ክቡር ሩስላን ናሲቦቭ ራፋኤል (በኢትዮጵያ የአዘርባጃን ባለሙሉ ሥልጣንና ልዩ አምባሳደር)
ውድ የግዮን መጽሔት አንባቢያን፣ በምሥራቅ አውሮፓና በምዕራብ እስያ (በደቡብ ካውካሰስ) መገናኛ ላይ የምትገኘው አዘርባጃን ሪፐብሊክ እና የታላቋ አፍሪካ የፖለቲካ መዲናና ዋና በር የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀና ስትራቴጂካዊ ደረጃ አሸጋግረዋል፡፡
በእነዚህ ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ እንቅስቃሴዎች፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ትስስሮች እንዲሁም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕቀፎች ላይ በመመስረት በኢትዮጵያ የአዘርባጃን ባለሙሉ ሥልጣንና ልዩ አምባሳደር ከሆኑት ክቡር ሩስላን ናሲቦቭ ራፋኤል ጋር የግዮን መጽሔት ጋዜጠኞች ተረፈ ወርቁ እና ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ያደረጉትን ጥልቅ፣ አጠቃላይና አስተማሪ ቃለ መጠይቅ የመጨረሻ ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ!!
ግዮን፦ አዘርባጃን አብዛኛው ሕዝቧ የእስልምና እምነት ተከተይ የሆነ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያዎቹን የእስልምና እምነት ተከታዮች (የነቢዩ ሙሐመድ ባልደረቦችን) በሰላም በመቀበልና በመጠበቅ በታሪክ ልዩ ቦታ አላት፡፡ ይህንን ታሪካዊ ትስስር እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሃይማኖታዊ አብሮ መኖር እንዴት ይገልጹታል?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ ይህ እጅግ መሠረታዊና ታሪካዊ ጥያቄ ነው! ኢትዮጵያ (ቀደሞ ሀበሻ/አክሱም) በእስልምና ታሪክ ውስጥ የተቀደሰና የተከበረ ቦታ አላት፡፡ የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች በነጃሺ ንጉሥ ሥር በሐበሻ ጥገኝነት ሲያገኙ ኢትዮጵያን ለእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ልዩ አድርጓታል፡፡
አዘርባጃንም ቢሆን ሕዝቧ አብዛኛው ሙስሊም ቢሆንም፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶችና የሌሎች እምነት ተከታዮች እኩል መብት አግኝተው በሙሉ ሰላም አብረው የሚኖሩባት ዓለማዊ (secular) ሀገር ናት፡፡ በባኩ መስጊዶች፣ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት፣ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እና የአይሁድ ምኩራቦች ጎን ለጎን ቆመው ይገኛሉ፡፡
ይህ አዘርባጃንና ኢትዮጵያ የሚጋሩት ታሪክ በዓለማችን ላይ ሃይማኖትንና ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችና የጠብ ንግግሮች በተበራከቱበት በዚህ ዘመን፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ የሃይማኖት መቻቻልና የአዘርባጃን የባሕል ብዝኃነትና የሃይማኖት እኩልነት ሞዴል ለዓለም ትልቅ ተስፋና ትምህርት የሚሰጡ ሕያው አብነቶች ናቸው። ሁለቱም ሀገራት በተለያየ ጂኦግራፊያዊና ታሪካዊ context ውስጥ ቢገኙም፣ ልዩ ልዩ እምነቶችንና ባህሎችን በፍቅርና በሰላም አጣጥሞ በመያዝ ረገድ ያላቸው የጋራ እሴት የሁለቱን ሀገራት የባሕል ዲፕሎማሲ የሚያጠናክር መሠረት ነው፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ የመቻቻል መሠረት ከእስልምናው ዓለም ጋር ካላት ልዩ ታሪካዊ ትስስር ጋር ተደምሮ፣ ከአዘርባጃን ዘመናዊ የባሕል ብዝኃነትና የሃይማኖት እኩልነት ሞዴል ጋር ሲቃኘት ሁለቱን ሀገራት በጠንካራ የባሕል ዲፕሎማሲ የሚያስተሳስር ድልድይ ነው። ይህ አብሮነትና የጋራ እሴት ደግሞ አክራሪነትን፣ ጥላቻንና የጠብ ንግግርን በመከላከል ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሰጠው ትምህርት እጅግ የጎላ ነው፡፡
ግዮን፦ በኢትዮጵያ ቆይታዎ ወቅት የሕዝቡን የአኗኗር ዘይቤ በተመለከተ ያስገረመዎት፣ ያስደመመዎት ወይም ልብዎን ይበልጥ የነካው ልዩ ክስተት ምንድን ነው?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ ከምንም በላይ ልቤን የነካውና ልዩ አድናቆትን በውስጤ የፈጠረብኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንካሬ፣ ጽናትና ተስፋ ነው፡፡ እናንተ ኢትዮጵያውያን በታሪካችሁ ውስጥ በርካታ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶችን አልፋችዋል፤ ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ፈገግታችሁ ከፊታችሁ አይጠፋም፤ ለሀገራችሁ ባላችሁ ፍቅርና አንድነት የጸናችሁ ናችሁ፣ እንግዳንም በአክብሮት ትቀበላላችሁ፡፡ በተለይም የሀገሪቱ ወጣቶች ያላቸው ጉጉት፣ ለትምህርት ያላቸው ትጋት እና ሀገራቸውን ወደ የተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያላቸው ፍላጎት እጅግ ተስፋ ሰጪና ልብ የሚነካ ነው፡፡
