የኢትዮጵያ ወጣቶችና የመካከለኛው መንገድ ትርክት አስፈላጊነት
የጽሁፍ አዘጋጅ ዶ/ር ታደሰ ብሩ
ግዮን መጽሔት :- ከፋፋይና ተፃራሪ ትርክቶች ለበርካታ ዜጎቻችን ሕይወት መቀጠፍ፤ ቁጥራቸው ለበዛ ወገኖች የአካል ጉዳት፤ ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ለሆኑ ወገኖቻችን መፈናቀል ምክንያት ለሆኑ ግጭቶች እንደዳረጉን ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አውዳሚ ለሆኑ ግጭቶች የዳረጉን በማኅበራዊ መስተጋብር በተገነቡና በሰረጹ ትርክቶች (socially constructed narratives) ላይ የተመሠረቱ ከሀብትና ሥልጣን በላይ መነሻቸው ሐሳብ ወይም እሳቤ የሆኑ ጦርነቶች ናቸው፡፡
ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቬሎፕመንት ፋውንዴሽን (YCDF) የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑት ወጣቶቻችን የነዚህ ጽንፈኛ ትርክቶች ሰለባና መሣሪያ እየሆኑ መምጣታቸው ያሳስበዋል፡፡ YCDF በተፃፃሪ ትርክቶች መካከል አስማሚና አስታራቂ የሆነው አዎንታዊ የወጣቶች እድገት (positive youth development) በሚለው መርሁ አማካይነት የመካከለኛው መንገድ ትርክት ለመገብንባት ይጥራል።
የትርክቶቹ ፍጥጫ፡ ወጣቱ የት ላይ ነው?
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለዘመናት ሲፋለሙ የቆዩ ሁለት ተፃራሪ ትርክቶች አሉ። የመጀመሪያው ኢትዮጵያን “የሥልጣኔና የነፃነት ማማ” (Cradle of Civilisation and Freedom) አድርጎ የሚስለው ሲሆን፣ አክሱምንና የዓድዋን ድል እንደ ምሳሌ ይጠቀማል።
ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያን “የብሔር፣ ብሔረሰቦች እስር ቤት” (Prison of Nations and Nationalities) አድርጎ የሚፈርጀውና የኢትዮጵያን ማኅበረሰቦች በበዳይና በተበዳይ የሚከፋፍለው በ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ገኖ የወጣው ትርክትነው።
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስለ ሀገራቸው ያላቸው ግንዛቤ በእነዚህ ሁለት ጽንፎች መካከል የሚንገዋለል ሆኗል፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ፣ በቤተሰብ ወግና በፖለቲካ ልሂቃን ቅስቀሳ አማካኝነት የሚደረገው ማኅበራዊ ኮትኩቶ የማሳደግ ሂደት (socialisation) ወጣቱን የአንዱ ጎራ ጠበቃና የሌላው ተቃዋሚ አድርጎታል፡፡
“የእስር ቤት” ትርክቱ ወጣቱን በታሪካዊ ቅሬታና በበቀል ስሜት እንዲሞላ በማድረግ ለማንንነት ፖለቲካ (identity politics) እንዲሰለፍ ሲያደርገው፣ “የነፃነት ማማ” ትርክት ደግሞ ከአህጉሩ አገሮች የተለየ አድርጎ በመውሰድ የውስጡን ችግር በማሳነስ አንድ ዓይነት ብሔራዊ ማንነትን (homogenising identity) ለመጫን ይሞክራል። ይህ ፍጥጫ ወጣቱን በ“ብሔር ደኅንነት ስጋት ወጥመድ” (ethnic security dilemma) ውስጥ ከቶታል፡፡
ሚዲያና አካዳሚ፡ የግጭት ማራገቢያ ወይስ የሰላምመድረክ?
