የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን፣ ሃገሪቱ የኒውክሌር ኃይል ልማት መሠረተ ልማቶችን እያዘጋጀች መሆኑንና በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደምትጀምር አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አብዱራዛቅ ኡመር እንደገለጹት፤ የኒውክሌር ኃይል ልማት ፕሮግራሞችን አከናውኖ ኃይል ማመንጨት ከ10 እስከ 15 ዓመታት ሊፈጅ ቢችልም፣ ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ግን በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ ኃይል ማመንጨት ትጀምራለች ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
አክለውም ለሥራው የሚያስፈልጉ ተቋማት መደራጀታቸውን፣ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑንና የደኅንነት ጥንቃቄ ሥራዎችም በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የኒውክሌር ልማት ፕሮግራሙ የኃይል አቅርቦትን ከአየር ንብረት ጋር በተጣጣመ መልኩ አስተማማኝ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ቴክኖሎጂው በጤና፣ በኢንዱስትሪና በግብርና ዘርፎች ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ኒውክሌር ኃይልን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለልማት ለማዋል ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መጀመሩን መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ልማት ፕሮግራም እንደምትጀምር ማስታወቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን እንዲቋቋም መወሰኑና የሚመራበት አዋጅም ይፋ መደረጉ አይዘነጋም።