ግዮን፦ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዘርባጃን ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ከወራት በፊት ደግሞ የሄይዳር አሊዬቭ ፋውንዴሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሌይላ አሊዬቫ፣ በቅርቡ ደግሞ የአዘርባጃን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ በአዲስ አበባ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ደረጃ የሥራ ምልልሶች በሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ያላቸው ፋይዳ ምንድን ነው? የተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶችስ ምንድናቸው?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ እነዚህ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ መሪዎች የጋራ ምልልሶች በሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ አዲስ ወርቃማ ምዕራፍ የከፈቱ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ቲዎሪ ሲቃኝ፣ ይህ ግንኙነት ከመደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አልፎ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የመሸጋገር ሂደትን ያሳያል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ክቡር ኢልሃም አሊዬቭ መካከል የተደረገው ውይይት እጅግ ፍሬያማና በጥልቅ የጋራ አክብሮት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ውይይቱ ከፖለቲካዊ ግንኙነት፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች እስከ ኢኮኖሚ፣ አይሲቲ፣ ኢንቨስትመንትና ንግድ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ ትብብሮችን ያካተተ ሰፊ መስክ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
የብሔራዊ ምክር ቤት (ሚሊ መጅሊስ) አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ በቅርቡ በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጋር ተወያይተው የፓርላማ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር መሠረት ጥለዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት ሕግ አውጪ አካላት ውስጥ የወዳጅነት ቡድኖች (Friendship Groups) መቋቋማቸውና ሥራ መጀመራቸው ለሁለቱ ፓርላማዎች ግንኙነት ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ በጎ ልምድ መሆኑ ተስመሮበታል፡፡ የኣዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወደ ባኩ ያደረጉት ጉብኝት ደግሞ የከተሞች ትብብርን ወደ አዲስ ደረጃ አሸጋግሯል፡፡ ሁለቱ መዲናዎች የእህትማማች ከተሞች (Twinning Cities) ግንኙነት መሥራች የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ግዮን፦ የመዲናችሁ ባኩ የጥንታዊና ዘመናዊ ሕንፃዎች ውህደት፣ ጽዳትና ዘመናዊ የከተማ አስተዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ነው። በከንቲባ አዳነች አቤቤ ጉብኝት እና በአዲስ አበባ ወቅታዊ ፈጣን የኮሪዶር ልማትና ትራንስፎርሜሽን አንጻር፣ አዲስ አበባ ከባኩ ልምድ ልትወስዳቸው የምትችላቸው ዋና ዋና የስማርት ሲቲና የከተማ ማደስ ልምዶች ምንድናቸው?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መሪነትና በከንቲባ አዳነች አበቤ አስተዳደር እየተከናወነ ያለው የኮሪዶር ልማትና የከተማ ማደስ ሥራ አስደናቂና የመዲናዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የለወጠ ነው፡፡ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና እንደመሆኗ አዲስ አበባ ይህንን የትራንስፎርሜሽን እርምጃ የሚገባት ናት፡፡
ባኩ ተመሳሳይ የከተማ ማደስና ዘመናዊ ማሻሻያ ፕሮጀክቶችን ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት የጀመረች ሲሆን ይህም አሁንም የሚቀጥል ሂደት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሁለቱ ከተሞች ሊተባበሩባቸው የሚችሉ የከተማ ልማት ሞዴሎች አሉ፦