ማኅበራዊ ሚዲያ ከተስፋፋ ወዲህ ከተፈጠሩ አሳሳቢ ጉዳዮች አንዱ ጦርነት በመሬት ላይ ከመጀመሩ በፊት በማኅበራዊ ሚዲያዎች (Facebook, TikTok, YouTube) የሚጀመሩ መሆናቸው ነው። ወጣቱ ዋነኛ የሚዲያ ተጠቃሚ በመሆኑ፣ በጥላቻ ትርክቶችና በተዛቡ መረጃዎች ተጽዕኖ ስር ይወድቃል።
ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚነሱ የብሔር ግጭቶች ሚዲያው የፈጠራቸው ትርክቶች ውጤቶች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ምሁራን (intelligentsia) ሚና አሳሳቢ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን ገለልተኛ የእውቀት አምራቾች ከመሆን ይልቅ፣ ለወጣቱ የጥላቻ ትርክቶችን በማቅረብ ታሪክን መሣሪያ በማድረግ (weaponising history) አንዱን ወገን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ አድርገው በመሳል ለግጭት መስፋፋት ሰንካላ ምክንያቶችን ሲያቀርቡ ይ
ሰተዋላሉ።
መፍትሔው፡ “የመካከለኛው መንገድ” ትርክት
ኢትዮጵያን አገራችን ካለችበት ቀውስ ለማውጣት ሦስተኛ መንገድ ያስፈልጋል። ይህንንም “መካከለኛው መንገድ” የኢትዮጵያን ታሪካዊ አንድነትና ሉዓላዊነት እያከበረ፣ በተመሳሳይ መልኩ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነትና ታሪካዊ በደሎችን አምኖ የሚቀበል ሚዛናዊ አመለካከት መሆንይኖርበታል። የመካከለኛው መንገድ ትርክት በራሱ እና ብቻውን አይወጣም፤ የሚከተሉት ድጋፎች ይፈልጋል።
1. ሕገ-መንግሥታዊ ሪፎርም (Constitutional Reform):
የ1995ቱ ሕገ-መንግሥት የብሔር ግጭቶችን በማባባስ ረገድ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም፣ ከብሔር ፌዴራሊዝም ወደ መልክዓ-ምድራዊ ፌዴራሊዝም (geographic federalism) መሸጋገር የመካከለኛው መንገድ ትርክት መዳበርን ያፋጥናል።
2. እውነተኛ ብሔራዊ ምክክር (Genuine National Dialogue):
እውነተኛ ብሔራዊ ምክክር ወሳኝ ጉዳይ ነው። በየደረጃው ምክክርና ውድይቶችን ማካሄድ ለመካከለኛው መንገድ ውልደት እና መ
ፋፋት ወሳኝ ነው።
3. ሂሳዊ አስተሳሰብ ትምህርት (Critical Thinking):
ወጣቱ የሚቀርቡለትን ትርክቶች እንደ ወረደ ከመቀበል ይልቅ፣ መርምሮና አጣርቶ እንዲረዳ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የሂሳዊ አስተሳሰብ ስልጠና መካተት አለበት።
4. የትርክት ሕክምና (Narrative Therapy):
በታሪክ አረዳድና ትርካዊ ምክንያት የስነልቦና ጥቃት የቆሰለውን የትውልድ ንቃተ-ህሊና ለመፈወስ፣ በጋራ እሴቶች ላይ የተገነባ አዲስ ብሔራዊ ትርክት መቅረጽ ያስፈልጋል። በከፋፋይ ትርክት የቆሰለውን ህሊና በአስታራቂ ትርክት ማከም ይገባል።
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ወጣቶች ካለፈው ትውልድ የወረሱት የጥላቻ ትርክት እስረኞች መሆን የለባቸውም። ወጣቱ የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ እንዲወስንና “ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ናት” የሚል አዲስ ማኅበራዊ ውል (social contract) እንዲመሰርት ማገዝ ይገባል። ሰላም የሚገኘው አንዱ ትርክት ሌላውን በማሸነፉ ሳይሆን፣ በልዩነቶቻችን ውስጥ የጋራ ትርክት መገንባት ስንችል ብቻ ነው። YCDF ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ይተጋል።
====================
የዚህን ጽሁፍ አዘጋጅ ዶ/ር ታደሰ ብሩ የYCDF Program and Partnership Director ናቸው፤ በ tkersmo@yahoo.com በኩል ማግኘት ይቻላል።
ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 229 የካቲት 2018 ዓ.ም
