‹‹እኛን በኢኮኖሚ አዳክሞ መጣል ይፈለጋል››
‹‹ድርጊቱ በሃይማኖት አባቶችና በሃይማኖት ሰዎች ጭምር እየተፈጸመ ነው››
ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ ነጋሽ (ዘወይንዬ)
የዛሬው የመጽሔታችን እንግዳ ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ ነጋሽ ነው፡፡ መምህር ደረጀ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለማችንም ኾነ በሀገራችን እየተስፋፋ የመጣውን የግብረሰዶም እንቅስቃሴ ለማስወገድ እና በድርጊቱ የተጎዱ ዜጎችንም ለመርዳት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ የፊታችን ጳጉሜ ዐራት ዓመት የሚሞላው ማኅበራቸውም በዚህ ረገድ ሰፋፊ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ ስለችግሩ አሳሳቢነት እና መጨመር፣ በመንግሥትና በሃይማኖት ተቋት በኩል እየታዩ ስላሉ ክፍተቶች እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ እነኾ!
ግዮን፡- ራስህን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ እና ተቋማችሁ መቼ እንደተመሠረተ ከመግለጽ ብትጀምርልን?
ደረጀ፡- ሥሜ ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ ነጋሽ ዘወይንዬ እባላለሁ፡፡ የ‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም ፤ ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ ማኅበር›› መሥራችና ፕሬዝዳንት ነኝ፡፡ ማኅበሩ የተመሠረተው ጳጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ነው፡፡ በመጪው ጳጉሜ 4 ዓመት ይኾነዋል፡፡ ማኅበራችን በተጠቀሰው ተግባር የሚንቀሳቀስ በዓለም ላይ ብቸኛው ማኅበር ነው፡፡ ዓለም ላይ ግብረሰዶምን የሚያስፋፉ እንጂ የሚቃወሙ ማኅበራት የሉም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ‹‹ኢንተርናሽናል ሌዚቢያን አንድ ጌዬ አሶሴሽን” (ILJA) የሚባል ግብረሶዶምን የሚደግፍ ማኅበር አለ፡፡ ከተመሠረተ 45 ዓመት አልፎታል፡፡ ከአንድ ሺህ በላይ ቅርጫፎች አሉት፡፡ ተግባሩም ግብረ ሰዶማውያኑን ማገዝ ነው፡፡ የእኛ ማኅበር ግን ግብረሰዶማዊያንን የሚቃወም ነው፡፡ ያ በመኾኑም ነው የእነትራምፕ ሚዲያ ሳይቀር አሶሴሽን ፕሬስን ጨምሮ በርካታ ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች የምሥረታችን ወቅት ሽፋን ሰጥተው የዘገቡት፡፡ የማኅበራችን ዓላማ ጥቃትንና መደፈርን መቃወም፤ ከዚያም ሕይወት እንዲወጡና እንዲታገዙ ማድረግ ነው፡፡ የሰብዓዊነት ሥራንም እንሠራለን፡፡ በዋናነት ግን ግብረሰዶምን የሚቃወም ማኅበር መሥርቶ ችግሩን መቋቋም እንደሚቻል ለማሳየት የሚሞክር ነው፡፡ በዚህም ለተጎጂዎች የሕግ፣ የሥነልቦና እና መሠል አገልግሎቶች እንሰጣለን፡፡ በተጨማሪም ለተጎጂዎች ሙያዊ ሥልጠና በመሥጠት ለማገዝ እንሞክራለን፡፡ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግም እንሞክራለን፡፡
ግዮን፡- ማኅበሩ ከተቋቋመ በኋላ ‹‹ሠራን›› የምትሉት ውጤታማ ሥራ ምንድነው?
ደረጀ፡- የመጀመሪያው በጣም የተጎዱና ግብረሰዶም የተፈፀመባቸው ልጆች ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመኾን በኢኮኖሚ እንዲታገዙ ማድረጋችን ነው፡፡ በዚህም ቤተሰቦቻቸው ሙያዊ ሥልጠና እንዲወስዱና ራሳቸውን እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ የሥነ-ልቦና ሕክምና እነ ፕሮፌሰር በቀለን ጨምሮ እየረዱን ሲሰጥ ነበር፡፡ የአእምሮ ጭንቀት የነበረባቸው፣ የማይተኙ፣ የማይማሩ፣ እንዲሁም ሁሉም ነገር የሚያስጠላቸው ልጆች ወደ ጤንነታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዐቃቢ ሕግ፣ ፖሊስ፣ ሰላም ሚኒስቴር እና ከሌሎችም ጋር የጋራ ስብሰባ በማድረግ በፊት ቅጣቱ ቀላል የነበረውን የግብረሰዶም ወንጀል የ18 እና 15 ዓመት መቀጮ እንዲኖረው አስደርገናል፡፡ ሌላው ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቢሠራ ውጤታማ ሊኾን ይችላል ብለን ያሰብነውን ምክረ ሐሳብ ለሰላም ሚኒስቴር አቅርናል፡፡ ሃያውንም ሚኒስቴር መሥሪያ መሥሪያ ቤት ብንጠራም፣ ዐሥሩ ተገኝተው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ሰጥተናል፡፡ ውይይቱን ያካሄድነውም ኤሊያና ሆቴል ሲኾን፣ ያለንበትን ደረጃ በደንብ የሚያሳይ ውይይት ነበር ያደረግነው፡፡ በሌላ በኩል የተጎዱ ሰዎች ቢሮ ድረስ በመምጣት የምክር አገልግሎት የሚያገኙበት እና የሚበረታቱበትን ሁኔታ ፈጥረናል፡፡ በአጠቃላይ ማኅበራችን ለተጎዳው ሕዝብ የቆመ ማኅበር ነው፡፡
ግዮን፡- ለማኅበራችሁ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት አሉ?
