የኢራና ሁለንተናዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ ተቃዋሚዎች ትራምፕን ለማስደሰት ሲሉ የራሳቸውን ሀገር እያወደሙ ነው ሲሉ ከሰሱ።
ካለፉት ዓመታት ከፍተኛ የተባለለት የመንግሥት ተቃውሞዎች በቴህራን እና በሌሎች የኢራን ከተሞች እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ተቃውሞውን በተመለከተ የኢራኑ ሁለንተናዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ፥በቴህራን በሚገኘው የኢራን መንግስት ቴሌቪዥን ላይ ትላንት በተላለፈ ንግግራቸው፥ተቃዋሚዎች የትራምፕን ቀልብ ለመሳብ ሲሉ የኢራን ከተሞችን እያወደሙ እና ትራምፕን ወክለው ሴራቸውን እየፈጸሙ ነው ሲሉ ከሰዋል።
ተቃዋሚዎችን “አጥፊዎች” ሲሉ የጠራቸው ኻሚኒ፥ የኢራን ከተሞች ትራምፕን ለማስደሰት በሚሯሯጡ ተቃዋሚዎች ውድመት እየደረሰባቸው ነው ብለዋል።
የኢራኑ ሁለንተናዊ መሪ፥ ትላንት ባስተላለፋት መልዕክት ፥በሀገሪቱ ዋና ከተማ እና በሌሎች አካባቢዎች የተፋፋመው ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲቆም እና ወደ አንድነት አማራጭ እንዲመጣ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።በኢራናውያን ደም ትራምፕ እጃቸውን አለበት ሲሉም ከሰዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ትራምፕ ”ኢራን ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በኃይል የምትገድል ከሆነ አሜሪካ ታድናቸዋለች” ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
በታህሳስ 28 በሀገሪቱ ከተሞች በተጀመረው የተቃውሞ ሰልፉ ይህ ዜና እስከሚጠናቀርበት ሰዓት ድረስ ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ዶክተሮች አስታውቀዋል።
በመላ አገሪቱ ኢንተርኔት መዘጋቱም ተዘግቧል። ቴህራን ሁኔታውን ለመቆጣጠር እየታገለች መሆኑን ገልጻለች፡፡
ተቃዋሚዎች የኢራን ሁለንተናዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ከሥልጣን እንዲለቁ እና ደጋፊዎቻቸው ወደ ጎዳና እንዲወጡ ያሳሰቡትን የቀድሞ ሻህ ልጅ ሬዛ ፓህላቪ ቦታውን እንዲረከቡ ሲጠይቁ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በስፋት ተሰራጭተዋል።
ዘገባው የስካይ ኒውስ እና የቢቢሲ ነው።