- ስምሙየከተማ ሕንፃ ጥበብ (Harmonious Urban Architecture)፦ ጥንታዊ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶችን ሳይጎዱ መጠበቅ፣ ጎን ለጎንም ዘመናዊና አረንጓዴ ሕንፃዎችን መገንባት (እንደ ሄይዳር አሊዬቭ ሴንተር ያሉ ዓለም አቀፍ ምልክቶች)፤
- የሕዝብመናፈሻዎችና አረንጓዴ ፓርኮች፦ ባኩ በካስፒያን ባሕር ዳርቻ ላይ «ባኩ ቡሌቫርድ» በመባል የሚታወቅ ከ14 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም ፓርክ አላት፡፡ አዲስ አበባም የወንዝ ዳርቻ ልማቷንና የወቅቱን የኮሪዶር ልማት ከዚህ ሞዴል ጋር በማጣጣም ለዜጎቿ ምቹ ማኅበራዊ ቦታዎችን እየፈጠረች ይገኛል፤
- የስማርትሲቲና የዲጂታል አሰራሮች፦ የከተማ ትራፊክ ቁጥጥርን፣ የቆሻሻ አወጋገድን እና የመልካም አስተዳደር አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ መደገፍ፤
- የ“Azerbaijan Service and Assessment Network.” አገልግሎት (ASAN Service) ሞዴል፦ በአዘርባጃን ተፈጥሮ በዩኤን (UN) እውቅና ያገኘው ይህ ሥርዓት፣ ሁሉንም የመንግሥት አገልግሎቶች (ፓስፖርት፣ ፈቃዶች፣ የንብረት ባለቤትነት ወዘተ) በስራ ቀልጣፋነት፣ ከሙስናና እንግልት ነፃ በሆነ መንገድ በአንድ ጣሪያ ስር በደቂቃዎች ውስጥ የሚሰጥ ነው፡፡
አዘርባጃን በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቢሮክራሲንና ሙስናን ለማስወገድ የዘረጋችውና በዓለም አቀፍ ደረጃ (UN Public Service Award) እውቅና ያገኘው ASAN Service ሞዴል፣ ለኢትዮጵያ የሕዝብ አገልግሎት ማሻሻያ መነሻ ሆኗል። አዘርባጃን አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል (One-Stop-Shop) የመስጠት ልምዷን ለኢትዮጵያ በማጋራቷ፣ ሀገራችን ይህንን ተሞክሮ ከአገራዊ እሴቷ ጋር አጣጥማ “የሞሰብ አገልግሎት” በሚል ስም ዕውን አድርጋችኋል፤
በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ በይፋ የተበሰረው ይህ አገልግሎት፤ እንደ ፓስፖርት፣ ውልና ማስረጃ፣ ብሔራዊ አይዲ፣ ንግድና ታክስ ያሉ በርካታ የመንግሥትና የግል አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር አገናኝቷል።
በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በተከፈቱት ዘመናዊ የሞሰብ ማዕከላት አማካኝነት የዜጎች እንግልት፣ ጊዜና ወጪ መቀነስ ተችሏል።አዘርባጃን ይህንን አወንታዊ ልምድ ማጋራቷ የሀገራቱን ወንድማማችነትና የቴክኖሎጂ ዲፕሎማሲ ያጠናከረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የመንግሥት አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማዘመን ጉዞዋን አፋጥኖታል።
የአዘርባጃን ASAN Service ተሞክሮ በኢትዮጵያ ወደ የሞሰብ አገልግሎት ተቀይሮ መተግበሩ የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ወዳጅነት የሚያሳይና በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ትልቅ እመርታ ያስመዘገበ ስኬታማ ትብብር ነው። በዚህም ደስተኞች ነን፡፡
ግዮን፦ ከወራት በፊት የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት (FAI) ተገኝተው ስለ አዘርባጃን የአፍሪካ የውጭ ፖሊሲ ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ ኢትዮጵያ የአህጉሪቱ የፖለቲካ መዲናና ዋና በር በመሆኗ፣ ኤምባሲዎ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አህጉራዊ እንቅስቃሴው ጋር እንዴት ይመለከታታል?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ የአዘርባጃን ሪፐብሊክ የውጭ ፖሊሲ ዋና ዋና አቅጣጫዎች አንዱ በ«ደቡብ-ደቡብ ትብብር» (South-South Cooperation) እና በጋራ አክብሮት ላይ የተመሰረተ ሁለንተናዊ ዲፕሎማሲ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የፕሬዝዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኤልቺን አሚርባዮቭ በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ያቀረቡት ገለጻ ይህንኑ ያብራራ ነበር፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት (AU) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) መቀመጫ፣ እንዲሁም የፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ ልብ ናት፤ ስለሆነም ለአዘርባጃን የውጭ ፖሊሲ ኢትዮጵያ በወሬ ሳይሆን በተግባር የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት፡፡