ደረጀ፡- በመንግሥትም ኾነ በሃይማኖት ተቋማት ደረጃ ድጋፍ አልተደረገለትም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ግን በርካታ ድጋፎች ተደርገውለታል፡፡ ግለሰቦች በሚያደርጉት አስተዋጽዖ ነው ማኅበሩ እየሠራ ያለው፡፡ ሁለት ዓመት የቤት ኪራይ ነፃ ያደረገልን የአልፎዝ ሕንፃ ባለቤት አቶ ዓሊ ነው፡፡ የሠራተኞች ደሞዝ መክፈል ሲያቅተንም የደረሰልን አቶ ወርቁ አይተነው ነው፡፡ ስለዚህ የማኅበራችን ወጪ እየተሸፈነ ያለው በግለሰቦችና ዓመታዊ በዓል ላይ በሚገቡ ቃልኪዳኖች ነው፡፡ የዛኑ ያህል በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ቃል ተገብቶልን ሳይሰጠን የቀረበት ሁኔታም አለ፡፡ እንዲህ ዐይነት ተቋም በጣም ሊታገዝ የሚገባው ነው፡፡ በመጀመሪያ ተቋሙ የዓለማችን ብቸኛ ተቋም ነው፡፡ ትውልድ ጨራሽ የኾነ በሃይማኖት የተወገዘና በሕግ ወንጀል የኾነውን ግብረሰዶምን የሚታገል ተቋም ነው፡፡ ይህን ተቋም በርብርብ ማገዝ ይገባል፡፡ ችግሩ ሁሉም ቤት እያንኳኳ ነው፡፡ እኛ እንደውም የምናገለግለው በነጻ ነው፡፡ ሥራ አስኪያጅ ቢቀጠር ተጨማሪ ወጪ ይጠይቀናል፡፡ ለምሳሌ የአንድ ዓመት የጸሐፊ ደሞዝ የሸፈነልን አቶ ትዕዛዙ ነው፡፡ አቶ ትዕዛዙ ማለት የዮድ አቢሲኒያ ባለቤት ነው፡፡ በጥቅሉ ግለሰቦች በሚረዱን እንጅ እንደተቋም የሚረዳን አካል ኖሮ አይደለም እየሠራን ያለነው፡፡
አንድ ዓመት የምንሰበሰበው እኔ ቢሮ ውስጥ ነበር፡፡ እኔ ቢሮ ውስጥ መሠብሰብ ያቆምነው የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከደረሱልን በኋላ ነው፡፡ በርካታ ተግዳሮቶች አሉብን፡፡ እኛን በኢኮኖሚ አዳክሞ መጣል ይፈለጋል፡፡ ባለፈውም ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ያዘጋጀነው ፕሮግራም እንዳይካሄድ ተደርጓል፡፡ አዳራሹንም ‹‹ለሌላ ሰው ተከራይቷል›› በሚል ነው የተከለከልነው፡፡ መንግሥትም አንድ ፕሮግራም ለማካሄድ 19 ቀን የፈጀ ቢሮክራሲ አካሂዶብናል፡፡ ፕሮግራሙ እንደነገ ሊካሄድ እንደዛሬ ከሰዓት ነው ግንቦት 23 ቀን የፈቃድ ወረቀት የሰጠን፡፡ እኛኮ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ አይጠበቅብንም ነበር፡፡ ነገር ግን የተሰጠን ፈቃድ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍም ቢኾን ማሳወቅ እንጂ ፈቃድ አያሻውም፡፡ ነገር ግን ከንቲባ ቢሮ ሁለት ጊዜ፤ ፖሊስ ኮሚሽን ሁለት ጊዜ፤ ፌደራል አንድ ጊዜ ሄደን ነው በመጨረሻ ፈቃዱን ያገኘነው፡፡ ያም ኾኖ በመጨረሻ ፕሮግራሙ ተሰርዞ ለሌላ ቀን ተላለፈ፡፡ ፕሮግራሙ ግንዛቤ ማስጨበጫ ነበር፡፡ የኾነ ኾኖ አሁን ያለው እንቅቃሴ ጥሩ ነው፡፡
ግዮን፡- በቀጣይ በጣም የሚስፈልጋችሁ እገዛ ምንድነው?
