ሠሎሞን ለማ ገመቹ.
‹‹ዝናቡ ዘነበ ይሞላል ውሃው
አወይ ይሄን ጊዜ ለተሻገረው››
ከፍ ሲል በጥቅስ የተቀመጠው ቅኔ ነገር ነው፡፡ ‹‹ሰምና ወርቅ አለው›› ተብሏል፡፡ ያሻው እንደተመቸው ይፍታው፡፡ በበኩሌ ወርቁን ከሰሙ የመለየት ፍላጎት የለኝም፡፡ ጊዜው ግሪንቢጥ ነው፡፡ ጊዜው ያ ምስኪን ወጣት ድምፃዊ ‹‹ተጠምቶ እሳት ይሞቃል፤ ተርቦ ልብስ ይደርባል…›› እንዳለው ዓይነት ነው፡፡ በቀላሉ የሚሻገሩት አይደለም፡፡ ሰው ድህነት ጦሩን ሰብቆ ጎን ጎኑን እየጠበሰቀው፣ የኑሮ ውድነት ሠይፉን ስሎ ላይ ታች እያሯሯጠው… የድንዛዜ መጋረጃውንም ጋርዶበት፤ የዘር፣ የጎጥ፣ የመንደር ባንዲራ ይዞ ሲያውለበልንና ሲወራጭ እየታየም አይደል?
የድህነቱ ዝናብ ጨቅ አርጎ… ይዘንባል፡፡ በዚያው ልክ የዋጋ ንረቱ ወጀብና ውሽንፍር መቆሚያ የለውም፡፡ እርጋታ የሚባል ነገር ያልፈጠረበትም ነው፡፡ የደንታ-ቢስነቱ፣ የግዴለሽነቱ እና የተስፋ መቁረጡ ውሃም፤ ሞልቶ ሲፈስ እየታየ ይመስለኛል፡፡ ጊዜው እንዲህ መሰል ሐሣባዊ መልክና ቅርፅ ያለው ለመሆኑ አያከራክርም፡፡ ይህን መሰሉን የዘመን፣ የጊዜ ውሃ ማን ይሆን የሚሻገረው? በከተማው፣ በሠፈሩ ስንቱ ነው ረሃቡን ልብስ ደርቦ፣ ጥሙን እሳት ሞቆ ለመሸወድ የሚከጅለው? የእኛ ‹‹እናት ሃገር›› መልከ-ብዙ ኑሮስ፤ ምን ያህሉን ‹‹… ያልፍልኝ ይሆናል›› ባይ እንደወጣ አስቀርቷል? በ‹‹ሲሾም ያልበላ…›› ፈሊጥ፤ ስለ ሆዱ ሽቅብ ወጥቶ፤ በሆዱ ምክንያት ከዘብጥ የተፈጠፈጠውስ ስንቱ ‹‹ሰው ጤፉ…›› ለከርሱ ብቻ ሟች ይሆን? ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ሃገሪቱ አሁንኛ ጠረፍ ድረስ ምን ያህል ሰው፤ ይህን ‹‹ኑሮ›› የሚባል ኑሮ ለመሻገር ተቸግሮ እንዳለ፤ ቤት፣ ጎዳና፣ ጋራ ሸንተረሩ… ይቁጠረው፡፡
የጊዜው ሁኔታ በኑሮ መነጥር ሲታይና ይኸው ኑሮ ጫንቃውን ያጎበጠው መስሎ በማይታየው አንዳንድ ሰው ቃል ሲመዘን፤ ከዚህ የኑሮ አዘቅትና ማጥ ሊያሻግረን የሚችል የተስፋ ዘመን፣ ሊጨበጥ ይችል ይሆናል የሚባል የምኞት ጊዜ በቀላሉ እንደማይመጣ መገመት ‹‹ልሂቅ፣ ምሁር፣ ጠቢብ…›› መባልን፤ ወይም እንደዚያው እንደሚባሉት ሆኖ መገኘትን የግድ የሚል አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ ጊዜ፤ አምና ሰዎች ‹‹ረገሙት›› እንደተባለው ጊዜ፤ ወደተሻለው መፃዒ ጊዜ የሚሻገር ዓይነት አለመሆኑን፤ አንድ አፍታ ቆም ብሎ ከቤት እስከ አደባባይ ያለውን ሃገራዊ ሁኔታ መታዘቡ ብቻ በቂ መስሎ ይታየኛል፡፡ ኑሮ ‹‹ያምናን ቀን ረገምኩት ለአፌ ለከት የለው፤ የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው›› እንዲሉ ሆኗል፡፡ አጠር ሲል የእኛ ኑሮ፤ ሟች ፕሮፌሰር ከመሞታቸው በፊት ‹‹እንዘጭ ዕምቦጭ›› እንዳሉት ነው፡፡ የኑሮ እና የአኗኗር… እንዘጭ ዕምቦጭ፡፡ የፖለቲካ፣ የአስተዳደር፣ የብልሃት፣ የአካሄድ ስልት ጠመዝማዛነትና ገታራነት፣ የ‹‹ተገዢው››› ጫንቃ በዘመን ውስጥ የመሰልነቱ ጉዳይ… የይዘት ለውጥ አለማሳየት እንዘጭ ዕምቦጭ፡፡
አንባቢያን… ከፍ ሲል ከጀመርኩት የኑሮ ጉዳይ አንጣር፤ ስለ መንግሥት አላወራም፡፡ ኑሮ ስለሚያስወድዱት ነጋዴዎችና አቀባባዮቻቸውም አልፅፍም፡፡ ስለ ሕዝብም፡፡ ስለ ብሔርም፡፡ ‹‹ስለብሔር፣ብሔረሰቦች ሕዝቦች››ም የምለው የለኝም፡፡ ለምን? እነዚህ ሁሉ ከፖለቲካው ጋር ንክኪ ያላቸው ናቸው፡፡ ወይም ከእነሱ ጋር ተያይዘው የሚነሱት እና የሚጣሉት ጉዳዮች በሙሉ፤ በቡሃው ላይ የለሙ ‹‹ቆሮቆሮች›› ናቸው፡፡ ስለዚህ የምፅፈው ወይም የማወራው ወይም የምለው፤ ስለ ኑሮና ስለ ኑሮ ብቻ ይሆናል፡፡
ኑሮ ዛሬ፤ በባሕርዩም በሉት በጠባዩ… ‹‹ከፍ ከፍ ብለናል›› ከሚሉት ውጭ በመሀልና በበታች ደረጃ እንዲሁም ‹‹የደሀ ደሀ›› የሚባሉትን ሰዎች በልዩነት የሚመለከት፤ አንገብጋቢና አቃጣይ!!!…ሃገራዊ ነጥብ ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል በራሱ የኖረና የማይፋታን ዓይነት ሃገራዊ ነጥብ በመሆኑ፤ በሌላ በኩል ራሴን ጭምር በጦሰኛው ኑሮ ምክንያት ከ‹‹ደሀ ደሀዎቹ›› ደጃፍ አካባቢ ያገኘሁት በመሆኑ፤ በተጨማሪም ከይህ ሳምንት ዋዜማ ጀምሮ ከናካቴው መልከ-ጥፉ እና አረመኔ ሆኖ በመጣው የዋጋ ንረት የተነሳ፤ እነሆ ስለ ኑሮና ሕይወት ስላልኖሩ ነዋሪዎች ጥቂት መፃፉን መርጫለሁ፡፡
