✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)ከአሜሪካ ኒውጀርሲ
አንዳንድ ጉዞዎች በእግር አይጀምሩም፤ በሕልም ይጀምራሉ። አንዳንድ ድሎችም በዋንጫ አይለኩም፤ ከአመታት በፊት በልብ ውስጥ የተዘራ ተስፋ ሲያብብ ነው የሚለኩት።
ከ24 ዓመታት በፊት እግር ኳስን ለማየት የምገፋው ዊልቼር ነበር፤ ፊቴ ያለው ደግሞ ሽቦ። ሜዳውን በሙሉ ማየት አልችልም ነበር፤ ግን ሕልሜን ማንም ሊያጥረው አልቻለም። ያኔ ማን ያስብ ነበር አንድ ቀን ሕልሜ በዓለም ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ ላይ እውን እንደሚሆን?
ሕይወት አንዳንድ ጊዜ ከምናልመው በላይ ድንቅ ታሪክ ትጽፋለች። በቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ ብቻ የማያቸውን የዓለም ታላላቅ ከዋክብት ዛሬ በዓይኔ በብረቱ በቀጥታ እያየሁ እግር ኳስን ከምንጩ መጠጣቴን መቀጠሌን ሳስብ፣ አሁንም የሕልም ይሆንብኛል።
ዛሬ በኒውጀርሲ በተካሄደው የ2026 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ፣ ከዓለም አቀፍ ፖለቲካ አነጋጋሪ ክስተቶች ፊት የሆኑት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በተመሳሳይ ስታዲየም ውስጥ ተቀምጬ ጨዋታውን ማየት ለእኔ የማይረሳ ትውስታ ነው።
ሰውን ከቴሌቪዥን ውጪ፣ በእውነቱ ፊት ለፊት ማየት የሚፈጥረው ስሜት በቃላት ለመግለጽ ያስቸግራል።
ነገር ግን የፍፃሜው ቀን ትልቁ ስጦታ ይህ ብቻ አልነበረም።
ሁለት የማይረሱ ስሜቶች በልቤ እንዲፈራረቁ አድርጓል፤
ዛሬ የማካፍላችሁ የመጀመሪያውን ብቻ ነው።
እ.ኤ.አ. 2022 በካታር የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ፣ የዓለም እግር ኳስ ንጉሥ ሊዮኔል ሜሲ ሕይወቱን ሙሉ የተከተለውን ሕልም ሲያሳካ በቅርብ አየሁት።
በዚያ ቅጽበት በፊቱ ላይ የነበረው ደስታ ወጠን የሌለው ነበር፤ ነገር ግን ከዚያ የሚበልጠው በዓይኑ ዳር የተከማቸው እንባ ነበር።
አንድ ንጉሥ ፈገግ እያለ ልቡ ሲሰበር፣ የደስታ እንባ የዓይኑን ግድብ ጥሶ ለመፍሰስ ሲታገል ማየት እንዴት ያለ ትምህርት ነው! ያኔ በልቤ ውስጥ አንድ ቃል ብቻ ተወለደ፤”አይ… የሰው ልጅ!”የሚል፤
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት የተሳተፉበትን ታሪካዊ ውድድር ከመክፈቻው እስከ ፍፃሜው በክብር ተከታትዬ ተመለከትሁ።
በአንድ ሜዳ ላይ ሜሲን፣ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝን፣ ኤንዞ ፈርናንዴዝን፣ ጁሊያን አልቫሬዝን፣ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝን፣ እንዲሁም የነገውን የእግር ኳሱ አልጋ ወራሽን ላሚን ያማልን፣ ማርክ ኩኩሬላን፣ ፔድሮንና ኒኮ ዊሊያምስን በቅርብ ማየት የሕልም ዓለም ውስጥ የመኖር ያህል ነው።
ያኔ ግን ራሴን አንድ ጥያቄ ጠየቅሁ፤
“ከዚህ በላይ ምን ደስታ አለ? ከዚህ በላይ ስኬትስ ምን አለ?”
ወዲያው ግን ሌላ ምስል በአዕምሮዬ ተመለሰ።
ከ24 ዓመታት በፊት፣ በዊልቼር የሚሄዱ ባለውለተኛዬን ስገፋ ከሽቦ ጀርባ ሆኜ ኳስ ለማየት ዊልቸር ሲገፋ የነበረው ትንሹ ልጅ…
ዛሬ ደግሞ በዓለም ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ተቀምጦ የፍፃሜ ጨዋታን በዓይኑ እያየ ነው።
ይህ የትጋት ታሪክ ብቻ አይደለም፤ ይህ የፀጋ ታሪክ ነው።
እኔ የሄድኩትን መንገድ ተመልክቼ የማውቀው አንድ እውነት ብቻ አለ፤ ይህን ሁሉ በራሴ ኃይል አላመጣሁትም።
ከላይ የተከፈተልኝ በር፣ ከፈጣሪ የተሰጠኝ ጸጋ እና ወርቃማ ዕድል ነው።
ስለዚህ ዛሬ የምጽፈው የድል ታሪክ ሳይሆን፣ የምስጋና ታሪክ ብቻ ነው።