ደረጀ፡- የምንፈልገው እገዛ ሁለገብ ነው፡፡ በተቋም ደረጃ የሚሠራ ሥራ ተቋማዊ አስተሳሰብ ያስፈልገዋል፡፡ ይኽን ጉዳይ እኔ የጀመርኩት የዛሬ 15 ዓመት ነው፡፡ ብቻዬን ስታገል ቆይቼ ‹‹ዘወይንዬ አቡነ ተክለሃይማኖት›› ወደሚባል ማኅበር አመጣሁት፡፡ ‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም›› በማለት ደብዳቤ ጽፌ በወቅቱ ለነበረው ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስገባን፡፡ በአስገባነው ደብዳቤ መሠረት 6 ኪሎ ስብሰባ ማዕከል አስፈቅደን በማኅበር በመሰብሰብ ማኅበሩ እንዲመሠረት ተደረገ፡፡ ይኽ ማኅበር ተቋም ሲኾን ከሃይማኖትና ፖለቲካ ነጻ ተቋም ነው፡፡ ያ ከኾነ ደግሞ አሳታፊ መኾን ስላለበት ራሱን ማሳደግ ይገባዋል፡፡ ‹‹ማኅበረ ወይንዬ›› ሃይማኖታዊ ስለኾነ ሌላው እንዳይሳተፍ ያደርገዋል፡፡ ማኅበሩም በኢኮኖሚ መታገዝ ስላለበት ዓመታዊ በዓላችንን ጳጉሜ ላይ ስለምናደርግ በጣም ሊያግዙን ይገባል፡፡ የሕግ ባለሙያዎች እና የጤና ባለሙያዎች አብረውን ገብተው ሊያግዙንና በጋራ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ማንኛውም ሰው ነፃ ተቋም ስለኾነ አግዞን ትውልዱ ላይ ካልሠራን ወደፊት በጣም አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡
ግዮን፡- ታዲያ ምን ያህል ጥሪ አድርጋችኋል?
ደረጀ፡- እያደረግን ነው፡፡ በየክፍለሀገሩም ሥራው መከናወን ይኖርበታል፡፡ አዲስ አበባ በራሷ ሰፊ በመኾኗ ትልቅ ሥራ ማከናወን ይገባናል፡፡ የሕግ ባለሙያው፣ የጤና ባለሙያው፣ በኢኮኖሚም ጭምር ሙያተኞች ሊያግዙን ይገባል፡፡ ቢሮዎች በተለያየ ቅርንጫፍ ሊከፍቱ ይገባል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ክፍለ ሀገር ቀርቶ አዲስ አበባ ራሱ በጣም መሠራት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ የሁሉም ሕብረተሰብ ክትትልና ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡
ግዮን፡- ወደ አንተ እንመለስና፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እንድትሠራ ያነሳሳህ ነገር ምንድነው?
ደረጀ፡- እኔ በመጀመሪያ እሠራ የነበረው በገዳማት ታሪክ ዙርያ ነበር፡፡ የገዳማትን ታሪክ በመመራመር 21 ዓመታትን ቆይቻለሁ፡፡ ከ100 በላይ በሚኾኑ ገዳማት ታሪክ ላይ በመሥራት በብቸኝነት የምታውቅ ግለሰብ እኔ ነኝ፡፡ ከ36 ዓመታት በላይ በርካታ ገዳማትን ዞሬ አይቻለሁ፡፡ የኾነው ኾኖ የምሠማውና የማነብበው ነገር በጣም ለጆሮ የሚከብድ ስለኾነ ጉዳዩን መከታተል ጀመርኩ፡፡ የተለያዩ ነገሮችን ማንሳት ስጀምር ደግሞ ነገሩ ከባድ መኾኑን ተረዳሁ፤ በዚህም የችግሩን መኖር አለመኖር፤ ማንን እንደሚያጠቃ፤ ወዘተ… ማጥናት ጀመርኩ፡፡ በ2003 ዓ.ም ዮሴፍ የማነ ብርሃን የሚባል ኤርትራዊ የግብረ ሰዶም አስፋፊ የነበረን ግለሰብ ሽመልባ ኤርትራ ስደተኞች ካምፕ በመሄድ ቀረጽኩት፡፡ እሱም ግብረሰዶምን በምሥራቅ አፍሪካ እንዴት እንደሚያስፋፋ በዝርዝር ተናገረ፡፡ ይኼን ካደረኩ በኋላ ‹‹ግብረሰዶም እየተስፋፋ ነውና እባብን በእንጭጩ ነውና የሃይማኖት አባቶቻችን እና መንግሥት ትኩረት ይስጡ›› ብዬ ቪዲዮውን አቀረብኩ፡፡
ልጁ በቪዲዮ እየታየ ነበር የተናገረው፡፡ ቀጥሎ በ2005 ‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አልልም›› የሚል ቪሲዲ ሠራን፡፡ የግብረሰዶማውያን ፓርቲ ጭፈራቸውን ሄደን በመቅረፅ በስምንት ዓመታቸው ገብተውበት 32 ዓመታት እዚያ ውስጥ የቆዩትን ልጆች በመቅረጽ ‹‹ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ›› የሚል ሴቶችም ወንዶችም ችግሩ ውስጥ ያሉ ልጆች የሰጡትን መረጃ ጭምር በቪዲዮ አቀረብን፡፡ በዚህም አልመለስ ሲል ቀጥሎ ወደ ‹‹ማኅበረ ዘወይንዬ›› ከዚያ ‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አልልም›› የሚለውን መሠረትኩ፡፡ ባደረግኩት 19 ሀገራት ጉዞ ዙሪያም ብዙ ነገር ሠርቻለሁ፡፡ አሜሪካ ብቻ 12 ጊዜ ሄጃለሁ፡፡ ሕጉ ላይ ያልተካተቱ ብዙ ነጥቦች እንዲካተቱ ብዙ ሐሳቦችን አቀርቤያለሁ፡፡ ለምሳሌ፡- ጾታዊ ቅየራው በውጪ ሀገር ግብረሰዶም ነው፡፡ በእኛ ሀገር ግን በሕግ ደረጃ ያልተካተተ ነው፡፡ የግብረሰዶም ዓይነቶች የተለያዩ መኾናቸውም ከግምት እንዲገባና እንዲሁም በቢጋሩ ላይ ያሠፈርነው ከዚያ ለመማር ነው፡፡ በጥቅሉ ወደዚህ ሥራ የገባሁት ከማየውና ከምሠማው በመነሳት ነው፡፡
ግዮን፡- በቅርቡ የሰጣችሁት ጋዜጣዊ መግለጫ ምን ላይ የሚያጠነጥን ነው?