መቸም ስለ ኑሮ ሲወራ፤… ‹‹በልማት ስም፣ በፍትሕ ስም፣ በዴሞክራሲያው ሥርዓት ግንባታ ስም፣ በነፃው ገበያ ሂደት ስም…›› ኑሮ ‹‹ጢባ ጢቤ…›› ስለተጫወተባቸው ሰዎች እና እነሱም ‹‹እንከባከባቸው፣ አብረውንም ይደጉ፣ ይኑሩም…›› ስላሏቸው እንስሳትንም አብሮ ማንሳቱ ጡር አይደለም፡፡ በይበልጥም የምስኪን ምስኪን ስለሆኑት፤ ኑሮ ጉስቁልቁል፣ ብክንክን … ያደረጋቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እጅ ዓይተው ስለሚያድሩት ድመቶችና ውሾች ማስታወሱ፤ እንደ ኃጢያት የሚቆጠር ጉዳይ አይሆንም፡፡
ኢምንት በሆነ ደረጃ የምፅፍላቸው… ሰዎች! ኑሮ እየናረባቸውና አዋራ እያስነሳባቸው፤ ዝም የሚሉ ናቸው፡፡ ደሞም ዝም የማይሉም ናቸው፡፡ ሰዎቹ ምንጊዜም ቢሆን ኑሯቸውን ከመጥበሻው ወደ ዕሳቱ የሚወረውረው የገበያ ዋጋ ሲጨምር፡- ‹‹ተመስገን! የባሰ አታምጣ!…›› የሚሉ፤ ካላቸውም፣ ለነገ ይሁን ካሉት ላይም እየቀነሱ ጨምረው የሚሸምቱ ናቸው፡፡ መጨመር ሲያቅታቸው ጦም የሚያደሩ፣ የምግብ መጠን እና ዓይነት የሚቀንሱ፣ ለመለወጥ የሚሞክሩና በዚህን ዓይነቱ የኑሮ ዛቢያ ዙሪያ እየተሽከረከሩ ‹‹ኖረናል›› የሚሉ ግን ያልኖሩ ኗሪዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ሰዎች፣ ወይም ኑሮን ያልኖሩ ኗሪዎች… ኑሯቸው ጠሮ እያለ ‹‹ነጋዴውስ ቢሆን ምን ያድርገው?!…›› ሲሉም ይሰማሉ፡፡ ዘወትር በሚባል ደረጃ ‹‹መንግሥትስ ከስንቱ ይሁን? ግራ ገባው ዕኮ!… ነጋዴው እንደሆነ ዓሣ የላሰው ድንጋይ ነው!….›› ብለው፤ የደረቀ ከንፈራቸውን በየዋህነትም በሉት በሽሙጥ፤ ለመምጠጥ ሲሞክሩ ወይም ሲመጡ የምንመለከታቸው ናቸው፡፡ ደግሞም እንደ እነሱ በኑሮ አምበርጭቃ… ታሽተው ለከሱትና ለሞገጉት ድመቶቻቸውና ውሾቻቸው፤ የሚንሰፈሰፍ አንጀትና የሚያዝን ልብ ያላቸውም ናቸው፡፡ ጉድ ዕኮ ነው!…. የውሾቹና የድመቶቹ መጎስቆል፣ በረሃብ አለንጋ መገረፍ፣ በጥም ንዳድ መቃጠል የሚያስኮንናቸው፤ የፅድቅን ጎዳና የሚያግድባቸው ሆኖ የሚሰማቸውም እነዚሁ ሰዎች ናቸው፡፡
