Home ሰብዓዊነት ነጻነት የሌለው ሕዝብ ነጻ ተቋም አይኖረውም!

ነጻነት የሌለው ሕዝብ ነጻ ተቋም አይኖረውም!

ነጻነት የሌለው ሕዝብ ነጻ ተቋም አይኖረውም!

[አማራ ባንክ እንደ ናሙና]

ከሰሞኑ አንድ ወዳጄ ከአማራ ባንክ የገዛዉን አክስዮን እንዴት ማስመለስ እንደሚቻል አዉቅ እንደሆን  ጠየቀኝ፡፡ እኔም ሁላችንም የገዛነው ባንኩን ለማቋቋም እንጂ ማስመለሻ መንገዱን እንደማላውቅ ነግሬው ይልቁንም በዚህ ወቅት ሠው እየታገተ በሚዘረፍበት ጊዜ “ያንተ ጥያቄ አስግቶህ ያለህን እንዳታጣ ይኾን?” ስል ቀለድኩበት፡፡ ይህ ወዳጄ በጣም አምርሮ ስለነበረ አማራ እንዲህ መጫወቻ  ሆኖ ይቅር፣ ደሃው ገበሬ የቆጠበውን ገንዘቡን የብልፅግና ካድሬዎች ዘረፉት፡፡ የአማራ ባንክ ብለው እውነት መስሎን በስሜት አክስዮን ገዛን፡፡ ከፍተኛ  ገንዘብ ተከፈለ፣ ይሄዉ ከማስታወቂያ ጋጋታ በስተቀር  ወፍ የለም፣  ጭራሽ ገንዘቡን የብልጽግና ካድሬዎች በመቶ ሺዎች ደሞዝ እየተቀጠሩ ሥራ ማማረጫ አድርገውታል ብሎ የተቀጠሩ  ካድሬዎችን ነገረኝ፡፡

እኔም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቼ ማሠብ ጀመርኩ፡፡ በመሠረቱ ነጻነት የሌለው ሕዝብ ለጌቶቹ አገልጋይ ከመሆን ውጪ የራሱ የሆነ ተቋምም ሆነ ህልውና  ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህ  ባንክ  ይቋቋማል  ከተባለ  ሦስተኛ  ዓመት  ያለፈው ሲሆን በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ከማስነገርና ያልተጨበጠ  ወሬዎች  ከማሥወራት የዘለለ ሥራ ሲሰራ አልታየም፡፡ ከእሱ በኋላ የተጀመሩ ባንኮች ሥራ የጀምሩ ሲሆን የአማራ ባንክ እንደ ጌታ ምጽአት “ይመጣል” እየተባለ ተስፋ ብቻ ሆኗል፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት ይህ ባንክ ምንም ዉጤት እንደማያመጣ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ግልፅ ነዉ፡፡ ይህ ሕዝብና ክልል በሁሉም ዘርፍ እንዳያድግና እንዳይለማ እንዳይሻሻል ሆን ተብሎ በዘመነ ወያኔ በመንግሥት ሲተግበር የነበረዉ አማራውን የማዳከምና የማኮላሸት ብሎም የማጥፋት ሤራ በከፋ መልኩ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ማሳያው በዘመነ ወያኔ ክልሉን ሢመሩ የነበሩ የወያኔ ምሥለኔዎች በሠሩት ሥራ መጠየቅ ሲገባቸው እንዲሁም አዲስ አመራርና ያለፈዉን በደልና ግፍ የሚክስ አሠራር መዘርጋት ሲገባ ያለምንም ለዉጥ የነበሩት ከፍተኛ አመራሮች ሳይለወጡ የጨለማው መንገድ  ቀጥሏል፡፡