ደረጀ፡- ሰሞኑን የሚታዩ ነገሮች ጥሩ አይደሉም፡፡ ‹‹ጾታ አንለይም›› የሚል ሆስፒታል መገኘቱን ነገሩን፡፡ ወንዱ ቀሚስ ለብሶ፣ ጡት ማስያዛ አድርጎ፣ ቦርሳ ይዞ ፋሽን ሾው ሲያሳይ አሳዩን፡፡ በሆቴል ደረጃ አንተ አንቺ አይባልም በሚል በተለይ ሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ያሰበውን ንግድ ባንክ ላይ ሬስቶራንት ሊከፍት መኾኑን መጥተው ነገሩን፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በፊትም አያያዛቸው የተለያየ ፓርቲ ከሚያደርጉ ሌሎች ክለቦች ጋር አያይዘን ባለ 15 ነጥብ ያለው የዐቋም መግለጫ እንድናወጣ አደረገን፡፡ ሁሉንም ሕብረተሰብ የሚነካ ነው ችግሩ፡፡ የመንግሥት ቸልተኝነት ነው ለዚህ ያደረሰን፡፡ ቤተ ዕምነቶችም ሥራ እየሠሩ አይደለም፡፡ የበጎ አድራጎት ተቋማትም መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ እንደ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉ ተቋማት አንድ ጋዜጠኛ ሲታሠር መግለጫ ያወጣሉ፤ እንዲህ ዓይነት ግብረ ሰዶማዊ የሰብዓዊ ጥሰት በሕጻናቶች ላይ ሲፈፀም አንድም ቀን ተናግረው አያውቁም፡፡ መግለጫም ሰጥተው አያውቁም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢኾኑ ሀገር ሲኖር ነው መምራት የሚችሉት፡፡ የውጭው ዓለም ዴሞክራትም ይሁን ሪፐብሊካን ደግፈው ወይም ተቃውመው ይወጣሉ፡፡
እኛ ሀገር ግን በፀጥታ ነው የሚያልፉት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዚህ ላይ አቋማቸውን እንዲገልፁ፤ የሰላምን ጉዳይም በተመለከተ ሁሉም ፊቱን ወደ ሰላም እንዲያዞር በአጠቃላይ በጀመርነው ሥራ ላይ ሁሉም ትኩረት እንዲሠጠው ጥሪ አቅርበናል፡፡ ወደፊት ሰላማዊ ሰልፍ እንደምናደርግና መንግሥትም በአዎንታዊ መልስ እንዲሠጠን፣ ሕዝቡም ከጎናችን እንዲኾን ባለ 15 ነጥብ የዐቋም መግለጫ ጥሪ አድርገናል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው በጣም ተደራሽ ኾኖ የሕዝቡን ልብ አስከፍቷል፡፡ በየኮንዶሚኒየሙ፣ በየእንግዳ ማረፊያው፣ በየመታጠቢያ ቤቱ ያለውን ኹነት ተከታትሎ እርምጃ ይወሰድ የሚለውም ሐሳብ መድረስ ችሏል፡፡ በዚህም ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አንድ ቤት ታሽጓል፡፡ የታሸገበት ምክንያት በግብረሰዶማዊያን ጭፈራ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን ቤቱን ከማሸግ ውጪ ግብረሰዶማውያኑ ጨፋሪዎቹ ላይ እርምጃ አልተወሰደም፡፡ ለምን? ሰዎቹ የድርጊቱ ፈጻሚዎች እስከኾኑ ድረስ እርምጃ መወሰድ ነበረበት፡፡ ከዚህ አንጻር ፖሊስ በወቅቱ የወሰደው እርምጃ ወቅታዊና አጀንዳ ማስቀየሪያ እንዳይኾን ያሰጋል፡፡ እኛ ዘላቂ መኾን ይኖርበታል ነው የምንለው፡፡
ግዮን፡- በዚህ ወንጀል የተሳተፉ አካላት የሚያገኙትን ሕጋዊ ቅጣት የምትከታተሉበት የራሳችሁ መንገድ አላችሁ?
