የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በምስራቅ ሸዋ ዞን፣ አቡ ሴራ ወረዳ ሊገነባ የታቀደውን “የሜጋ ኤርፖርት ፕሮጀክት” አስመልክቶ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ የተጋረጠውን ስጋት ለህዝብ ለማሳወቅ ይህንን መግለጫ አውጥቷል።
ኦፌኮ በመግለጫው ባለፉት ሶስት ዓመታት የሸገር ከተማ ምስረታን እና የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማትን ተከትሎ የተከሰተውን ህገ-ወጥ የመፈናቀል ማዕበል በተመለከተ ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎችን ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሷል። ይሁንና አሁን በአቡ ሴራ የተፈጠረው ሁኔታ ችግሩ ወደ አደገኛ እና የከፋ ደረጃ መሸጋገሩን ያሳያል ሲል አስታውቋል።
መንግስት ከዚህ ቀደም ‘መፈናቀል ይቁም’ በሚል ያቀረብነውን ጥሪ ችላ ብሏል ሲል የወቀሰው ኦፌኮ ለአቡ ማህበረሰብ ይህንን ልዩ ‘ቀይ ማስጠንቀቂያ’ ለመስጠት ተገደናል ብሏል።
ኦፌኮ የመሰረተ ልማት አውታሮች ለሀገርና ለክልላችን ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላቸውን ፋይዳ ሙሉ በሙሉ ይቀበላል፤ ሆኖም ግን ፕሮጀክቱ እየተተገበረበት ያለው መንገድ የአካባቢውን ነባር ማህበረሰብ ከቅድመ አያት ርስቱ የሚያፈናቅልና ታሪኩን የሚያጠፋ በመሆኑ በጽኑ እንደሚቃወም አስታውቋል።
ፓርቲው የአቡ ማህሰብን የድረሱልን ጥሪ በጥሞና አድምጦ ተቀብሏል። የአቡ ማህበረሰብን ዋይታ እንሰማለን፤እናስተጋባለን ሲል በመግለጫው አስታውቋል።
በአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው ከ3,000 በላይ አባወራዎች እና 15,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች ከአቡ አቺሮ፣ አቡ ጋርቢ፣ አቡ ኮምቦልቻ፣ አቡ ሎያ፣ አቡ ሉግና እና አቡ ሳርካማ ቀበሌዎች ለመፈናቀል የተጋረጠባቸውን አደጋ ለመመከት ከጎናቸው እንቆማለን ሲል ፓርቲው ገልጿል።
1. ህገ-መንግስታዊና የህግ ጥሰት
የኦሮሞን አርሶ አደር ያለ በቂ ምክክር እና ፈቃድ ከርስቱ ማፈናቀል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 40ን የሚጥስ ነው። አንቀጹ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬትን የማግኘት እና ያለመፈናቀል መብትን ያረጋገጠ ነው። ህዝቡን በድንገተኛ ትዕዛዝ እና ማስፈራሪያ እንዲለቅ ማድረግ ህገ-ወጥ እና ሞራለ-ቢስ አካሄድ ነው።
2. የኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ የመፈናቀል ጠባሳ
ኦፌኮ ከዚህ ቀደም በቦሌ፣ በቆቃ እና በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች በህዝባችን ላይ የደረሰው አሳዛኝ ታሪክ በአቡ ሴራ ላይ እንዳይደገም ያሳስባል። በነዚያ ጊዜያት የኦሮሞ ማህበረሰብ ከቀዬው ተፈናቅሎ፣ ማህበራዊ ትስስሩ ፈራርሶ እና ማንነቱ ጠፍቷል። “የአፍሪካ ኩራት” በሚል ስም ትውልድን የሚያጠፋ ልማት ተቀባይነት የለውም።
3. የኢኮኖሚ ፍትህ እና ባለቤትነት (Stakeholding)
ለአርሶ አደሩ መሬት የህይወቱ ዋስትና እንጂ የሚሸጥ ሸቀጥ አይደለም። በጊዜ ሂደት ለሚያልቅ የገንዘብ ካሳ አርሶ አደሩን ማፈናቀል ለትውልድ የሚተላለፍ ድህነትን መፍጠር ነው። ሊገነባ የታቀደው “የኤርፖርት ከተማ” (Airport City) የአካባቢውን አርሶ አደር ያገለለ መሆን የለበትም። ስለሆነም ኦፌኮ አርሶ አደሩ በገንዘብ ካሳ ብቻ ሳይሆን መሬቱ እንደ ካፒታል ተቆጥሮ በፕሮጀክቱ ውስጥ የአክሲዮን ባለቤት (Shareholder) እንዲሆን እና ከልማቱ ዘላቂ ተጠቃሚ እንዲሆን ይታገላል።
ጥሪ እና አቋማችን
ለፌዴራል መንግስት፣ ለኦሮሚያ ክልል መንግስት እና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጅመንት የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናቀርባለን፡-
መፈናቀሉ በአስቸኳይ ይቁም፡ ገለልተኛ የሆነ የማህበራዊ እና የአካባቢ ተጽእኖ ጥናት (Social and Environmental Impact Assessment) ተካሂዶ ለህዝብ ይፋ እስኪደረግ ድረስ በአቡ ማህበረሰብ ላይ የሚደረገው ማስፈራሪያ እና መፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም።
ህጋዊ ምክክር፡ የአካባቢው ማህበረሰብ ወኪሎች፣ የሲቪክ ማህበራት እና የህግ ባለሙያዎች በተገኙበት ግልጽነት ያለው ድርድር እንዲደረግ።
ለአቡ ነዋሪዎች ባለቤትነት እንጂ መፈናቀል አይገባም፡ የአቡ ማህበረሰብ በኤርፖርት ከተማው ልማት ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ (Equity) እንዲኖረው እና መሬታቸው እንደ ኢንቨስትመንት ተቆጥሮ ዘላቂ ገቢ እንዲያገኙበት።
የባህል ጥበቃ፡ የአካባቢው ቋንቋ፣ ባህል እና እሴቶች በዚህ ግዙፍ የከተማ መስፋፋት እንዳይዋጡ ጠንካራ የህግ ዋስትና እንዲሰጥ።
የአለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ (AfDB) እና ሌሎች አበዳሪዎች ፕሮጀክቱ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መስፈርቶችን ማሟላቱን እንዲያረጋግጡ. አጥብቀን እንጠይቃለን።
ማጠቃለያ
ኦፌኮ የልማት ጠላት አይደለም፤ ነገር ግን የዝርፊያ እና የመፈናቀል ጠላት ነው። “የአፍሪካ ኩራት” ተብሎ የሚወደስ ፕሮጀክት በኦሮሞ አርሶ አደር እንባ፣ ውድመት እና ውርደት ላይ ሊገነባ አይገባም። የኦሮሞ ህዝብ፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአቡ ሴራ ህዝብ ድምጽ እንዲሆኑ ጥሪ እናቀርባለን።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
