Home ዜና አየር መንገዱ 362 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት እንዲከፍል በኦዲት ተወሰነበት

አየር መንገዱ 362 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት እንዲከፍል በኦዲት ተወሰነበት

አየር መንገዱ 362 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት እንዲከፍል በኦዲት  ተወሰነበት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በሰጠው የግንባታ ውል መሠረት 1ሺህ 992 መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ከቀረጥ ነፃ መብት የገቡ የግንባታ ዕቃዎች፣ በተለያዩ መንገዶች ያላግባብ ጥቅም ላይ መዋላቸው በጉምሩክ ኮሚሽን ኦዲት በመረጋገጡ 362 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል እንደተወሰነበት ተዘገበ።

በውሳኔው ላይ አየር መንገዱ ቅሬታ አቅርቦ እንዲሻር ማድረጉንና ሕገወጥ ድርጊቱን ፈጽመዋል ባላቸው አካላት ላይ ክስ መሥርቶ በክርክር ሒደት ላይ መሆኑን ሪፖርተር ዘግቧል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ታኅሳስ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአየር መንገዱ በላከው የኦዲት ውጤት ማሳወቂያ ደብዳቤ በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መካከል እ.ኤ.አ. ሐምሌ 17 ቀን 2015 የሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች ለመገንባትና የግንባታ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ መብት አማካይነት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ውል መፈጸሙን አስታውሷል።

ጉምሩክ ኮሚሽን የኦዲት ውጤት ማሳወቂያ እንደሚለው፣ በአየር መንገዱ ስም ከቀረጥና ታክስ ነፃ የገቡ የግንባታ ዕቃዎች “ያላግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን በመጥቀስ፣ ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ በሚል ለኮሚሽናችን ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ በሰጠው ጥቆማ መሠረት” የምርመራ መስክ ውስን ኦዲት እንዲከናወን ተደርጓል።

ይሁንና አየር መንገዱ ለጉምሩክ ኮሚሽን ባያስገባው ደብዳቤ፣ ከሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ሳይት ቀረጥ ያልተከፈለባቸው ዕቃዎች ያላግባብ እየተወሰዱ መሆኑን ገልጾ፣ ንብረቶቹ ከተወሰዱበት እንዲመለሱ አቤቱታ ማቅረቡን ገልጿል።