ደረጀ፡- ከዚህ በፊት ባደረግነው የጋራ ስብሰባ ላይ ገልፀን ነበር፡፡ ሰዶማውያን የት አካባቢ እንዳሉ፣ ምን ምን እንደሚያደርጉ እንገልፃለን፡፡ ችግሩ ግን ሕጉ ቢኖርም ተግባራዊ አይደረግም፡፡ ምክንያቱም በእርዳታ ሰበብ ግብረሰዶማውያንን ተጠያቂ ለማድረግ ዳተኝነት አለ፡፡ የሚገርመው በኮቪድ ወቅት ግብረሰዶማውያን ሬሽን ሳይቀር ይሰጣቸው ነበር፡፡ ወንጀለኛ እንዴት ሬሽን ያገኛል? ይኼንንም ተናግረናል፡፡ ነገር ግን የሚያስቆምም የሚጠይቅም አካል የለም፡፡ አሁንም ማኅበራዊ ሚዲያው በጣም ስለጮኸ ነው ፖሊሶችም ትኩረት የሰጡት፡፡ በዚህም ጥቂትም ቢኾን እርምጃ ሊወስዱ ችለዋል፡፡ ቀድሞውንም ግን ሊያነቃ የሚገባው መንግሥት ነበር፡፡ ልክ ኮቪድ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሠራው በዚህም ጉዳይ ላይ በደንብ መሥራት ነበረበት፡፡ ከዚህ ቀደም ግብረሰዶማውያን ከችካጎ 7900 ዶላር ከፍለው ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነበር፡፡ ለመኾኑ ሊመጡ የነበረው ከማን ጋር ተነጋግረው ነበር? ማንስ ነበር ያንን ዋጋ ያወጣው? የኢትዮጵያ አየር መንገድስ እንዴት ተመረጠ? የት የትስ ያርፍ ነበር? ሕዝቡ ተቆጥቶ ባይነሳ ኖሮ ተስማምተው ሊያደርጉት ነበር ያሰቡት፡፡ በወቅቱ በጣም ታግለን ነበር፡፡ በግሌ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ በመናገሬ ፓትርያሪኩ አወገዙ፡፡ በተመሳሳይ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ላይ ተገኝቼም መምህር ታጋይ ታደለን አናግሬ እንዲወገዝ ተደረገ፡፡ ብሎም ከአስጎብኚው ኃላፊ ጋር ቢቢሲ ላይ በጣም ተከራክረን ነበር፡፡ እሱ ‹‹ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ እንፈጥራለን ፤ አንቀርም›› ሲል እኔ ደግሞ ‹‹ከመጡ አደጋ ይገጥማቸዋል›› ብዬ ስናገር ነበር፡፡ ያኔ ገና ማኅበሩ አልተመሠረትም ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ መቅረታቸው ሲታወቅ እነ ታከለ ዑማ ፕሮግራም አዘጋጅተው ጠርተውን ‹‹ቀርተዋል›› በማለት ተናገሩ፡፡
ታከለ ‹‹ቀርቷል›› ያለው ግን ነገሩ ካለቀ በኋላ ነበር፡፡ ታዲያ መጀመሪያ ከማን ጋር ነበር ስምምነት አድርገው ሊመጡ የነበረው? የኛ ባለሥልጣናት ለምንድነው እንደዑጋንዳው ፕሬዝዳንት ወጥተው የማያወግዙት? እስካሁን አንድ ሚኒስትር ይኽን ነገር አውግዞ አያውቅም ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሲያወግዙ አላየንም፡፡ ፑቲን እኮ ወጥቶ አውግዟል፡፡ ስለዚህ ሆይሆታው ጊዜያዊ አይሁን፡፡ ግብረሰዶምን ፖለቲካ አናድርገው፡፡ ድምፅ አልባ ገዳይ መኾኑን አውቀን በዘላቂነት እንዲጠፋ መሥራት አለብን፡፡ እኔ ማኅበሩን በመሠረትኩበት ወቅት ሰነዱን አውጥቼ ‹‹ዩኔስኮ 75 ሚሊዮን ዶላር ብር መድቦ ግብረሶዶምን እያስፋፋ ነው፡፡ 3 ሺህ ዶላር ተከፍሎ ሥልጠና እየወሰዱ ነው›› ብዬ ተናግሬያለሁ፡፡ በወቅቱ ሚኒስትሩ ተገርመው ነበር፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ተግባራት በመንግሥት ሥራ ደረጃ ሲሰጥ መንግሥትም ራሱ የት ነበር? አሁንም ቢኾን እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮም በ2008 ያስጠናው ጥናት አለ፡፡ ጥናቱን አጥንቶ ዶክመንቱን አስቀምጦታል፡፡ ለምን እርምጃ አልተወሰደም? አሁንም ሁላችንም ተበረታተን ጠንካራ ኾነን ይኼ ነገር ከሀገራችን እንዲጠፋ መትጋት አለብን፡፡
ግዮን፡- ሀገራችን በሃይማኖታዊ ሥርዓት እና ሥነልቦና ታንጻ የኖረች ሀገር ከመኾኗ አንፃር ኢትዮጵያዊ ግብረሰዶማዊነት እንዴት ሊያስፋፋ ይችላል? ለሚሉ ሰዎች ምን ትላለህ?
