ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ ጋር ጦርነት ውስጥ ትገበላች መባሉን ውድቅ ማድረጓን ስፑትኒክ ዘግቧል፡፡
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 6ኛው የፓን አፍሪካ ፓርላማ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን የወከለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፓን አፍሪካ ቡድን፣ የግጭት መከላከል ቅድመ ማስጠንቀቂያ የአቻ ግምገማ ላይ በአንድ ጽሑፍ አቅራቢ ለተነሳው ሐሳብ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያና ግብፅ ድንበር እንደማይጋሩ የሞገቱት የልዑኩ አባል ዶ/ር አወቀ አምዛዬ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ምንም ዓይነት የድንበር ግጭት እንደሌለና ግድቡም የግጭት ምንጭ ሊሆን እንደማይችል አበክረው ገልጸዋል።
“ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉት ኢትዮጵያን አግልሎ የአባይን ውሃ የመጠቀም ሙሉ መብት ግብፅ እንድትጎናፀፍ የሚያደርጉ በብሪታንያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል የተደረጉ ጊዜ ያለፈባቸው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ናቸው” ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረትና የፓን አፍሪካ ፓርላማ እነኚህ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዙ ብርቱ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም ዶ/ር አወቀ አምባዬ አሳስበዋል።
