ኢትዮጵያን እየጠበቃት ካለው ፍርሰት እንታደጋት!

Date:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከ40-60 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርበታል ተብሎ በሚገመትው የዐማራ ክልል ላይ ወታደራዊ አገዛዝ ካወጁ ሦስተኛ ሳምንታቸው እየመጣ ነው፡፡ የዐዋጁን ባለቤት ‹‹ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ›› ያልነው እንበለ ምክንያት አይደለም፡፡ የክልል ም/ቤት ያልተወያየበትና ያላወቀው፣ ከዛም ባስ ሲል በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈውን ደብዳቤ እማኝ አድርገን ነው፡፡ በዚህ መልክ ‹‹ጦር አውርድ›› የተባለበት አካሔድ ደግሞ ውጤቱ ፍንትው ብሎ እየታየ ነው፡፡ የከባድ መሣርያ እና ድሮን ውርጅብኞች ሰለባ የኾነውም እንደሚባለው ‹‹ዘራፊው›› ሳይኾን ለፍቶ አዳሪው መኾኑ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ያረጋገጡት ጉዳይ ኾኗል፡፡ ከክልሉ በየዕለቱ የምንሠማቸው መሪር ዜናዎች እጅግ ልብ ሰባሪ የሚኾኑትም ለዚህ ነው፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ሁለንተና የሚገለጸው በጦርነት እና እሱ ባዋለደው ሕልቆ መሣፍርት ሞት መኾኑ ‹‹እንመራችኋለን›› ከሚሉት ሰዎች ይልቅ ዓለምን በእጅጉ አስደንግጧል፡፡ መሪዎች በ‹‹እንኪያ ሰላምታ›› እና ‹‹ጠብ በደላላ›› እያሉ ተወያይቶ ችግርን ከመፍታት ይልቅ ‹‹ይዋጣልን›› ማለትን የአገዛዛቸው መለዮ ለማድረግ በዚህ ርቀት የመጓዛቸው አመክንዮ ምንድነው የሚለው ግን ከተራ ‹‹አምባገነን የመኾን መሻት›› ላቅ ያለ ምላሽ ሳይኖረው እንደማይቀር ያስጠረጥራል፡፡ በተለይም ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግሥት ደጋፊ ኾኖ የኖረው ዐማራ ክልል እንዲህ ያለው መከራ እንዲወርድበት ትዕግሥት ያጣው መንግሥት አካኋን ብዙ የሚያስብል ነው፡፡    

ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ውጊያ የተካሔደበት የትግራይ ጦርነት በ‹‹ሰላም›› መቋጨቱን ተከትሎ ብዙ እናቶች እንደ ዋዛ የቀሩ ልጆቻቸውን ሞት ተረድተው ሳያበቁ፣ መንግሥት ሌላ ጦርነት ለማዋለድ የሔደበት ፍጥነትም ቢኾን አሳዛኝ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ አሁን ተረኛው የጦር አውድማ እንዲኾን የተፈረደበት የዐማራ ክልል ሕዝብ ላለፉት ዓመታት በሰላማዊ መንገድ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ እና መፈናቀል እንዲቆም ትዕግሥትን በተላበሰ መንገድ መጠየቁን አስታውሶ፣ አሁን በሞት አበላ እንዲታጠብ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንደታወጀበት ማሰብ፣ ከጦርነት ያላገገመውን ክልል ወደ ባሰ ውድመት እንዲያመራ ከመሻት ከፍ ያለ ፍላጎት በመንግሥት ዘንድ መኖሩን በእጅጉ ብንጠራጠር ፈራጅ አይኖርብንም፡፡

ለዚህ ሩቅ ሳንሔድ ክልሉን ለአምስት ዓመታት ያስተዳደሩት እና የ‹‹ለውጥ›› የሚባለውን መንግሥት ካዋለዱት ግለሰቦች ግንባር ቀደም የኾኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ከሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያደረጉትን ንግግር ማስታወስ ይበቃል፡፡ ‹‹ፖለቲካዊ ጥያቄን ፖለቲካ መልስ›› ከመሥጠት ይልቅ፣ ወታደራዊ ዘመቻን የመጀመሪያም የመጨረሻም መንገዱ ያደረገው አገዛዝ አቶ ገዱ እንዳሉትም ሕዝቡ ከሦስት ወር በፊት ‹‹ጠባቂዬ›› ይለው የነበረውን ሰራዊት ‹‹አጥፊዬ›› ብሎ የሕልውና ትግል ውስጥ እንዲገባ መግፍኤ ከመኾን የዘለለ የሚያመጣው አንዳች ረብ አለመኖሩን መረዳት በተገባ ነበር፡፡ ኾኖም ግን ልክ እንደ በጎ ምሣሌ ‹‹በትግራይ ጦርነት ጊዜ ደግፋችሁ አሁን እንዴት ትቃወማላችሁ?›› የሚሉ የም/ቤት እና የመንግሥት ተጠሪ ሹማምንት ባሉበት ሀገር፣ ሞትን ማስቀረት ሳይኾን ሞትን በፍትሓዊነት ማዳረስ መርኆ ተደርጎ በአደባባይ የሚሞገትበት ሀገር በመኾኑ ይኽን አመክንዮ ማቅረብ ከንቱ ኾኗል፡፡ እንደ መጽሔታችን ዕምነት ነገሩ አሁንም ቢኾን አልረፈደም፡፡ በክልሉ በየዕለቱ የምንሰማቸው እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር እየዘገቧቸው የሚገኙ ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሣርያ ንጹሐን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችም ኾኑ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከዐማራ ክልል ውጪ ባሉ ከተሞች እየተፈጸሙ ያሉ የጅምላ እሥሮች ባስቸኳይ ቆመው፣ ሀቀኛ እና ሰላማዊ ንግግር በማድረግ ኢትዮጵያን አድፍጦ ደጇ ላይ እየጠበቃት ካለው ፍርሰት መታደግ ይገባል እንላለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...