ደረጀ፡- የመጀመሪያው ጉዳይ የእርዳታ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደሀ ሀገር ነች፤ ሀገራችን የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ በእርዳታ ሰበብ የሚመጡ ናቸው የችግሩ ምንጭ የኾኑት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የመከላከል አቅማችን ደካማ መኾን እንዲስፋፋ እድል ሰጥቶታል፡፡ በ2003 ግብረሰዶማውያን ብዛታቸው 13 ሺህ ነበር፤ በ2005 ደግሞ 30 ሺህ ገቡ፤ ከአራት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት ደግሞ 100 ሺህ ደርሰዋል፡፡ ይኽን ያህል በቀላሉ ሊስፋፉ የቻሉት ወንጀሉን የሚከላከል አካል ባለመኖሩ ነው፡፡
ግዮን፡- የተጠቀሰው ጾታ የኢትዮጵያውያን ነው? እንዴትስ ማወቅ ተቻለ?
ደረጀ፡- አዎ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ነው፡፡ ዳታ ስንሠራ በመጠይቅ ነው፡፡ በመጠየቅ እዚያ ሕይወት ውስጥ ያሉ ሰዎችን፤ ከዚያ ሕይወት ውስጥ የወጡ ሰዎችንም፤ እንዲሁም እነርሱ የሚያውቋቸውን ሰዎች በመጠየቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ሴተኛ አዳሪዎች በቅርበት ይተዋወቃሉ፡፡ ስለዚህ እነርሱ የሚሠጡን ዳታ አለ፡፡ ያንን ዳታ ይዘን ነው የምንሠራው፡፡ በየጊዜው ለምንድነው ቁጥራቸው የሚጨምረው ሲባል ወንጀል የሚከላከል አካል ስለሌለ ነው፡፡ አንዴ አውሮፓ ላይ የእነሱን ባንዲራ ይዞ የወጣ ሶዶማዊ ‹‹የኢትዮጵያን መንግሥት እናመሠግናለን እንድንስፋፋ ረድተኸናልና›› ነው ያለው፡፡ የድግስ ፓርቲ ሲሠሩ፤ ተጋብተው ሲሄዱ፤ እንደልባቸው ሲኾኑ ምንም ዐይነት ቁጥጥር የለም፡፡ አንድ ፈረንጅኮ ሁለት ኢትዮጵያዊ ወንዶችን አቅፎ አድሯል ፤ በሆቴል፡፡ ቱሪዝም ሚኒስቴር ምንም ዐይነት ቁጥጥር አያደርግም፡፡ በውጪው ዓለም የትኛውንም ሀገር ስንጎበኝ በጥብቅ ቁጥጥር ነው፡፡ ከኤርፖርት ጀምሮ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ክትትል ይደረግበታል፡፡ እኛ ሀገር ግን ቱሪስቱ እንደፈለገ ሲኾን ማንም የሚቆጣጠረው አካል የለም፡፡ በጥቅሉ ቸልተኝነት ስለበዛ ነው እዚህ ደረጃ የተደረሰው፡፡
ግዮን፡- የሃይማኖት መሪዎች እና አባቶች ምን ያህል የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ?
ደረጀ፡- ምንም ዐይነት ነገር እያደረጉ አይደለም፡፡ አንዴ ከማውገዝ የዘለለ የሠሩት ነገር የለም፡፡ ይኽን ነገር የሚፈጽሙት ሰዎች ሃይማኖት አላቸው፡፡ በሃይማኖታቸው ታንጸው ቢኾን ኖሮ ይኽን ነገር አያደርጉም ነበር፡፡ ስለዚህ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ሌላው ቀርቶ ድርጊቱ በስፋት እየተፈጸመ ያለው ቤተ ዕምነት ውስጥና አካባቢ መኾኑ ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ ድርጊቱ በሃይማኖት አባቶችና በሃይማኖት ሰዎች ጭምር እየተፈጸመ ነው፡፡ ስለዚህ አልተሠራበትም፡፡ አንዴ ያወግዛሉ ከዚያ በኋላ ይረሱታል፡፡ ሥነ ምግባርን ማረቅና ማነጽ ያለበት ሃይማኖት ነው፡፡ ትውልድ በሁለት መንገድ ነው የሚታነፀው፡፡ የመጀመሪያው በሃይማኖት ትምህርት ቤት ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ በመደበኛው ትምህርት ቤት ነው፤ ከዚህ አንጻር ምንም የተሠራ ነገር የለም፡፡ ይኼ በታሪክም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡
ግዮን፤- በሀገራችን ያለው የግብረሰዶማውያን መቅጫ ቢሻሻል በመንግሥት ላይ የሚያሳድረው ዓለም አቀፍ ጫና ምንድነው?
