኝ ቦታ ጠቁመን ብለው የሚጠይቁ ሰዎች የሽርሽር ቦታዎች ማስታወቂያ ሊያዩ ይችላሉ።
ኩባንያው ተጠቃሚዎች ከቻትጂፒቲ ጋር የሚያወሩትን ነገር ማስታወቂያ ለሚያስነግሩ ድርጅቶች አሳልፎ እንደማይሰጥ ቃል ገብቷል።
አክሎም፤ ማስታወቂያ ያስፈለገው “በሚገኘው ገቢ ተጠቃሚዎቹን የበለጠ ለማገልገል” እንደሆነ ገልጿል።
ፋይናንሻል ታይምስ በአውሮፓውያኑ 2025 የመጀመሪያው 6 ወር ብቻ ኦፕንኤአይ 8 ቢሊዮን ዶላር ከስሯል ሲል ፅፏል። ቻትጂፒቲን ከሚጠቀሙት 800 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 5 በመቶው ብቻ ከፍለው እንደሚጠቀሙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