አዘርባጃን በኢትዮጵያ በኩል በገነባቻቸው መሠረታዊ ድልድዮች አማካኝነት ከአፍሪካ አህጉር ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ ትስስር እያሰፋች ይገኛል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ለአዘርባጃን ወደ አፍሪካ አህጉር መግቢያ ዋና በር ናት፡፡
አዘርባጃን Non-Aligned Movement (NAM) ሊቀመንበር በነበረችባቸው ዓመታት፣ በዓለም አቀፍ መድረክ የበለፀጉ ሀገራትንና የአፍሪካን ድምፅ ለማጎላት፣ በኮቪድ-19 ወቅት የክትባት እኩልነትን ለማስፈንና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡ እነዚህን ጥረቶች ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
ግዮን፦ አዘርባጃን COP-29 ታላቁን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ በስኬት አስተናግዳለች፤ ኢትዮጵያ ደግሞ COP-32ን ለማስተናገድ በዕጩነት እየተዘጋጀች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መሪነት ሂደት ከአዘርባጃን ምን ዓይነት የሎጅስቲክስ፣ የዲፕሎማሲና የዘላቂነት ልምዶችን ልትወስድ ትችላለች?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ አዘርባጃን COP-29ን በባኩ ስታስተናግድ ከ190 በላይ ሀገራት የተወከሉ ከ70 ሺህ በላይ ልዑካንን፣ የዓለም መሪዎችንና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን በብቃትና በስኬት አስተናግዳለች፡፡ ጉባኤው ለአየር ንብረት ፋይናንስ አዲስ የጋራ የቁጥር ግብ ላይ ታሪካዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው «አረንጓዴ አሻራ» ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከልና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን በመታገል ረገድ እውነተኛ የመሪነት ምሳሌ ሆናለች፡፡
አዘርባጃን ኢትዮጵያ COP-32ን ለማስተናገድ የምታደርገውን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ትደግፋለች፡፡ ሁለቱ ወገኖች በCOP32 ዝግጅት ትብብር ላይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፤ ይህም ትብብር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ግዮን፦ ኢትዮጵያ እጅግ ሰፊ፣ ወጣትና ንቁ ሕዝብ አላት፡፡ የአዘርባጃን መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ለከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ምን ዓይነት የትምህርት ዕድሎችን (ስኮላርሺፖችን) እና የትምህርት ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን ያቀርባል? ይህንን ለማስፋት ምን አቅዳችኋል?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ ይህ ለእኛ የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር ቅድሚያ የሚሰጠው መስክ ነው፡፡ የአዘርባጃን መንግሥት የ«ሄይዳር አሊዬቭ ዓለም አቀፍ የትምህርት እርዳታ ፕሮግራም»ን እንዲሁም በNAM እና በOIC በኩል የስኮላርሺፕ ዕድሎችን ዘርግቷል፡፡
በእነዚህ ፕሮግራሞች አማካኝነት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በአዘርባጃን ዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በትብብር እየሠራን ነው፡፡ ዋና ዋና የትምህርት መስኮቹም የሚከተሉት ናቸው፦
- የነዳጅ፣ጋዝ እና የታዳሽ ኃይል ኢንጂነሪንግ፤
- የሕክምናሳይንስ፤
- አይቲ፣ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፤
- ዓለምአቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ናቸው፡፡
ወደፊት ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የስኮላርሺፕ ቁጥሩን በይበልጥ ለማሳደግ እየሰራን እንገኛለን፡፡ ይህም በጋራ በምንሠራቸው የሁለትዮሽ ሰነዶች እንዲሁም የምናበረታታቸው በትምህርት ተቋማት መካከል በሚደረጉ ቀጥታ ግንኙነቶች ሊከናወን ይችላል፡፡ በቅርቡ የፓርላማችን አፈ ጉባኤ በኢትዮጵያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት (IFA) እና በአዘርባጃን የልማትና ዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት (IDD) መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ተመሳሳይ ሰነድ በባኩ ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መካከል ልንፈራረም እንችላለን፡፡
