ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ አዳዲስ ወታደራዊ ጥቃቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ ካስጠነቀቁ በኋላ፣ አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ዜጎቿ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና አስፈላጊ ከሆነም አካባቢውን በፍጥነት ለመልቀቅ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳሰበች።
በነዚህ ቀናት በባህሬን፣ ኢራቅ፣ እስራኤል፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች በሙሉ ለዜጎቻቸው በላኩት የጥንቃቄ መልእክት፤ ድንገተኛ የበረራ መሰረዞች፣ የአየር ክልል መዘጋቶች እና የጉዞ መስተጓጎሎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት አስተያየት ዲፕሎማሲያዊ ንግግሮቹ ውጤት ካላመጡ ዋሽንግተን በኢራን ላይ «አደገኛ ጥቃት» ልትሰነዝር እንደምትችል ቢናገሩም፣ ውይይቱ በመቀጠሉ ምክንያት ግን የታሰቡት ጥቃቶች ለጊዜው መገታታቸውን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ቴህራን በበኩሏ፤ ከአሜሪካም ሆነ ከእስራኤል ለሚሰነዘርብኝ ማንኛውም ጥቃት ወዲያውኑ ምላሽ እሰጣለሁ ስትል ዝታለች። አክላም ጥቃት ከተፈጸመባት በቀጣናው የሚገኙ የኃይልና የኢነርጂ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደምታደርስ አስጠነቅቃለች።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት እየረገበ ካልመጣ ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት እና ከአሜሪካ ጋር ቁራኝነት ያላቸው ድርጅቶች ኢላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ የገለጸችው አሜሪካ፣ ዜጎቿ ወደ አካባቢው የሚያደርጉትን ጉዞ ድጋሚ እንዲያሰላስሉበት አጥብቃ አሳስባለች።
አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙ ዜጎቿ አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ አስተላለፈች
Date:
