የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒ፣ የአሜሪካ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል የቀረበላቸውን የደህንነት ማስጠንቀቂያ ተከትሎ፣ በቴህራን ወደሚገኝና እጅግ የተወሳሰበ የምድር ውስጥ መሸሸጊያ መግባታቸውን ኢራን ኢንተርናሽናል ቅዳሜ ዕለት ዘገበ።
የኢራን ተቃዋሚ የመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት፣ ከፍተኛ ወታደራዊ እና የደህንነት ባለስልጣናት የአሜሪካ ጥቃት የመሰንዘር እድሉ እየጨመረ መምጣቱን ካስጠነቀቁ በኋላ፣ መሪው ወደ ጠንካራ የኮንክሪት ዋሻዎች ገብተዋል።
ይህንን ተከትሎም የዕለት ተዕለት የአመራር ስራውን ሦስተኛ ልጃቸው ማሱድ ካሜኒ እንደተረከቡና፣ ከመንግስት አስፈጻሚ አካላት ጋር የሚደረገው ግንኙነት በእርሳቸው በኩል ብቻ እየተደረገ መሆኑ ተዘግቧል።
ይህ የኢራን ባለስልጣናት ስጋት የጨመረው፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ ነው። ፕሬዚዳንቱ “በርካታ የአሜሪካ መርከቦች ወደ ኢራን እያቀኑ ነው፤ ነገር ግን ልንጠቀምባቸው እንደማይገባ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢራን ባለስልጣናት በበኩላቸው ለማንኛውም ጥቃት ከባድ ምላሽ እንደሚሰጡ እየዛቱ ነው። አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለስልጣን “ማንኛውም ጥቃት በእኛ ላይ እንደታወጀ ሙሉ ጦርነት ይቆጠራል” ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢራን ብሔራዊ ደህንነት ኮሚሽን፣ በካሜኒ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት “የጂሃድ” አዋጅ እንደሚያስከትል ማክሰኞ ዕለት አስጠንቅቋል። የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በበኩላቸው፣ በመሪው ላይ የሚደረግ ጥቃት “በኢራን ህዝብ ላይ እንደታወጀ ጦርነት ነው” ብለዋል።
ይህ ውጥረት የመጣው፣ በኢራን ውስጥ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ እና መንግስት እየወሰደ ያለው የኃይል እርምጃ በቀጠለበት ወቅት ነው። ምንም እንኳን ትክክለኛው ቁጥር ባይታወቅም፣ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተቋም (HRANA) እንደገለጸው፣ በግጭቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 5,137 መድረሱ ተረጋግጧል። አሜሪካም ይህንን የኃይል እርምጃ በመቃወም አርብ ዕለት በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ጥላለች።
በሌላ በኩል አልጀዚራ ባወጣው ሰፊ ትንታኔ፣ ኢራን በውጭ ወታደራዊ ስጋት ብቻ ሳይሆን በውስጥ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ አመልክቷል። ምንም እንኳን መንግስት በቅርቡ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ በኃይል ማፈን ቢችልም፣ ለተቃውሞው መነሻ የሆነው የኢኮኖሚ ውድቀት እና የዋጋ ንረት ግን አልተቀረፈም።
በአሁኑ ወቅት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር፣ የኒውክሌር እና የሚሳኤል ፕሮግራሞቿን እንዲሁም ቀጠናዊ ተጽዕኖዋን መቀነስ ይኖርባታል። ሆኖም እነዚህ እርምጃዎች ለካሜኒ ስርዓት እንደ “ራስን ማጥፋት” ስለሚቆጠሩ ውሳኔው ከባድ ሆኖባቸዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት፣ ኢራን አሁን ባለችበት መቀጠል የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። ከካሜኒ በኋላ ያለው የኢራን ዕጣ ፈንታም ከሃይማኖታዊ መሪዎች ወደ ወታደራዊው ክፍል (የኢራን አብዮታዊ ዘብ – IRGC) የበላይነት ሊሸጋገር እንደሚችል እና ለውጥ የማይቀር ጉዳይ መሆኑን ባለሙያዎች ይተነብያሉ።