ግዮን፦ ከፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ባሻገር በሁለቱ ሀገራት መካከል ገና ያልተነካ ሰፊ የኢኮኖሚ አቅም አለ፡፡ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ማኅበረሰብ በቱሪዝም፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ ለማገናኘት ምን ዓይነት ስትራቴጂዎች ተዘርግተዋል?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ፖለቲካዊ ግንኙነት እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም፣ የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነታችን ግን ገና ያልተነካ ሰፊ አቅም ያለው ዘርፍ ነው። ይህንን ክፍተት ለመድፈን በኤምባሲያችን በኩል በርካታ እርምጃዎችን እየወሰድን እንገኛለን፦
- የንግድምክር ቤቶችን ማገናኘት፦ የንግድ ለንግድ (B2B) ቢዝነስ ፎረሞችን ለማዘጋጀት በአዘርባጃን የሚመለከታቸው አካላት እና በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መካከል ቀጥታ ትስስር መፍጠር፤
- የንግድተሟላችነት (Trade Complementarity)፦ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ቡና፣ አበባ፣ ሰሊጥና የእንስሳት ምርቶችን ታመርታለች፤ አዘርባጃን ደግሞ ማዳበሪያ፣ ፔትሮኬሚካሎችን፣ ካርቶንና የኬሚካል ምርቶችን ታመርታለች፡፡ እነዚህን ምርቶች ቀጥታ ለመለዋወጥ የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት ጥረቶች አሉ፤
- ቴክኖሎጂእና ዲጂታላይዜሽን፦ የአዘርባጃን የኢኖቬሽን እና ዲጂታል ልማት ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጥብቅ እየሰራ ይገኛል፤
- የቱሪዝምትስስር፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባኩ ቀጥታ የበረራ መስመር ለመክፈት የሚያደርገው ውይይት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ግዮን፦ በመጨረሻም፣ ክቡር አምባሳደር፣ ውይይታችንን ስናጠናቅቅ እስካሁን ያላነሳነው ሐሳብ ካለ አሊያም በማጠቃለያነት ሊያስተላለፍ የሚፈልጉት ሐሳብ ዕድሉን እንስጥዎት?
አምባሳደር ናሲቦቭ፦ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ! ዋናው መልዕክቴ፦ ኢትዮጵያና አዘርባጃን ረጅም የታሪክ መሠረት፣ የበለጸገ የባሕልና የሃይማኖት ብዝኃነት፣ እንዲሁም ለሀገራዊ ነፃነታቸውና ሉዓላዊነታቸው ያላቸው የማይወላወል ጽኑ አቋም የሚያስተሳስራቸው እውነተኛ ወዳጆች ናቸው፤ ሁለቱም ሀገራት የየራሳቸው ጥንታዊ ሥልጣኔና ታሪክ ያላቸው ሲሆን፣ የተለያዩ ሃይማኖቶችና ባህሎች በፍቅርና በመከባበር አብረው የሚኖሩባቸው የሰላምና የመቻቻል አርአያ ናቸው።
በሁለቱም አገራት መሪዎች የተጀመረው አዲስ ምዕራፍ ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኝ ሕያውና ጠንካራ ድልድይ ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ ይህ በጋራ እሴቶችና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተው ወዳጅነት ሁለቱን ሀገራትና ሕዝቦች ይበልጥ የሚያቀራርብና ወደተሻለ የልማትና የስልታዊ አጋርነት ደረጃ የሚያሸጋግር ሕያው መድረክ ነው እላላሁ። ይህ በአገሬ አዘርባጃንና በኢትዮጵያ መካከል የቆየው ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በጋራ እንሠራለን፡፡
ለግዮን መጽሔት ዝግጅት ክፍል ለዚህ ጥልቅ ቃለ-መጠይቅ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ብልጽግና እና ዕድገት እመኛለሁ! አመሰግናለሁ!
የዝግጅት ክፍሉ ማስታወሻ፦
ለአዘርባጃን ሪፐብሊክ ኤምባሲ እና ለክቡር ባለሙሉ ሥልጣንና ልዩ አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ ራፋኤል ለተደረገልን ሞቅ ያለ አቀባበል እና ለሰጡን ቃለ-መጠይቅ በዝግጅት ክፍላችን ስም የላቀ ምስጋናችንን እናቀርባለን፤ ግዮን መጽሔት በኢትዮጵያ እና በአዘርባጃን መካከል ያለው ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ይበልጥ እያበበና እየጠናከረ እንዲቀጥል መልካም ምኞቷን ትገልጻለች!!
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 235 ነሐሴ 2018 ዓ.ም