ደረጀ፡- እርዳታ እናቆማለን ነው የሚሉት፡፡ ሌላ የሚያመጡት ነገር የለም፡፡ ስለዚህ እንደዑጋንዳ ዐይነት ጠንካራ አቋም ይዞ መቅረብ ነው፡፡ ለምሳሌ ጎግል ሲደረግ ከ10 ግብረሰዶም ተቃዋሚ ሀገሮች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ የለችም፡፡ ለምንድነው ኢትዮጵያ ከእነ ጋና ያነሰችው? ሀብታም ሀገራት ድርጊቱን ይቃወማሉ፡፡ አሜሪካን ሀገርም 4.5 በመቶው ነው ግብረሰዶምን የሚቀበለው፡፡ ከ300 ሚሊዮን ውስጥ ግብረሰዶምን የሚቀበለው ጥቂቱ ነው ፤ 95.5 በመቶው አይቀበልም፡፡ ሕጉ ቢሻሻል እርዳታዎች እንደማያደርጉ ነው የሚገልጹት፡፡ ያ ካልኾነ ደግሞ ግብረሰዶምን ከሚቃወመሙ ሀገራት ጋር ግንኙነት ማድረግ ይቻላል፡፡ አሜሪካ አልረዳም ብትል ከሩሲያና ቻይና ጋር ግንኙነት ቢደረግ ጠንካራ አቅም ያላቸው ሀገራት ስለኾኑ ያግዙናል፡፡ የእኛ ትልቁ እርዳታ ግን ከሰማይ ነው፡፡
‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› ነው የሚለው ቃሉ፡፡ ዛሬ እርዳታ የሚሰጡ ሀገራት ትላንት ተረጂ ነበሩ፡፡ የእኛ ታሪክ የ5ሺ ዓመት እንጂ የ50 ዓመት አይደለም፡፡ ገንዘባችን በኃይለሥላሴ ጊዜ ዶላር ነበር፡፡ በደርግ ጊዜም አንድ ዶላር 2.7 ብር ይመነዘር ነበር፡፡ ስለዚህ የወደቅነው እርዳታ ስንጠብቅ ኃጢአት ስለበዛብን ነው፡፡ ራቁት ጭፈራ፣ የድንግልና ጨረታ፣ ሺሻ ቤት፣ መጠጥ ቤት ሲኾን ነው ትውልዱ የጠፋው እና በረከት ያጣነው፡፡ ኮቪድ ከጨረሰን በላይ እርስ በእርስ የተጨራረስነው ይበልጣል፡፡ ገዳይ እኛ፤ ሟች እኛ፤ ደም አፍሳሽ እኛ፤ አፈናቃይ እኛ፤ ተፈናቃይ እኛ ኾነን ስናበቃ የራሳችንን ሰው ገድለን ‹‹ሰበር ዜና›› ብለን የምናወጣው እኛ ነን፡፡ ቋንቋችን ባቢሎን ኾኖ ምድሪቱ አኬልዳማ የኾነችው በኃጢአት በመጣ ገንዘብ በመኖራችን ነው፡፡ ገንዘቡ ኃጢአት መግዣ እንጂ ትውልድ ቀያሪ መኾን አልቻልም፡፡ ኑሯችን እንደካሮት ቁልቁል ሄዷል፡፡ ኑሮው በየዕለቱ እየተወደደ ነው የሄደው፡፡ የጤና ማጣቱ፤ የውሃው ችግር፣ መብራት፣ ሰላም ማጣት፣ ሥራ ማጣት፣ የሞራል ውድቀት፣ የትምህርት ውድቀት ይኼ የመጣው በኃጢአት ነው፡፡
የእነርሱን እጅ እጅ በማየታችን የምናመጣው ለውጥ የለም፡፡ ይኼ የግብረሰዶም ሕግ የወጣው 1949 ነው፡፡ ወንጀሉ ግን እየተበራከተና እየተስፋፋ የመጣው የወንጀል ሕጉ ከተሻሻለ በኋላ ነው፡፡ በፊት በሥነ-ምግባር የታነጽን ስለኾንን ሽማግሌ ደካማ ምናምን አይታለፍም ነበር፡፡ አሁን ግን በጣም የተማረ ሰው ካገኘን በኋላ ሀገሪቷ በጣም እየተጎዳች መጥታለች፡፡ እናት ልጇን ፕሮፌሰር አድርጋዋለች፡፡ ፕሮፌሰር የኾው ግለሰብ ግን እናቱን መቀየር አልቻለም፡፡ አንድ ምሳሌ ለመናገር ያህል፣ በዐፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ የነበረው የዩንቨርሲቲ ቁጥር በደርግ ቀጥሎ በኢሕአዲግ ዘመን በዛ፡፡ የግል ዩንቨርሲቲ ኮሌጆች በዙ፡፡ በዚህም ብዙ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ ማስተር ያለው ኖሯል፡፡ ታዲያ ለምንድነው ሀገሪቷ ያልተለወጠችው? ስብዕና ማምረት ስላልቻልን ማንነታችንን ስላጣን ነው ፤ ሀገሪቷ እየተጎዳች ያለው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ከሞት በኋላ ገነት አለ ብላ የምታምን ሀገር ናት፡፡ ይቺን ሀገር ያቆረቆዟት ተምረናል ብለው የሚያስቡ የተማሩ መሃይሞች ናቸው፡፡ ይኽን ኃጢአት ወደ ሀገራችን እንዲገባ ያደረጉት በር እየከፈቱ ያሉት እነርሱ ናቸው፡፡ በባሕላችን ባልና ሚስት እንኳን በአደባባይ አይሳሳምም፡፡ ይህን ሥነ-ምግባርና አብሮነታችንን ነው ያጠፉት፡፡ ለምሳሌ አደምሻን የተባለ የ24 ዓመት ፕሮፌሰር ኢሉሚናቲን የፈለሠፈው ግንቦት 1 ቀን 1776 ዓ.ም ግላዊነትን አስቦ ነው፡፡ ድሮኮ ጎረቤት የጎረቤትን ልጅ ይቀጣል፡፡ አብሮ ይጫወታል፡፡ አሁን እህትና ወንድም እንኳን አብረው አይጫወቱም፡፡ አብሮነት ጠፋ፡፡ በሩን ክፍት አድርጎ ‹‹ቤቴን እዩልኝ›› የሚል የለም፤ ኮንደሚኒየሙም፣ ሪልስቴቱም ጎረቤትና ጎረቤት እንዳይተዋወቁ እያደረገ ነው፡፡ የሚጠቅሙ እሴቶቻችንን እንዲጠፉ እየተደረገ ነው፡፡ ወደራሳችን መመለሱ ነው የሚያስፈልገው፡፡
ግዮን፡- ለመንግሥትም ለሃይማኖት ተቋማትም ለሕዝቡም ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ?
ደረጀ፡- ቤተ ዕምነቶች በዚህ ዙሪያ ላይ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ጠንካራ አቋም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መንግሥትን ማስደንገጥ የሚችሉት ቤተ ዕምነቶች ናቸው፡፡ መንግሥትን መፍራት የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ቤተዕምነቶች ያደሩት ለነፍሳቸው እንጂ ለሥጋቸው አይደለምና ነው፡፡ ሥጋንም ነፍስንም ማዳን የሚችሉት ቤተዕምነቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ትውልዱ ላይ በጣም መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡
መንግሥትም ቢኾን የሚመጣው ዕርዳታ እንደማይጠቅመን ሊያውቅ ይገባል፡፡ የሚጠቅመን ወደ ፈጣሪ መመለስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሃይማኖት እና የባሕል ሀገር ናት፡፡ መንግሥት የዚህን ሕዝብ ፍላጎት ሊጠብቅለት ይገባል፡፡ 98 በመቶ የሃይማኖት በኾነበት ሀገር በፍፁም መንግሥት ለእርዳታ ብሎ ትውልዱን መግደል የለበትም፡፡ ትውልዱን ማቀጨጭና ስብዕናውን መንቀል የለበትም፡፡ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባሕል፣ ፍልስፍና እንዲሁም ሀገር በቀል እውቀትን ማጥፋት የለበትም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ወደ ቀደመ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ሊመለስ ይገባል፡፡
ከሕግ አንፃር ደግሞ ሕጉ በራሱ የሚያስገርም ነው፡፡ አንድ የግብረሰዶም ወንጀለኛ መክሰስ የሚያስችል ሕግ የለንም፡፡ ከዚህ በፊት አንድ ዳኛ ጠይቄ ነበር፡፡ አንዴ አንድ ግለሰብ የዘጠኝ ዓመት ልጅን በፊንጢጣዋ ተገናኛት፡፡ ይኽን ዳኛው ‹‹ደፈረ›› ሲል እኔ ደግሞ ‹‹ደፈረም፤ ግብረሰዶምም ፈጸመ››ም አልኩ፡፡ ዳኛው ግብረሰዶም ፈጸም ለማለት በምን ሕግ ይጠይቅ አለ፡፡ ሰው ብቻውንም ኾኖ ግብረሰዶም ሊኾን ይችላል፡፡ ከወንድም ከሴትም ጋር ኾኖ ግብረሰዶም ሊኾን ይችላል፡፡ ስለዚህ ሕጉ ላይ መሠራት አለበት፡፡ በተለይ እኛ ለሰላም ሚኒስቴር ያቀረብነው ባለ 25 ገፅ ሐሳብ ተግባራዊ ቢኾን ለትውልዱ መነሳት ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡ ጥራዙ እነ መምህር ፋንታሁን ዋቄን የመሰሉ ፈላስፋዎች ትልቅ ሐሳብ የሰጡበት ነው፡፡
ግዮን፡- እናንተን ለማግኘት፤ ጥቆማ ለመስጠት የሚፈልግ አካል ካለ በምን መልኩ እናተን ሊያገኛችሁ ይችላል?
ደረጀ፡- ቢሯችን ኢምፔሪያል ሆቴል አለፍ ብሎ አልፎዝ ሕንፃ 5ኛ ፎቅ ላይ ነው፡፡ ስልክ ቁጥር 09-22-21-21-21 የእኔ ስልክ ነው፡፡ ሥራ አስኪሂጇ ጋዜጠኛ ትዕግስት አምባው ትባላለች፡፡ 09-05-05-37-37 የእሷ ስልክ ነው፡፡ በመደወል ማግኘት ይችላሉ፡፡ ቢሮም በመምጣት ሐሳባቸውን ማጋራት ይችላሉ፡፡ በተለይ እዚህ አስከፊ ሕይወት ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢመጡና ከዚህ ሕይወት ቢወጡ የሞራልም ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በራችንም ልባችንም ክፍት ነው፡፡ እናተም ተከታትላቹ ስለዘገባችሁልን ከልብ እናመሠግናለን፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው በዚህ ዙሪያ መሥራት ይኖርበታል›› የሚል መልዕክት አለኝ፡፡ ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡
