አይ.ኤፍ.ሲ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የሸራተን ሆቴል ፕሮጀክቶች የ80 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት እቅድ ያዘ

Date:

የዓለም ባንክ የግል ዘርፍ አበዳሪ የሆነው ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ፣ በኢትዮጵያ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት ዘርፍን ለማነቃቃት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እስከ 80 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ( በግምት ወደ 12.4 ቢሊዮን ብር ) የሚደርስ የብድር ኢንቨስትመንት ለማቅረብ ማቀዱን ይፋ አደረገ።

ተቋሙ ያቀረበው የብድር ድጋፍ  ዓላማውም በሀገሪቱ ታዋቂ የሆነውንና ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን ሸራተን አዲስ ሆቴልን በከፍተኛ ደረጃ ለማደስና አዲስ በሸራተን ስም የሚጠራ ተጨማሪ ሆቴል ለመገንባት ነው።

እንደ አይ.ኤፍ.ሲ ከሆነ ፣ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ወጪ 116 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተገምቷል። ከዚህ ውስጥ ተቋሙ ለማቅረብ ያሰበው 80 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ቀሪው ወጪ በባለሀብቱ እንደሚሸፈን ይጠበቃል።

ይህ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉት የተገለፀ ሲሆን የመጀመሪያዉ በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉ የቅንጦት ሆቴሎች አንዱ የሆነውንና ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች ማዕከል ሆኖ የሚያገለግለውን ሸራተን አዲስን ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እድሳት ማድረግ።

ሌላኛዉ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሸራተን ብራንድ ተደራሽነትን ይበልጥ የሚያሰፋ አዲስ የሆቴል ግንባታ ማከናወን የሚሉት ይገኙበታል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በታዋቂው ዓለም አቀፍ ባለሀብት ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ እና በወይዘሮ ሶፊያ ሳላህ አል-አሙዲ ባለቤትነት የሚመራ ነው።

ይህ የኢንቨስትመንት ዕቅድ በአሁኑ ወቅት በዝግጅት ላይ ያለ ሲሆን፣ የአይ.ኤፍ.ሲ የዳይሬክተሮች ቦርድ የፊታችን የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም በሚያደርገው ስብሰባ የብድር ጥያቄውን መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ታሪካዊው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በትላንትናው ዕለት ጥር 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወራሾች ወደ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ መዘዋወሩን ተከትሎ፣ ሆቴሉ በዓለም አቀፉ የማሪዮት ደረጃ ዘመናዊና ቅንጡ ሆኖ እንዲታደስ መታቀዱ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማዘጋጀት መመረጧን ተከትሎ፣ ሚድሮክ ሆቴሉን ለጉባኤው ተሳታፊዎች ምቹና ከፍተኛ ደረጃ ያለው ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑ መግለፁ ይታወሳል።

ሚድሮክ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በዩናይትድ ስቴትስ ሰፊ የንግድ መረብ ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በሪል እስቴት፣ በሆቴል፣ በኮንስትራክሽንና በፋይናንስ ዘርፎች በንቃት በመሳተፍ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አዲስ አበባ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ...

የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የ5 በመቶ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ክፍያን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና...

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ለኢራን ህዝብ – “እኛ ከእናንተ ጋር ነን”

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ፥ የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ...

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና...