አንተሁን ሙሉዬ
ከ19ኛው ሁለተኛ አጋማሽ እስከ 20ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ድረስ አፍሪካውያን በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ሥር እየማቀቁ ነበር፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ነጻነታቸውን መቀዳጀት የቻሉት እ.ኤ.አ በ1963 ነው፡፡ ይህም ዓመት የአፍሪካ ነጻነት አመት ተብሎ ይጠራል፡፡ ልክ እንደ ሌሎች አፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ስትማቅቅ ከነበረችውና ከቅኝ ግዛት በኋላ ደግሞ ከአፍሪካውያን ሀገሮች በተለያዩ ሀኔታ ሁለንተናዊ አመርቂ እድገት ስላስመዘገበችው ቦትስዋና እናወጋለን፡፡ ቦትስዋና እ.ኤ.አ ከ1885 ጀምሮ እስከ 1966 ድረስ በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ቁጥጥር ስር ነበረች፡፡ ቦትስዋና ከቅኝ ገዢዎቿ ወዲያኑ ነጻ ስትወጣ ራሷን ያገኘችው በአስከፊ ድህነት ውስጥ ነበር፡፡ ጠቅላላ አስፋልት የለበሰው የሀገሪቱ መንገድ 12ኪ.ሜ ብቻ ነበር፡፡ ከዩንቨርሲቲ የተመረቁ ጠቅላላ ዜጎቿ ብዛት 22 ብቻ ሲሆኑ የነበራት የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ብዛት ደግሞ 100 ነበር፡፡ ቦትስዋና ከቅኝግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ ለተከታታይ 45 ዓመታት በዓለም ላይ ፈጣን የሚባል እድገት አስመዝግባለች፡፡ ዛሬ ቦትስዋና ከሰብ ሰሀራን አፍሪካ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላት ሀገር ስትሆን ላለፉት 45 ዓመታት በተመሳሳይ ጊዜ ይህ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ እንደ ሀንጋሪና ኢስቶንያ ከመሳሰሉት የምሥራቅ አውሮፓ ሀገሮች ጋር እኩል የነበረ ሲሆን ከደቡባዊ አሜሪካዋ ኮስታሪካ ደግሞ በጣም የበለጠ ነበር፡፡
ቦትስዋና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ ሁኔታ ለምን አደገች? መልሱ ግለጽ ነው፡፡ ቦትስዋና ከቅኝ ግዛት በኋላ ሁሉን የሀገሪቱን ዜጋ አካታች የሆነ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋም ስለገነባች ነው፡፡ አካታችነት የሌለው ሀገር ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ አይችልም፡፡ ቦትስዋና ሁሉንም ማኅበረስብ አካታች የሆነ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተቋም ስለገነባች የእርስ በርስ ጦርነትና መፈንቅለ መንግሥት አድርጋ አታውቅም፡፡
የቦትስዋና ነጻነት የተመራው የቦስትዋና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (BDP) ሲሆን የተመሰረተው በ1960 ነበር፡፡ ኬቲ ማስሬ እና ሰርሴ ካም የድርጅቱ መሪዎች ነበሩ፡፡ መጀመሪያ ላይ የቦትስዋና ኢኮኖሚ የተመሰረተው የሥጋ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ነበር፡፡ ነገር ግን በሀገሪቱ ዳይመንድ ከተገኘ በኋላ በቦትስዋና ነገሮች ሁሉ በፍጥነት ተቀያየሩ፡፡ የመጀመሪየውና ትልቁ የዳይመንድ ክምችትም የተገኘው በሰርሴ ካም የትውልድ ስፍራ በሆነችው ንግዋቶ ላንድ ነበር፡፡ ዳይመንድ መገኘቱ ለቦትስዋናውያን ከመገለጹ በፊት ሰርሴ ካም በየትኛውም የቦትስዋና ግዛት የሚገኝ ማእድናት ሁሉ የሁሉም ቦትስዋናውያን ሀብት እንጅ የአንድ ጎሳ ብቻ መሆን የለበትም በማለት ከዚህ በፊት የነበሩትን ከፋፋይ የጎሳ ሕጎችና ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ቀየረው፡፡ ከዚህ ባሻገር ከዳይመንድ የሚገኘው ገቢ የቦትስዋና ሀገረ መንግስት ለማጠናከር ቢሮክራሲውን ለማዘመን፣ ትምህርትና መሠረተ ተቋማትን ለመገንባት መዋል ጀመረ፡፡
ከቦትስዋና በተቃራኒው ደግሞ በሴራሊዮንና በሌሎች ብዙ የአፍሪካ አገራት የተገኘው ዳይመንድ ለተለየዩ ቡድኖች ለእርስበርስ ጦርነት እንደ ነዳጅ ሆኖ አገልግሏል ፤ ለተራዘመው ደም አፋሳሽ ጦርነትና ለዘር ጭፍጨፋ ሳይቀር ዳርጓቸዋል፡፡ ይህም የሆነበት የቦትስዋና ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሰርሴ ካምን ጨምሮ በሕዝቡ ተቀባይነት ያላቸው ልሂቃን አምባገነናዊ ስርዓት ስላልመሰረቱና በሕዝቡ ኪሳራ ራሳቸውን የሚያበለጽግ በዝባዥ ተቋም ስላልመሰረቱ ነው፡፡