አንዳንዴ ስለነዚህ መሳይ ሰዎች ማውራት፤ በራሱ ቅኔ ይሆናል፡፡ ከንፈር ለመምጠጥ ቢፈለግ ዕንኳ ተመጣጩ ከንፈር ቢያንስ ረጠብ ያለ ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ ሰዎቹ ግን ነዳጅ በሌትር አንድ ብር የጨመረ መሆኑን ጠብቆ፤ በአንዲት ዕንቁላል ከአንድ ብር በላይ ዋጋ ለመቆለል ለሚጣደፍ ‹‹ነጋዴ ነኝ›› ባይ በህልም ካልሆነ በቀር ቂቤ ነክቶት የማያውቅ አዚመኛ… ደረቅ ከንፈራቸውን፤ በኃዘኔታ ስሜት የሚመጡ ናቸው፡፡ ታዲያ እኔ በነዚህ ሰዎች ሁኔታ መገረምና መደነቅ አለመቻሌ … ይኸው አስከ ዛሬ ድረስ ሼም እንደሆነብኝ አለ፡፡
እንዳው ለመሆኑ ግን… በዓለም ላይ ቢዞር፤ በድህነቱ፣ ከድህነቱም ፅናት የተነሳ በአፅሙ መሄዱን እያወቀ ወደ መቃብር እስኪወርድ ድረስ ሊያተርፍበትና ፍፁም ሊበለጽግበት ለሚፈልግ ነጋዴ… ‹‹እሱም ዕኮ ወዶ አይደለም…›› በማለት ደረቅ ከንፈሩን የሚመጥ እንደ እኛ ሃገር ዓይነት በኑሮ የተሳከረ ሰው ይገኛል? በበኩሌ እንዲህ ዓይነቱ የእኛ ሰው፤ ራሱን አቅል ከነሳው ኑሮ ለማስማማት የወሰነ ከመምሰሉም በላይ፤ ይህንኑ ‹‹ኑሮ›› ተብዬ ይበልጥ ሲዖል ከሚያደርግበት የገበያና የአገልግሎት… ዋጋ ንረት ጋር የመጋፈጡን እውነት ከራሱ ለመሸሸግ በመፈለግ ስሜት፤ በየራሱ ‹‹አስማት›› የሚመስል ኑሮን ‹‹ኖርኩ›› ማለቱ ሳያንስ፤ ዞሮ፡- ‹‹ይህ መንግሥት እነዚህን አስተማተኛ ነጋዴዎች ምን ያድርጋቸው?…›› ብሎ መጠየቁ፤ ኑሮን ያልኖረ ኗሪ ለመሆኑ አንድ መመዘኛ ይመስለኛል፡፡
ማረሚያ!
ባለፈው የመጽሔታችን ዕትም ‹‹ተስቦ እና ሌቦ›› በሚለው ርዕስ ቀርቦ ከነበረው ጽሑፍ፤ በ‹‹ዲዛይን›› ሥራ ስህተት ተቆርጦ የቀረው የመጨረሻው አንቀፅ የሚከተለው ነው፡- ‹‹በሰልስቱ ለሊቱን፤ ያንን ተስቦ ፈርተው ከሩቅ ምግብ ያቀብሉን ከነበሩትና ከሌሎችም ዘመዶቹ መካከል ጥቂት የማይባሉት አቁማዳቸውን እየያዙ በጎተራው፣ በቤቱ ውስጥ የነበረውን የአያቴን እህል ለመዝረፍ መጡ፡፡ እኔም እርስ በርሳቸው በሌብነት ተግባራቸው ሲጨቃጨቁ በትዝብት ዓይን ተመለከትኳቸው፡፡ ደግሞም ‹‹ሰው ሌባ ሲሆን ተስቦ አይዘውም? በወረርሽኝ አይጠቃም ማለት ነው?…›› የሚለውን ጥያቄ ለራሴው በለሆሳስ አቀረብኩ፡፡ ያን የሕይወት ትዕይንት ከተመለከትኩ በኋላ በአማካይ ከስልሳ በላይ ዓመታት አለፉ፡፡ አይ ተስቦና ሌቦ? ስትታመም የማይጎበኝህ፤ ስትሞት ሀብትን ለመዝረፍ ይሰለፋል፡፡ እስካሁንም ድረስ ያን በታዳጊነቴ ዕድሜ… ታዝቤው ያለፍኩትን የወገኖቼን ይሉኝታ-ቢስ ድርጊት ዳግመኛ አስተውላለሁ፡፡ /ለወርቅነሽ ገላኔ. ሰላሌ./