ለአንድ ማኅበረሰብ ጠንካራ ድርጅት፣ ጠንካራ አመራር፣ ጠንካራ አባላት በጣም ወሣኝ ናቸው፡፡ ስለሆነም ለውጥ በየት በኩል ይምጣ? በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጊዜ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ይህ ጉዳይ ጠፍቷቸው ሳይሆን አውቆ የተኝን ቢቀሠቅሱት አይሠማም እንደተባለው ነው፡፡ የባንኩ እንቅስቃሴ ከወቅቱ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሕዝብ ላይ የተያዘው የተሳሳተ ፍረጃ ከመሠረቱ እስካልተለወጠ ድረስ ለሕዝቡ የሚጠቅም ተቋም ሊኖር አይችልም፡፡ እስከመቼ  ድረስ በመጠላለፍና በመመቀኛኘት እንኖራለን? የአንዱ አካባቢ እድገት ለሌላው ተስፋና ምሣሌ መሆን ሲገባው ሌላውን አደህይቶና አጎሳቁሎ በሠላም መኖር ከቶውንም ይቻል ይሆን? በአጠቃላይ የሀገራችን ሕዝብ ለሠላምና ለለውጥ እየጓጓ አድርግ የተባለውን እየታዘዘ  የቱንም ያህል ቢለፋም በመሪዎች ባለመታደሉ የሠላምና  የእድገት ጎዳናዎችን እየዘጉ የተንኮልና  የሤራ መለማመጃ  እያደረጉን ብዙ የመከራ ዘመን ለመኖር ተገደናል፡፡

ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ዋነኞቹ ተጠያቂዎች የመንግሥት ባለሠልጣናት ሲሆኑ የተቃዋሚ  መሪዎች በዋናነት  የእምነት አባቶች  የማህበረሰብ  መሪዎች፣  ምሁራን፣  ሀገራችንንና ሕዝባችንን በዘላቂነትና በእውነት አንቅተነውና አደራጅተነው ቢሆን  ኖሮ  የሥልጣን ጥመኞች  መሠላል ከመሆን ታድገነው በሃገራችን  ሠላምና ይሠፍን ነበር፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ሕዝብ ለመብቱና ለነጻነቱ፣ ለእድገትና ለሠላም አምርሮ እንዳይታገል አቅጣጫ እየሳትን በጥቅም ፍርፋሪ እየተደለልን እውነተኛ ታጋዮችን አሳልፈን እየሠጠን ግራ የገባው ሃገርና ሕዝብ ፈጥረናል፡፡ ዛሬ እንኳን መብት ለመጠየቅ ቀርቶ በሕይወት ለመኖር  ስጋት ውስጥ ወድቀናል፡፡ ከዚህ ለመውጣትና የባሰ ነገር እንዳይመጣ በግልጽ በመነጋገር ትልቅ  ትግል ማድረግ አለብን፡፡ የሥልጣን ጥመኞችን መታገል፣  ሌቦችን መታገል፣ አድርባዮችን መታገል፣ ውሸታሞችን መታገል፣ አጭበርባሪዎችን መታገል፣ ሠነፎችን መታገል፣ ዘረኞችን መታገል፣ የኋላቀርነት አስተሳሰብን መታገል፣ ጎጂ ልማዶችን  መታገል፣ በአጠቃላይ አብዮት ያስፈልጋል፡፡ ሰላማዊ  አብዮት፣  ጉልበተኞችን እና ትእቢተኞችን፣ ገራፊዎችን እና ገዳዮችን ሲያሸክመን እንጂ  ሕዝብን የሚያገለግሉ መሪዎችን  አምጥቶ  አያውቅም፡፡ ሠላማዊ ትግል ጎጂና ጠቃሚውን ለመለየት ያስችላል፡፡ ለዚህ ትልቁ ምሣሌያችን የሆነው መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የጨለማውን ጊዜ የዲያብሎስን የትእቢት ሥራ በትህትና አፍርሷል። ምንም እንኳን የሁሉን ቻይ ጌታ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እውነተኛ ፍቅርን በሥራ ለዓለም አሳይቷል። በመጨረሻም ጌታ በገንዘብ በይሁዳ ቢካድም የጸሐፍትና የፈሪሳውያንን፣ የግብዞችን የጨለማ መንገድ በመለወጥ የሠውን ልጅ ነጻ  ለማውጣት ክርስቶስ  እውነትን አስተምህሮ ለእውነትና ለፍቅር ኖሮ እውነትና ፍቅር የሚያስከፍለውን ዋጋ ከፍሎ ትንሣኤውን አሣየን፡፡ የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ትንሣኤ የምንፈልግ ሁላችን ከትንሣኤው  በፊት  ያለውን  ሠሞነ ሕማማትን አውቀን ሕማማት ሳይኖር ትንሣኤ የለምና ለሀገራችንና ለሕዝባችን ትንሣኤ በእውነት እንስራ። ሠላም!