ኢትዮጵያስ ከቦትስዋናና ከሴራሊዮን ምን ትማራለች? ይህን ሐሳብ እንዳነሳ ያስገደደኝ ከዚህ በፊት የማዕድንና ኢነርጂ ሚንስትር ኢ/ር ታከለ ኡማ በኢትዮጵያ 7 ትሪሊዮን ሜትሪክ ኪዩብነዳጅ በኡጋዴን ላይ መገኘቱን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው፡፡ መገኘቱ እጅግ በጣም ደስ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟንና አንድነቷን ማስጠበቅ ከቻለች ተስፋ ያላትና የምታሳሳ ሀገር ነች፡፡ የኔ ሥጋት የነዳጅ ዘይቱን መገኘት ተከትሎ የውጭ ኃይሎች በተለይ የምዕራባውያን ሀገራት ጣልቃ በመግባት የውስጥ ሰላማችንን እንዳይበጠብጡንና በሀገር ጉዳይ ላይ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች የኔ የሚሉት ወይም የሚጠብቁት የጋራ የሆነ የሚያስማማ ሕገ-መንግሥት ሳይኖረን ልክ እንደ ሴራሊዮን ወደለየለት ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳንገባ ነው፡፡ በዓለም ላይ በአብዛኛው የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ሀገራት ሰላም የራቃቸው ናቸው፡፡ አንድ ሀገር የውስጥ ጉዳዮቿን በራሷ ካልፈታች፣ የተፈጥሮ ሀብት ስላላት ብቻ ታድጋለች ማለት አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ለአንድ ሀገር እድገት ያለው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ለማንም ሰው የተሰወረ አይደለም፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ ቦትስዋናውያን የነዳጅ ዘይት መገኘቱ ከመገለጹ በፊት የጋራ የሆነ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያስማማና በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት የሚገኝ የማዕድን ሀብት የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጂ የአንድ ጎሳ ብቻ መሆን የለበትም የሚል ሕግ ካልተረቀቀ በስተቀር፣ ነገ ነዳጅ ዘይት ወይም ዳይመንድ አልያም ፕላቲኒየም ያገኘ ክልል ወይ “የኔ ብቻ ነው” አልያም “እገነጠላለሁ” ላለማለቱ ምንም ዋስትና የለም፡፡
በውስጥ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ካለ፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት አይኖርም፡፡ ቢኖር እንኳ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩና አንድ ከሆኑ ጣልቃ ገብነቱን ማስቆም ወይ መከላከል ይችላሉ፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚኖረው እኛ ኢትዮጵያውያን ስንከከፋፈል ብቻ ነው፡፡
ሌላው አንድ የሚገርመኝ ነገር በዓድዋ ጦርነት የተሳተፈው ጣሊያናዊው ጀነራል ባራቴሪ በስካን በመወከል ለ20 ዓመታት የኢጣሊያ ፓርላማ አባል ነበር፡፡ በስካ ማለት ጣሊያን ውስጥ የሉምራዲ ዋና ከተማ ናት፡፡ ባራቴሪ ከ20 አመት በኋላ የኢጣሊያን ፓርላማ ሲለቅ አንድ መልእከት አስተላልፎ ነበር፡፡ መለእክቱም “men pass, the nation’s remains” የሚል ነው፡፡ ባራቴሪ ሰዎች ያልፋሉ ሀገር ግን ይቀጥላል ነበር ያለው፡፡ የባራቴሪን አባባል ብዙ ኢትዮጵያውያን ሀሳቡን ገዝተው ሲናገሩት ይስተዋላል፡፡ ዳሩ ግን ባራቴሪ እንዳለው ሳይሆን በፖለቲካ ልሂቃን አለመግባባት ምክንያት ሀገርም ሕዝብም የማይቀጥልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግሥት ምስረታ ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ እስከምትገነጠል ድረስ፣ የኤርትራ ታሪክ አንዱ የኢትዮጵያ የታሪክ ክፍል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ኤርትራ በተመድ እውቅና አግኝታ እንደ ሀገር መቆም ከጀመረች ከሦስት ዐሠርት አመታት በላይ አስቆጥራለች፡፡ ዛሬ ላይ ከ30 ዓመት በኋላ የተወለደ ኤርትራዊና ኢትዮጵያዊ ያላቸው የሥነልቦና ማንነት አንድ ዐይነት አይደለም፡፡ ኤርትራዊው በአሁኑ ሰዓት ጥልቅ የሆነ የሀገር ፍቅር ስሜትና ታማኝነት የሚኖረው ለኤርትራ እንጅ ለኢትዮጵያ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም እንደ ኤርትራዊ ሀገር መኖርና ማሰብ ከጀመሩ 30 ዓመት አልፏቸዋል፡፡ አንባቢየንን ማሰልቸት ይሆንብኛል እንጂ ሌላም ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡
