Home ሰሞነኛ እገታ ኢኮኖሚያዊ ወይስ ፖለቲካዊ ጨዋታ?

እገታ ኢኮኖሚያዊ ወይስ ፖለቲካዊ ጨዋታ?

እገታ ኢኮኖሚያዊ ወይስ ፖለቲካዊ ጨዋታ?

ሕግና ሥርዓት ባለበት ሀገር ላይ እገታ መፈጸም የተለመደ ተግባር አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እገታ የሚፈጸመው የአንድ ሀገር መንግሥት የማስተዳደር አቅሙ እየደከመ ሲሔድ ነው፡፡ እገታ ሲባል እንግዲህ ብዙ አይነት እገታዎች አሉ፡፡ ስለመንግሥትና ሥርዓት ሲወራ ሊኾን የሚችለው እገታ ግን ምን ማለት ሊኾን እንደሚችል ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የመንግሥትን ደካማነት የሚጠቁሙ እገታዎች የሚፈጸሙት ያለፉትን ጥቂት ዓመታት እንደታየው ዐይነት እገታዎች ሲከሰቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሦስት ዓመታት በፊት በደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ እገታ ተፈጸመ ተብሎ ድፍን አማራ ክልልን በሰልፍ እንዳጥለቀለቀው አይነት እገታ የመንግሥትን ሥርዓት የማስከበር ዝንፈት የሚያሳይ እና አልፎም ፖለቲካዊ ሸፍጥን የተላበሰ እገታ ነው፡፡ ይህ አይነቱ እገታ ከዚያን ወቅት ጀምሮ በሀገራችን በጣም እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ እገታው በተለይም በኦሮሚያ ክልል እጅጉን ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡  

የኾኖ ኾኖ እገታው ኢኮኖሚያዊ ወይስ ፖለቲካዊ የሚለው ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ለመበየን ደግሞ እስካሁን የተካሄዱ እገታዎችን መመርመር ያሻል፡፡ ለምሳሌ እንደመጀመሪያ የሚቆጠረው የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታ ገንዘብ ያልተጠየቀበት ታጋቾች ደብዛቸው ጠፍቶ የቀረበት አንዳንዶች “ምናባውያን ታጋቾች” እያሉ የፖለቲካ ዶሴ የሚያሸክሟቸው ኾነው ይገኛሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የተከናወኑ በርካታ እገታዎች ግን በአንድ በኩል በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የተጠየቀባቸው በሌላ በኩል ከፍ ያለ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ናቸው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚፈጸሙ እገታዎች ከአንድ አቅጣጫ በሚጓዙ አሽከርካሪዎች እና መንገደኞች ላይ ማንነታቸው ተለይቶ በመኾኑ ፖለቲካዊ አንድምታው ግዘፍ ነስቶ ብዙ ሲባልበት ሰንብቶ እዚህ ደርሷል፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይም ከርእሱ አንጻር እገታው ስላለው ተጠየቅ መልስ ለመስጠት አሁን ላይ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በፌደራል መንገዶች ላይ እየተከናወነ ያለው እገታ ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም ሚና አለው ቢባል ስሕተት አይኾንም፡፡

ከዚህ አንጻር ኢኮኖሚያዊ ሚናው ምንድነው ቢባል እገታውን እየፈጸመው ያለው አካል አንድ የታጠቀ እና ፖለቲካዊ ጥያቄ ያለው አልፎም መንግሥትን በኃይል ለመቀየር የሚፈልግ ቡድን በመኾኑ እገታውን ፈጽሞ በሚያገኘው ገንዘብ የድርጅቱን የሎጂስቲክ አቅም ይገነባበታል፡፡ ይህ ሀቅ መኾኑንም አጋቹ ድርጅት በተለያዩ ወቅቶች በቪዲዮ የታገዙ መረጃዎችን በመስጠት አረጋግጧል፡፡ በተጓዳኝ ፖለቲካዊ ሚናው ሲታይ ደግሞ በአንድ በኩል መንግሥት በተለይ የፌደራል መንገዶችን መቆጣጠር አለመቻሉና በዚህ ሳቢያ በዜጎች ላይ የሚፈጠረው ስጋት ለአጋቹ ኃይል ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ትርፍ ያስገኝለታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሚታገተው የማኅበረሰብ ክፍል በአጋቹ ዘንድ እንደፖለቲካ ባላንጣ የሚታየው ልሂቅ አካል ስለኾነ የአሸናፊነት ሥነልቦናን ያጎናጽፈዋል፡፡

የዚህ ዓይነት እገታዎች በያዝነው ሐምሌ እና ሰኔ ወራት ብቻ ለበርካታ ጊዜያት ተፈጽመዋል፡፡ ሰኔ 10 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ኦሮሚያ ክልል ዓሊዶሮ በተባለ ቦታ ሹፌሮችና ረዳቶችን ጨምሮ 79 ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታግተው የተወሰዱበት ሁነት ተፈጥሯል፡፡ ቡድኑ በዚህ እገታ ከእያንዳንዱ ታጋች አንድ ሚሊዮን ብር ጠይቆ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሰኔ 8 ቀን  6 የሞኤንኮ ሠራተኞች ለሥራ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሄዱበት ታግተዋል። ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲሁ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ፤ በርካታ ሰዎችን ይኸው ቡድን አግቷቸዋል፡፡ በዚህ እገታም ቡድኑ በእያንዳንዱ ሰው ከ200 እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ ማስለቀቂያ ጠይቆበታል፡፡ የዚህ ቡድን እገታ ሌሎች አካባቢዎች ከሚፈጸሙ እገታዎች ለየት የሚያደርገው እገታውን ለሁለት ዓላማ ሲጠቀመው መታየቱ ነው፡፡ ይኸውም ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው በእገታው የገንዘብ አቅሙን ከማጎልበቱም በላይ ፖለቲካዊ ሥራን ያከናውንበታል፡፡ የፌደራል ዋና መስመርን በመዝጋት በሀገር ላይ ከፍ ያለ ሽብር ይፈጥርበታል፡፡ የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራትና የመኖር ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማስተጓጎል መንግሥትን እረፍት ይነሳበታል፡፡

ከዚህ አንጻር ለምሳሌ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በጎንደር አካባቢ በርካታ እገታዎች ይፈጸማሉ፡፡ በዚያ አካባቢ የሚደረጉ እገታዎች ተራ እገታና ዓላማውም ገንዘብ ማግኘትን ታላሚ ያደረገ ነው፡፡ እገታዎቹ የሚፈጸሙት በተደራጁ ኃይሎች ሳይኾን በአንድ ወይም ሁለት ሦስት ግለሰቦች አማካኝነት ነው፡፡ ከዚያ ከፍ ካለም ቅማንት በተሰኘው ታጣቂ ኃይል አማካኝነት የሚፈጸም ነው፡፡ የዚህ ቡድን ዓላማ ደግሞ እንደደቡቡ አጋች ቡድን መንግሥትን መገልበጥ ወይም መገዳደር ሳይኾን ተራ ጊዜያዊ ሽብር መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ቡድኑ የሚፈጽመው እገታ በነዋሪዎች ላይ ጊዜያዊ ሽብር ከመፍጠርና በማስለቀቂያነት የሚሰጠውን ገንዘብ ከመዝረፍ የተለየ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡ ይህ ቡድን ለምሳሌ ሰሞኑን በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ከሦስት ሳምንት በፊት፣ ስድስት ግለሰቦች አግቶ የጠየቀውን ማግኘት ባለመቻሉ ግድያ ፈጽሞባቸዋል። በተመሳሳይ ከሳምንት በፊትም ጥቂት አርሶ አደሮችን በማገት ገንዘብ ማግኘት ባለመቻሉ ግድያ አድርሷል፡፡ በጥቅሉ የዚህ ቡድን ዓላማ ሲታይ ከፍ ሲል እንደተነሳው ከገንዘብም በላይ በቀልና ሽብር መፍጠርን ታላሚ ያደረገ ነው፡፡

የኾኖ ኾኖ ከሰሞኑ ከጎጃም አዲስ አበባ መስመር ጉዞ ላይ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና  በጎሃጺዮንና ደብረ ጉራቻ መካከል “ቱሉ_ሚሊክ” የሚባል አካባቢ ይኸው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይል እገታ ፈጽሟል። ከዚህ ድርጊቱ በኋላም በታጋቾቹ ልክ በእያንዳንዳቸው በመቶሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ጠይቆባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት ባለው ሀገር ላይ እንዲህ ዓይነት ድርጊት በተደጋጋሚ ሲፈጸም መታየቱ እጅግ የሚያሳዝንና የመንግሥትን አቅም ተጠየቅ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ መንግሥት በየትኛውም መልኩ በተለይም በሚቆጣጠራቸው ዋና መሥመሮች ላይ የሚፈጸሙ የእገታ ወንጀሎን ማስቆም ይኖርበታል፡፡ መንግሥትና ሚዲያዎቹ ችግሩ በተከሰተ ቁጥር ባልሰማ ባላየ የሚያልፉት ከኾነ ወደፊት ከባድ ፈተና ሊደቅን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ እገታ አንዱ የሥርዓተ አልበኝነት መገለጫ ከመኾኑም አንጻር አንድ ለዜጎቹ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት የግድ ዜጎችን ከአጋች ታጋች ችግር ማላቀቅ ይኖርበታል፡፡ ያ ካልኾነ ግን መንግሥትን የሚያክል የጸጥታ መዋቅር ያለው ተቋም ቀላል የኾነውን ኃላፊነት መወጣት ባለመቻሉ የወንጀሉ ተባባሪ ኾነ ማለት ነው፡፡ እንደእውነታው ተራ እገታ የትኛውም ዓለም ላይ የሚከሰት ተግባር ነው፡፡ የእኛን ሀገር ልዩ የሚያደርገው ግን ተራ እገታ አለመኾኑ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር በአስቸኳይ ማስቆም የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ይህን ኃላፊነቱን መወጣት የማይችል ከኾነ ግን ዜጎች እራሳቸውን ይከላከሉ ዘንድ ራሱን የቻለ አቅጣጫ መቀየስ ይኖርበታል፡፡